መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » አዲስ ኪዳን » የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ »          ሰባቱ ተአምራቶች

የትምህርቱ ርዕስ |          ሰባቱ ተአምራቶች

 
 እጅግ አስደናቂ ከሆኑ ክፍሎች አንዱ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ነው። ይህ ምዕራፍ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ተሰብኳል ። በመጀመሪያው ቀን ቆመው መጨረሻው አልታይ ላላቸው ፥ ነገሮች ሁሉ በማለዳ ሠርክ ለሆኑባቸው፥ ጉዳያቸው እንደ ተወለደ ላረጀባቸው ይህ ምዕራፍ ሲያጽናና ኑሯል ። ወንጌላዊው በጥንቃቄ እንደ ዘገበልን እንረዳለን ። የወንጌሉ ዓላማ እንደ ማቴዎስ ወንጌል የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በመጥቀስ ክርስቶስ የትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ማብሰር አይደለም ። እንደ ማርቆስ ወንጌልም የክርስቶስን የእጁን ተአምራት በመጥቀስ የእግዚአብሔር ልጅነቱን መግለጽ አይደለም ። እንደ ሉቃስም የነገሩን ቅደም ተከተል መተረክና ምሳሌያዊ ገለጻዎችን ማውሳት አይደለም። የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ የክርስቶስን ዘላለማዊነት መግለጥና ቀጥተኛ የክርስቶስ ትምህርቶች ማወጅ ነው ። የሁሉም ወንጌላት ዓላማ አንዱን ክርስቶስ መግለጥ ቢሆንም ከአራት አቅጣጫ የሚያሳዩን እይታ ወደ ሙሉ መልክ ያደርሰናል ። ስለዚህ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የክርስቶስን አምላክነት ለመግለጥ እንደ ማስረጃ የቀረቡት አራት  ናቸው ። የመጀመሪያው የዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነት፤ ሁለተኛው ሰባት ተአምራቶች ፤ ሦስተኛው የጌታችን ቀጥተኛ ትምህርቶች ፤ አራተኛው ሞትን አሸንፎ በሥልጣን መነሣቱ ናቸው።
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን ያነሣል።
1-  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር ማድረጉን ፤
2-  ቤተ መቅደሱን ከነጋዴዎች ማጽዳቱን ፤
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሰባት ተአምራቶች ተጠቅሰዋል ። ወንጌላዊው እነዚህን ተአምራት የጠቀሰው የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ለመግለጥ ነው። እነዚህ ሰባት ተአምራቶች፡-
1-  የውሃውወደ ወይን ጠጅ መለወጥ ። 4፥1-11 ።
2-  የብላቴናው መፈወስ ። 4፥46-54 ።
3-  የመጻጒዕ መዳን ። 5፥2-9 ።
4-  የበረከተው እንጀራ ። 6፥1-14 ።
5-  የተገሰጸው ማዕበል ። 6፥16-21 ።
6-  የዕውሩ መዳን ። 9፥1-12 ።
7-  የአልዓዛር ከሞት መነሣት ። 11፥38-44 ።
 ዮሐንስ ብቻ የዘገባቸው ተአምራቶች የቃናው ውኃ ወደ ወይን መለወጥ ፥ የብላቴናው መፈወስ ፥ የመጻጕዕ መዳን ፥ የዕውሩ ዓይን መብራት ፥ የአልዓዛር ከሞት መነሣት ናቸው ። ጌታችን የማይቆጠሩ ብዙ ተአምራቶችን ቢያደርግም ዮሐንስ ግን የመረጠው ሰባቱን ተአምራቶች ነው። ተአምራቱን የገሊላና የኢየሩሳሌም ብለን ለሁለት መክፈል እንችላለን ። የገሊላ ተአምራቶች የደቀ መዛሙርቱን እምነት ለማጽናት የሆኑ ናቸው ። የቃናው ውኃ ወደ ወይን መለወጥ ፥ የብላቴናው መፈወስ ፥ የበረከተው እንጀራና የተገሰጽው ማዕበል የገሊላ ተአምራቶች ናቸው ። የመጻጕዕ መዳን ፥ የዕውሩ ዓይን መፈወስ ፥ የአልዓዛር ከሞት መነሣት የኢየሩሳሌም ተአምራቶችና አይሁድን ለመርዳት የተደረጉ ናቸው ። የኢየሩሳሌም ተአምራቶች ብዙ ክርክርና ጠብ አሥነስተዋል ። የገሊላው ተአምራቶች ምስጋናና አምልኮትን ወደ ክርስቶስ ሲያመጡ ፥ የኢየሩሳሌም ተአምራቶች ግን ክርክርንና ጠብን አምጥተዋል ። የኢየሩሳሌም ተአምራቶች ይህን የወለዱት ለምንድነው ? ኢየሩሳሌም የአገልጋዮች የካህናት ፥ የተራዳኢዎች የሌዋውያን ፥ የመጻሕፍት አዋቂዎች የጸሐፍት ፥ የወግ አጥባቂዎች የፈሪሳውያን ፥ የሃይማኖት መሪዎች የሊቃነ ካህናት መኖሪያ ናት ። እነዚህ ለእውቀት እንጂ ለእምነት ያላደሉ ፥ ከእግዚአብሔር ክብር የራሳቸውን ክብር የሚያስቀድሙ ወገኖች ተአምራት ያደነድናቸዋል እንጂ ልባቸውን አይነካውም ። ስለ መለኮታዊው ኃይል እንጀራ ሆኖባቸው ይናገራሉ እንጂ የሰማይ ጉዳይ የላቸውም ።
 የደቀ መዛሙርቱን ልብ ለማጽናት የተደረጉት አራት ተአምራቶች ምንድነው ምሥጢራቸው ? የቃናው ውኃ ወደ ወይን መለወጡ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ግንኙነቱ ምንድነው ? በቃና ዘገሊላው ሠርግ ላይ እናትም አማኝም የነበረችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ። ልጇ ክብሩን ሠውሮ ፥ ውርደትን መርጦ መኖሩ ለእርሷ ይቆጫታል ። ይህ የእናትነትም የአማኝነትም ልብ መገለጫ ነው ። ከመጨረሻው የሚጀምር መሆኑን ባለቀው ድግስ ላይ የነበረውን ግብዣ ያየ ጴጥሮስ ፥ እኔም ሽምግልናዬ ይለመልማል ብሎ እንዲያምን አደርጎታል ። የመለወጥ ፍላጎት እንጂ አቅም ያልነበራቸው ደቀ መዛሙርት የእኛንም ሕይወት ጌታ እንዲህ ይለውጠዋል ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል ። የብላቴናው መፈወስ ጌታ ለባለሥልጣናትና ለአሕዛብ ዓላማ እንዳለው የገለጠላቸው ነው ። የበረከተው እንጀራ ጌታ በባዶ እንደሚያኖር የተረዱበት ፥ የማዕበሉ መገሰጽም ያስጨነቃቸው እንደሚረገጥ የተማሩበት ነው ።
ሦስቱና የኢየሩሳሌም ተአምራቶች የተባሉት ግን በአይሁድ ክርክር ብዙ ትምህርት የተገኘባቸው እንደሆኑ እንረዳለን ። የዮሐንስ ወንጌል በአብዛኛው ኢየሩሳሌም ላይ ያተኩራል ። ይልቁንም ከምዕራፍ 13 ጀምሮ የሚናገረው በኢየሩሳሌም ስለ ተፈጸመው ነገርና ስለ ተሰጠው ትምህርት በመሆኑ የኢየሩሳሌም ወንጌል ተብሎ ይጠራል ። ሌሎቹ ወንጌላት ግን የገሊላ ወንጌል የሚል ስያሜ ያገኛሉ ። በኢየሩሳሌም የተደረጉት ተአምራቶች የመጻጒዕ መዳን ፥ የዕውሩ መፈወስ ፥ የአልዓዛር ከሞት መነሣት ለየት ያሉ ተአምራቶች ናቸው ። መጻጒዕ የሠላሣ ስምንት ዓመት በሽተኛ ነው ፥ ዕውሩ ዓይኑ ግንባር የሆነበት ነውና እንደ ገና የዓይን ቅርጽ የሚያሻው ነው ፥ አልዓዛርም የአራት ቀን ሬሣ ነው ። ይህን ያህል ዓመት የታመመ በሽተኛ የለም ። ስለዚህ ፈውሱ ከሌሎች ፈውሶች ይለያል ።ዕውሮች በርተዋል ግን ዓይኑ ግንባር የሆነበትን ሰው እንደገና ጭቃ አቡክቶ ሠራው ። ከሞት የተነሡ ብዙ አሉ ። አልዓዛር ግን ከተቀበረ አራት ቀን የሆነው ሬሣ ነው ። የኢየሩሳሌም ተአምራቶች እጅግ የተለዩ ናቸው ። ወንጌላዊው የመረጣቸው ተአምራቶች በርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዱ ናቸው ።
 የጌታችንን አምላክነት ለመግለጥ ሰባት “እኔ ነኝ” የሚሉ መልእክቶችን ወንጌላዊው ጽፏል። በእነዚህ መግለጫዎች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን እንዳስረዳ እናያለን። እነዚህ ሰባት ተአምራትንም የጠቀሰበት ዓላማ ለአምላክነቱ አስረጂ እንዲሆኑ ነው ። ሰባት ፍጹም ቊጥር ነው ካልን ተአምራቱም ፍጹም አስረጂ ናቸው ማለት ነው ። ተአምራቶቹ ሲፈጸሙ የራሳቸው የሆነ ባሕርይና ምላሽ ነበራቸው።
ተአምራቱምልክት የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል /2፥11 ፤ 4፥54/። ምልክት ወደ ዋናው ለመድረስ ማሳያ እንጂ ፍጻሜ አይደለም ። እንዲሁም እነዚህ ተአምራት ስለ ትልቁ መዳን የሚያስረዱ እንጂ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የመጨረሻ ዓላማ የሚያብራሩ አይደሉም ። መዳን የክርስቶስን አምላክነት ከመቀበል ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። ማዳን የእግዚአብሔር ነውና ። ተአምራትን እንደ ፍጻሜ የቆጠሩ ሰዎች ፡-
·       ተአምራት አድራጊውን ሳይሆን ራሱን ተአምራትን አምልከዋል ።
·       የተሻለ ተአምር ፍለጋ ባዝነዋል ።
·       የዘላለሙን አምላክ ለጊዜያዊ ዓለም ብቻ ተጠግተዋል ።
·       ተአምራቱን ነጥቀው ሮጠዋል ።
 ስለዚህ ሐዋርያው እነዚህን ተአምራቶች ምልክት በማለት መግለጡ ፍጻሜ እንዳልሆኑ ማስረጃ ነው ። ምልክት ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ለመድረስ አመላካች እንጂ ጉዳይ ፈጻሚ አይደለም ። በምልክቱ ወደ መሥሪያ ቤቱ ያልደረሰ ምልክቱ እንደማይጠቅመው ተአምራቱ ወደ ክርስቶስ ካላቀረበም ከንቱ ነው። ለዚህ ነው የቃና ዘገሊላው ተአምር ከተፈጸመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዳመኑበት የተጻፈው /2፥11/ ።
 ተአምራቶች ሲፈጸም የማያምኑ ሰዎች ይበልጥ ይደነድናሉ ። ተአምራቶች ቢደረጉ ብዙ ሰዎች ወደ እውነት የሚመጡ ይመስለናል ። ተቃዋሚዎች በጌታችን ላይ የበለጠ ጥላቻና ሞትን የሚያፋጥን ጭካኔ ውስጥ ያስገባቸው ምክንያት ተአምራቶች ናቸው ። ለምሳሌ የዳነው አልዓዛርና ያዳነውን ጌታ ለመግደል ተነሥተዋል ። የመጻጒዕ መዳን ፥ በደረቅ ግንባር ዓይን የተሠራለት ሰው መፈወስ ታላቅ አምባጓሮ አስነሥቷል ። ተአምራቶች ያለንን ነገር ያጠነክራሉ እንጂ አዲስ ጠባይ አይሰጡንም ። ያመነ ይበልጥ ያምናል ። የማያምነው ይበልጥ ይደነድናል ።
 ሰዎች ለምድራዊ ፍላጎት ተነሣሥተዋል ። ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ አበርክቶ የመገበው ያ ሕዝብ ጌታን ለማንገሥ መጥቷል /ዮሐ. 6፥15/ ። ባገር ማንገሥ ቀላል ነው ። በልብ ማንገሥ ግን እምነት ነው ። ባገር የሚነግሥ ሎተሪ የወጣለት ነው ። በልብ የሚነግሥ ግን የታመነው አምላክ ነው ። እነዚህ ሰዎች ጌታን ማንገሥ ብቻ አይደለም ፥ ዐርባ ዓመት በምድረ በዳ መና እንደ በሉት እስራኤላውያን ለመኖር ፈልገዋል ። ተአምራትን ለስንፍና ተጠቀሙበት ። እስራኤል በምድረ በዳ መና የበሉት እግዚአብሔር ክብሩን ሊገልጥላቸው ስለ ወደደ ብቻ ሳይሆን ለመዝራትና ለማጨድ ለማብሰልና ለመመገብ ስፍራው ስለማይረዳ ነው ። ወደ አገራቸው አንድ ጫማ ሲረግጡና ዘርተው እህል ሲሰበስቡ ግን መናው ቆሟል ። መና ስንፍናን ማበረታቻ አይደለም ። ተአምራት የሚፈልጉ ሰዎች በአብዛኛው ሰነፎች ናቸው ። ለማስተማር መማር የማይፈልጉ ፥ ለመሥራት መጣርን የማይሹ ናቸው ። ቤተ ክርስቲያን ለአገልጋዮች ትምህርትና ተግባረ ዕድን ማሰልጠን አለባት ። ጳውሎስ ድንኳን ሰፊ እንደ ነበረ እናነባለን ። ተግባረ ዕድን መማር የሚጠቅመን ፡-
1.  አገልግሎትበጣም አድካሚ ነው። አንድ ስብከት ማዘጋጀት ፥ ለሁለት ሰዓት መቀደስ ፥ ሌሊቱን ሙሉ በቁመት ማደር አያል ተግባር ነው። ይህ ጸጋ ባይኖር አይዘለቅም ነበር። ይልቁንም የሰዎችን ንስሐና ችግር መስማት ምን ያህል አቅም እንደሚነሣ የታወቀ ነው ። አገልጋዮች ታዲያ አዲስ አየር ከሚወስዱበት ነገር አንዱ ተግባረ ዕድ ነው።
2.  ሙሉ በሙሉ በምእመናን ላይ መደገፍ ተገቢ አይደለም። ምእመናን ልጆች ናቸው ። ልጅ ምንም ፍቅር ያለው ቢሆንም መስጠት ግን አይችልም ። ይቆጥራል ። ከደግ ልጅ ክፉ ባል ይሻላል ። በድፍረት አምጣ የሚባለው ያ ክፉ ባል ነው ። ምእመናንም የመንፈስ ልጆች ናቸውና መቊጠር ያበዛሉ ። ስለዚህ አገልጋዮች ሙሉ በሙሉ በምእመናን ላይ ባይደገፉ መልካም ነው ። ዛሬ ተአምራት እናደርጋለን የሚሉ ትልቁ አሳባቸው የሰው መዳን ሳይሆን የእነርሱ መታወቅና ያ መከረኛ ገንዘብ ነው ።
 ተአምራትን መፈለግ በአብዛኛው ሰነፎች የሚሹት ነው። ይህ ስንፍና ተአምር ካጣ በጠባይ ዋዘኛ ይሆናል ። በእምነትም ወደ አምልኮ ባዕድና ወደ ጥንቆላ እየሄደ ምትሐታዊ ሥራ በመሥራት ለማደናገር ይከጅላል ።
 ተአምራት ፈላጊ ሕዝብ የዘማ ጠባይ አለው /ማቴ. 18 ፥ 3/። ዘማነት የብዙ ነው ። የአምልኮ ዘማ አለ ። አንዱን አምላክ ትቶ ለፍጡር የሚንበረከክ ። የእውቀት ዘማም አለ ። በአንድ እውቀት የማይረጋ ሁሉን ልወቅ የሚል ። የፍቅር ዘማ አለ ፥ በወረት ሁሉን ሰው የሚያዳርስ ። ተአምር ፈላጊ ሕዝብም እንዲሁ እንደ ሰፈር ምጣድ ሲነቀልና ሲተከል የሚኖር ነው ። ስንት ዓመት ያጽናናውን ቄስ ትቶ ዛሬ የመጣውን ተአምረኛ የሚከተል ፥ ንብረቱንና ትዳር የሚሰጥ ብዙ ወገን ተሸክመናል ። ለቋሚው አገልጋይ ሳይሆን ለመንገደኛው ስፖንሰር የሚሆን ብዙ ምእመናን ይዘናል ። ከሚያበላው የሚበላውን የሚመርጥ ሕዝብ አትርፈናል ። ተአምር አድራጊ ነን የሚሉ የበጎችን ጸጉር የሚሸልቱ ሳይሆኑ ጸጉሩን ጨርሰው ቆዳውን የሚገሸልጡ ናቸው ። ሕዝባችንም የሚወደው እነዚህን ነው ። እንዴት ዝቅ ብለው የሚያገለግሉንን ረግጠን እንሄዳለን ? የሚያዋርዱንንና በስማችን ለመጥራት እንኳ የሚጠየፉንን እንመርጣለን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም