የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፋሲካ በዓል

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቃና ዘገሊላው ተአምር ቀጥሎ በዋናነት የሚናገረው ጌታችን በቤተ መቅደስ ያሉትን ሻጮችና ነጋዴዎች ማስወጣቱን ነው ። ጌታችን የቤተ መቅደሱን ሻጮችና ለዋጮች ለሁለት ጊዜ ያህል እንዳስወጣ የሚነግረን ዮሐንስ ብቻ ነው። ሌሎቹ ወንጌላውያን ሁለተኛውን ሲዘግቡ ዮሐንስ ግን የመጀመሪያውን ይዘግብልናል። ይህን የምንረዳው በምንድነው ? ስንል ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጹሞና ጸልዮ በመጣ በሦስተኛው ቀን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ተገኝቷል ። ጌታችን የተጠመቀው ጥር አሥራ አንድ ቀን ነው ። ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ለጽሞና ሄዷል ። በዚያም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከቆየ በኋላ ተመልሷል። የተመለሰው የካቲት 21 ቀን 30 ዓ.ም. ነው። በሦስተኛው ቀን ማለት የካቲት 24 ቀን 30 ዓ.ም በገሊላ ቃና ሠርግ ላይ ተገኝቷል።
ወንጌላዊው ፡- ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” ይላል /ዮሐ. 2፥12-13/። ከቃና ዘገሊላው ተአምር በኋላ ለጥቂት ቀናት የቆዩት እስከ በዓለ ፋሲካ ነው። ይህ ማለት ፋሲካ ሚያዝያ 14 ቀን ነውና ለአንድ ወር ከ20 ቀን ያህል መቆየታቸውን እንረዳለን። ስለዚህ የገሊላ ቃና ተአምር ወደ ፊቱ የፋሲካ በዓል ስለነበረ ጌታችን ደግሞ ነጋዴዎችንና ሻጮችን ያወጣው በዚሁ ፋሲካ ስለሆነ ሁለት ጊዜ ያህል ቤተ መቅደሱን ከሻጮችና ከለዋጮች እንዳጸዳ እንረዳለን። ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳው በአገልግሎቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ነው። የአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ የሆሳዕና ምስጋና የለም። የመጨረሻው ላይ ግን በንጉሥ ወግ ስለገባ ሆሳዕና የሚል ዝማሬ ተሰምቷል።
ጌታችን በሁለተኛው የመቅደስ ጽዳቱ ከሕጻናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ተቀብሏል። በታላቅ ቊጣም ነጋዴዎችን ከመቅደሱ አስወጥቷል።በሁለተኛው ጽዳቱ የተቆጣው አስቀድሞ ከሦስት ዓመት በፊት ያጸዳው ስህተት እንደ ገና በመደገሙ ነው ። ጌታችን የቃና ዘገሊላን ታላቅ ተአምር ካደረገ በኋላ ወዲያው መቅደሱን አጸዳ ። ሆሳዕና በሚል ምስጋናም በንጉሥ መዐርግ ከገባ በኋላም መቅደሱን አጸዳ ። በአገልግሎቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ መቅደሱን ማጽዳቱ ቅድስና የሁልጊዜ ፍላጎቱ እንደሆነ ያሳያል ። ከታላቅ ተአምርና ምስጋና በኋላም ወደ ተግሣጽ መግባቱ በተአምራትና በምስጋና አለመዘናጋቱን ያስረዳል ። በሁለቱም ጽዳቱ የአባቴ ቤት በማለት አምላካዊ ክብሩንና የመቅደሱን ባለቤት ጠቊሟል። አምላክነቱን ቢረዱ ፈጥነው ንስሐ ይገቡ ነበር ። የእግዚአብሔር ቤት መሆኑን ቢያስቡም እንዲህ አይደፍሩም ነበር።
ጌታችን ከአራት ፋሲካ በኋላ ስለ ሰው ልጆች በመሞት እውነተኛው ፋሲካ ሆኗል ። ወንጌላዊው ዮሐንስ ሦስት ፋሲካዎችን እንዳከበረ ጽፎልናል። ወንጌላዊው ያሰፈረው የፋሲካ በዓላት፡-
1-  የመጀመሪያው ፋሲካ በ30 ዓመቱ ያከበረው /ዮሐ. 2፥13/።
2-  ሁለተኛው ፋሲካ በ31 ዓመቱ ያከበረው /ዮሐ. 6፥4/።
3-  ሦስተኛው ፋሲካ በ32 ዓመቱ ያከበረው ቢሆንም ዮሐንስ አልዘገበውም።
4-  አራተኛው ፋሲካ በ33 ዓመቱ ያከበረው ነው /ዮሐ. 12፥1/።
የፋሲካ በዓላት ጌታችን በስንት ዓመቱ እንደ ሞተ ይገልጡልናል ። ጌታችን የተወለደው ታኅሣሥ 29 ቀን ስለሆነ የሞተው ደግሞ በአራተኛው ፋሲካ ሚያዝያ ወር ላይ ነውና በዚህ ምድር ላይ የቆየው 33 ዓመት ከ3 ወር እንደሆነ እንረዳለን።
ቃና ዘገሊላ የመጀመሪያው ተአምር ያደረገበት ደቀ መዛሙርቱም ያመኑበት ትልቅ ቀን ነው። በአገራችን ቃና ዘገሊላ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። የሚከበርበት ቀን ግን ጥር 12 ነው ። ተአምራቱ የተፈጸመው ደግሞ የካቲት 24 ነው። ይህ ለምን ሆነ ስንል? በሦስት ምክንያቶች ነው ፡-
1-  የካቲት 24 ብዙ ጊዜ ዐቢይ ጾም ላይ ስለሚውል የደስታ በዓልን በጾም ላለማክበር ነው።
2-  ጥምቀት የውኃ በዓል ሲሆን የቃና ዘገሊላም በዓል ውኃው ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠበት በመሆኑ የውኃ በዓልን ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ነው።
3-  በአገራችን መኸሩ የሚከተትበት ደስታና የሰርግ ወራት ጥር በመሆኑ ጌታችን ሰርግ ቤቱን የባረከበት የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 እንዲውል ተደርጓል።
 እንደ አካሄዱ ከሆነ ዐቢይ ጾም መግባት የነበረበት ጥር 11 ቀን ነው። ዐቢይ ጾም ግን ፍጻሜው ፋሲካ እንዲሆን ስለተፈለገ ፍችው ሚያዝያና መጋቢት መጨረሻ ላይ ይደረጋል ። ብዙ ጊዜም የአይሁድን ፋሲካ ይከተላል። ለምን ስንል በኦሪት ፋሲካ ላይ አዲሱ ፋሲካ መንገሡን ለማስታወስ ነው።
በአይሁዳውያን ባሕል ሰርግ የሚደረገው ማክሰኞ ቀን ነው ። ስለዚህ ጌታችን እሑድ ከገዳመ ቆሮንቶስ ተመልሶ ከዮሐንስ ጋር ከተገናኘ በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ። ከዚህ የአይሁዳውያን ባሕል በመነሣት በአገራችንም ሰርግ ማክሰኞና ሐሙስ ይውል ነበር። ዓላማው የጌታችን ቀን የሆነችውን ሰንበትን ላለመንካት ነው። አሁን ግን ይህ እየቀረ መጥቷል ። አንዳንድ አባቶችም ጋብቻ ክብሩን ያጣው የጌታን ቀን በመንካቱ ነው እያሉ ሲያስተምሩ በልጅነቴ ሰምቻለሁ ። ጌታችን በገሊላ ቃና ሰርግ እንዳለ ያወቀው ከዐርባ ቀን በፊት ቢሆንም ከዐርባ ቀን በኋላ ሳይረሳ ወደ ሰርጉ ሄዷል ። እርሱ አይረሳም ። ጥሪንም ያከብራል ። ወደ ገሊላ ቃና ሰርግ ሲሄድም የአገሩን ሰው ናትናኤልን ይዞ ነው ። ትልቁ ሰርግ ግን የናትናኤል መዳን ነበር።
የቃና ዘገሊላው ሰርግ የቤተሰብ ሰርግ ነበረ ። ምክንያቱም ከናዝሬት ወደ ቃና መጥታ እናቱ የተገኘችው የቤተሰብ ሰርግ በመሆኑ ነው። ከከተማ ከተማ የሚኬደው የቤተሰብ ሰርግ ሲሆን ነው ። ዳግመኛም ፡- “የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች” ይላልና በእድምተኛነት ከመምጣት እዚያ ስታግዝ ቆይታለች /ዮሐ. 2፥1/። ጌታችን ግን በቀጥታ ከዮርዳኖስ ወደ ገሊላ ቃና ደቀ መዛሙርቱን ይዞ መጥቷል ።

እኛም እንጥራው ሳይረሳ ሳይንቅ ይመጣል ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ