የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልካም ባልንጀራ

“ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፡- ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው”
/ዮሐ. 1፡45-46/።
 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጓደኛ ወደ ሕይወትም ወደ ሞትም የመምራት አቅም አለው። ፈጣሪውን፣ ወላጆቹን፣ አስተማሪዎቹን የማይሰማ ጓደኛውን ይሰማል። ሰው ለሃይማኖት አባቱ የማያወራውን ኃጢአቱን ለባልንጀራው ያወራል። ባልንጀራ ለምን እንዲህ ቅርብ ሆነ? ስንል አድጎ በጌትነት፣ አንሶ በሎሌነት የማይቀርብ በእኩያነት ግን የሚያዋራ ስለሆነ ነው። የሰው ልጅ ኃጢአትና መከራ የጀመረው በክፉ ባልጀርነት ነው። ሔዋንና እባብ አጉል ባልንጀራ ሆኑ። አጉል ባልንጀርነት እንደ እባብ ቆዳ ልስላሴ አለው። ንግግሩም የማባበል ነው። ሁሉንም ነገር ቀለል አድርጎ ይመለከታል። ሁሉም ነገር ትክክል ነው ብሎ ያምናል። የመንፈሳዊነትና የሕግ ገደብ የለበትም። ፍጹም ግልጽነቶች አሉት። አንዱ ያንዱን ምሥጢር ይጠብቃል። አንዱ በአንዱ ኪስ ያዝዛል። መፈራራት የለም። አንድ መጠጥ ካወረዱ ቂምን ይረሳሉ። የሚያስጨንቅ ነገር መስማትም ማሰማትም አይፈልጉም። የራሳቸውን የሰዓታት ዓለም ይመሠርታሉ። በምኞትም ይሰክራሉ። እባብ ሔዋንን አምላክ መሆን ይቻላል እንዳላት ክፉ ባንጀርነትም በምኞት የማይጨብጠው ነገር የለም። አንዱ ስለ አንዱ ጥሩ ያወራል። በዚህ ኅብረት ውስጥ ቤተሰብ እንኳ ሰብሮ መግባት አይችልም።
 የእባብና የሔዋን ብቻ ሳይሆን የሶምሶንና የደሊላ ባልንጀርነትም መጨረሻው ውርደትንና ሞትን ወልዷል። ክፉ ባንጀርነት የተቀባውን ሶምሶንን ሳይቀር አስቷል። ለዚህ ነው ሐዋርያው፡- “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ያለው /1ቆሮ. 15፡33/። አይለውጡኝም እለውጣቸዋለሁ የሚለው ንግግር ሞኝነት ነው። ሰዓቱ፣ ቦታው፣ ሁኔታው፣ መላመዱ ይረዳቸዋል። ሰይጣን በመጀመሪያ አንድን ነገር እንድንለምደው እንጂ እንድናደርገው አያደርገንም። መጀመሪያ ዓይንና ጆሮአችን እንዲለምደው ያደርጋል። ከዚያ በኋላ መፈጸሙ ቀላል ነው። ይልቁንም አዲስ ክርስቲያን ክፉ ባልንጀርነትን በጣም መጠንቀቅ ያስፈልገዋል። የእርሱ ከምድር መራቅ ጠረጴዛ ላይ እንደ መውጣት ነው። ጠረጴዛ ላይ የቆመው ከታች ያለውን ከመጎተት፣ እታች ያለው ጠረጴዛ ላይ ያለውን መጎተት ይቀለዋል። የመሬት ስበቱም ያግዘዋል። አዳዲስ ክርስቲያኖች እስኪጸኑ ከክፉ ባልንጀርነት ፍጹም መለየት ይኖርባቸዋል። አምኖንም በክፉ ባልንጀራ ምክር እህቱን ደፈረ። በኋላም በአቤሴሎም ተገደለ /2ሳሙ. 13/።
መልካም ባልንጀራ ድኖ ያድናል። ዮናታንና ዳዊት በብሉይ ኪዳን፣ ፊልጶስና ናትናኤል በአዲስ ኪዳን ምሳሌ ናቸው። የዚህ ዓለም ንብረት የሚያጋድለው አይበቃም የሚል ፍርሃት ውስጥ ሰው ስለ ገባ ነው። ክርስቶስ ግን ቢሰጡት የማያልቅ ሀብት ነው። ዓለም በገንዘብ ይጣላ። እንዴት በክርስቶስ እንጣላለን? እርሱ የሚበቃ ሀብት ነው። “ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፡- ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው” /ዮሐ. 1፡45-46/። የፊልጶስ ንግግር መጻሕፍት እንደ መረመረ ያሳያል። መላው ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ያውቃል። በዚያ መሠረት ክርስቶስን አምኗል። እምነቱን የመሠረተው የጊዜ ነፋስ ላይ ሳይሆን መጻሕፍት ላይ ነው። የቃለ እግዚአብሔር መሠረት አይናወጥም። በክርስቶስ አለማመን ለአይሁዳውያን ሙሴንና ሕጉን፣ ነቢያትንና ትንቢታቸውን አለመቀበል ነው። ከሚያከብሯቸው ከነ አብርሃምና ከነሙሴ የሚለያዩት በክርስቶስ ነው። ጌታ ቢጣላ ሎሌ ይጣላልና።
መላው ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ይናገራል። ክርስቶስ በሥጋ የማይመጣ ቢሆን ኖሮ ብሉይ ኪዳን መመሥረት አያስፈልገውም ነበር። የብሉይ ኪዳንን ምሥረታ የወለደው አዲሱ ኪዳን መታሰቡ ነው። ስለዚህ ብሉይ ኪዳንን የተስፋ ወንጌል አዲስ ኪዳንን የፍጻሜ ወንጌል ብንለው ትክክል ነው። ሐዋርያው፡- “በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ”ይላል /ገላ. 3፡8/። አብርሃም ወንጌል ከተሰበከ ብሉይ ኪዳን የተስፋ ወንጌል መባሉ ትክክል ነው። ብሉይ ኪዳን ያለ አዲስ ኪዳን ፍጻሜ የሌለው ጅምር ነው፤ አዲስ ኪዳን ያለ ብሉይ ኪዳን ጅማሬ የሌለው ፍጻሜ ነው። ሁለቱ ኪዳናት ተናባቢ እንጂ ተቃራኒ ኪዳናት አይደሉም። አይሁድ ሕጉን በትክክል መተርጎም ባለመቻላቸው ክርስቶስን ገፉት። ሰው በትክክል ኦሪትን ቢኖር ክርስቶስ ጋ መድረሱ አይቀርም። ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ኪዳን በመሆኑ ክርስቶስን የሚገፋ አይደለም። ሰው በራሱ ኪዳን ውስጥ ሲሆን ብቻ ክርስቶስን ይገፋል።
ፊልጶስ ጌታችንን የዮሴፍ ልጅ ይለዋል። እውቀቱ እንዳልጠራ ያሳያል። ጌታችን በምድር አባት የሌለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በሰማይና በምድር አባቱ አንድ ነው። በሰማይና በምድር አብም አንድ ልጅ አለው። ለክርስቶስ ሁለት አባት፣ ለአብም ሁለት ልጅ መስጠት አይገባም። በአምላክነቱ የማያመኑ ሁለት አባት ይሰጡታል። በተዋህዶው የማያምኑ ሁለት ልጅ ያደርጉታል። እርሱ ግን ወልድ ዋሕድ – አንድያ ልጅ ነው። ፊልጶስ እውቀቱ ያድግና አንድ ቀን አብን አሳየን ይላል። ጌታ ግን እኔ በአብ ክብር አለሁ ብሎ ይመልስለታል /ዮሐ. 14፡8-9/። ጨርሰን አውቀን ጌታን አንከተለውም። ጨርሰን ተቀድሰን ወደ እርሱ አንመጣም። ከእኛ እሺታ ይጠበቃል። ማሳደግ ግን የእግዚአብሔር ድርሻ ነው /1ቆሮ. 3፡6/። ዮሐንስ ወንጌሉን በሚጽፍበት ጊዜ ፊልጶስ በዚህ እውቀት ውስጥ አይደለም። ግን ዛሬ ላይ የደረሰው ከዚህ ተነሥቶ ነው ለማለት ይህን ይጽፋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለደካሞች የተስፋ መጽሐፍ የሆነው ፍጹምነትን የሚናገር ሳይሆን በሰው ድካም ላይ የበረታውን የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚናገር በመሆኑ ነው።
የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል አለ። መጥፎ የሚባል ሰፈር ያደገ ሰፈር ለውጦ ይናገራል እንጂ ሰፈሬ እዚህ ነው አይልም። ጌታችን ግን የኃጢአተኞች ወዳጅ መሆኑን ለመግለጥ የናዝሬቱ ኢየሱስ መባልን ፈለገ። እርሱ ኃጢአትን ይጠላል፣ ኃጢአተኛን ግን ይወዳል። የዛሬው ዓለም ደግሞ ኃጢአትን ይወዳል፣ ኃጢአተኛውን ይጠላል። ይወገር ይሙት ይላል። ክርስቶስን መካድ እየበዛ መሆኑን የሰው ፈራጅነት ያሳየናል። ጌታችን በተሰቀለ ጊዜም ከእሾህ አክሊሉ በላይ በመላው ዓለም ቋንቋ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት ተጽፎ ነበር /ዮሐ. 19፡20/። ዛሬም የናዝሬቱ ኢየሱስ ይባላል። ይህ ስያሜ የሚያበረታቸው ብዙ ደካሞች አሉና። እርሱ በደካሞችና በኃጢአተኞች መከሰስ መወቀስ አይፈራም። “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው” ይላሉ ፈሪሳውያን /ማቴ. 9፡11/። ጌታ ግን እርሱን ለተጠጉ መልስ ይሰጣል። መልካም መማጸኛ ነውና። ዛሬም የኃጢአት ቊስል አላስተኛ ያላችሁ፣ እኔን የሚቀበል ማነው? የምትሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጃችሁ ነው። በር ቆላፊዎችን፣ መንገድ ዘጊዎችን፣ የሚዳስሱትን ሳይሆን የሚያጋፉትን እያያችሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በዚህ አትለኩት። እርሱ ልዩ ነው። የሰው እንኳን ክፋቱ ደግነቱም አይገልጠውም። ዛሬም ክርስቲያን ፈሪሳውያን ስለ ኃጢአተኞች ክርስቶስን ይከሱታል። ተማጻኙን መንካት አማጻኙን መንካት ነው። እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ይቅርና ኤምባሲ የተጠለለም አይነካም።
ጌታ ሆይ መልካም ጥግ ነህ፣ አንተን ያለውን ለአራዊት አትሰጥም። በእውነት ተመስገን። በቅዳሴአችንም፡-
“ካስነሣሃቸው ከሙታን ወገን፤
ከጠበቅሃቸው ከሕያዋን ወገን፤
ካነጻሃቸው ከርኩሳን ወገን፤
ካጸደቅሃቸው ከኃጥአን ወገን፤
ከሰበሰብሃቸው ከተበተኑት ወገን፤
ከመለስሃቸው ከበደሉትም ወገን ላንተ መታመን አለህ አሜን”
                       /ቅዳሴ ዮሐ. ወ.ነጎ. ቊ. 42/
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ