የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

… የውኃ በዓል

/ካለፈው የቀጠለ/
የዮሐንስ ወንጌል ስለ ውኃ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ይናገራል ። ውኃ የእግዚአብሔር ስጦታን ፥ ጥልቅ ስሜትን ፥ ፍሬያማ ሕይወትን ያመለክታል ። ባለፈው ጽሑፋችን ዘጠኙን ለማየት ሞክረናል ። በዛሬውም መልእክታችን የቀሩትን የውኃ ትንታኔዎች እናያለን ።
10- የኀዘን ውኃ ፡-
ጌታ በአልዓዛር ሞት ላይ መገኘቱ ልቅሶ ሊደርስ መስሎአቸዋል ። እርሱ ግን ልቅሶን ይሽራል እንጂ ልቅሶን አይደርስም ። የአልዓዛር እህቶች መታመሙን ወደ ጌታ ልከው ነበር ። እስካሁን ያለው እምነታቸው ጌታ የታመመን እንደሚፈውስ ነው ። ጌታችን ግን የበለጠውን ሊያሳያቸው ዘገየ ። እርሱ ሙት አንሣ ነው ። አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆነው ። ዕለቱን ቢመጣና ቢያስነሣው ኖሮ ደንግጠን ጮህን እንጂ ሙቀቱ አልበረደም ነበር ይባል ነበር ። ጌታ ግን አስተዛዛኝ ሁሉ ከተበተነ በኋላ በአራተኛው ቀን መጣ ። ሰው ሲጨርስ እርሱ ይጀምራል ። አስተዛዛኝ ሲበተን እርሱ ይመጣል ። ጌታችን በመጣ ጊዜ የአልዓዛር እህቶች እንባቸውን ማፍሰስ ጀመሩ ። ጌታም ሩኅሩኅ ነውና እንደሚያስነሣው እያወቀ እንኳ አለቀሰ ። በሕይወቱ እንደ ሳቀ አልተጻፈም ። ሁለት ጊዜ ግን እንዳለቀሰ ተጽፏል ። የመጀመሪያው በአልዓዛር መቃብር ላይ ያፈሰሰው እንባ ነው ። ሁለተኛው ኢየሩሳሌምን ባየ ጊዜ የጥፋቷን ዘመን ተመልክቶ ያለቀሰው ልቅሶ ነው /ሉቃ. 19፥41/። ወንጌላዊው ስለዚህ ጥልቅ ውኃ ዘግቦልናል /ዮሐ. 11፥35/ ።
11- የሽቱ ውኃ ፡-
አልዓዛር ከሞት ከተነሣ በኋላ የጌታችን የሞት ጊዜ እየተፋጠነ መጣ። ሌሎች ሲነሡ የአገልጋዮች ሞት ግን እየተፋጠነ ይመጣል ። የአልዓዛር እህት ማርያም ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባችው ። የወሰደችው ሽቱ እጅግ ውድ ሲሆን ለአንገት እንኳ የሚሰስቱለት ነው ። ለጌታ ግን ለእግሩም አይበቃም ነበር ። እግሩ ላይ ካፈሰሰች በኋላ እንደገና አነሰባትና በጠጉሯ አበሰችው ። በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛውን ስጦታ አመጣች ። አይሁድ ሰው ከሞተ በኋላ መቃብሩ ላይ ሽቱ ይቀባሉ ። የተከበሩ ሴቶችም ጌታን ሊቀቡ ወደ መቃብሩ ገስግሰዋል /ማር. 16፥1/ ። እርሱ ግን እኩለ ሌሊት ተነሥቶ ስለነበር አላገኙትም ። እርሱ ለሙት የሚገባን ስጦታ ሳይቀበል ተነሣ ። ሕያው ነውና የማርያምን ሽቱ በሕያውነት ተቀበለ /ዮሐ. 12፥1-8/ ።
ሽቱ ያላቸው ብዙዎች ናቸው ። ብዙዎቹ ይህን ሽቱ የሚያስታውሱት ወዳጃቸው የሞተ ቀን ነው ። በሕይወቱ ሊቀቡት አልቻሉም ። ጊዜ ያልፍና አዝነው ይቀራሉ ። በቁም ማጽናናት ፥ በቁም መረዳዳት የማርያም ሽቱ ነው ።
12- የእግር ውኃ ፡-
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን እራት ከበሉ በኋላ የደቀ መዛሙርቱን እግር ለማጠብ ከማዕድ ተነሣ ። እግር ማጠብ በእስራኤል ልማድ የባሪያ ተግባር ነው ። ባሪያውም እግር ለማጠብ ስለሚጸየፍ ቀድሞ እራቱን ይበላ ነበር ። ባጠበ እጁ ላለመብላት ይጠነቀቃል ። እራቱን ሳይበላ ማጠብ ግድ ከሆነበት ግን ጦሙን ማደር ይመርጣል ። ጌታችን እግር ያጠበው ከማዕድ ተነሥቶ ሲሆን ካጠበ በኋላ ግን ወደ ማዕዱ ተመልሷል /ዮሐ. 13፥1-11/ ። ባሪያ እግር ቢያጥብ የጌታውን ነው ። ጌታችን ግን እግር ያጠበው የደቀ መዛሙርቱን ነው ። ታላቅ ትሕትናን ገለጠ ። ጴጥሮስ አታጥበኝም ብሎ ነበር ። ጌታ ግን ግድ መሆኑን ሲነግረው እጄንና ራሴንም እጠበኝ አለው ። እጁ ስቶ የማልኮስን ጆሮ ይቆርጣልና ራሱም ሰንፎ አላውቀውም ይላልና ይህን ለመነ ። ጌታችን ግን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ ሌላ አያስፈልገውም አለ ። እግርን መታጠብ በዓላማ መጽናት ነው ። ጴጥሮስን እንደገና የመለሰው ያቀረበው ልመናና የታጠበው መታጠብ ነው ። የካቶሊኩ ፖፕ ፍራንሲስ በ2016 እ.አ.አ በፋሲካ በዓል ዋዜማ የስደተኞችን እግር ሲያጥቡ ታይተዋል ። ሲያጥቡ አንዷ ኢትዮጵያዊት ነበረች ። ስቅስቅ ብላ ስታለቅስ ለመመልከት ችለናል ። በሚበልጡን መታጠብ ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል ። ደቀ መዛሙርቱ በሰማይና በምድር ጌታ እጅ ሲታጠቡ ምን ተሰምቶአቸው ይሆን ? ወንጌላዊው ስለ ውኃ መዘገብ ይወዳልና ይኸው ስለ እግር ውኃ ጻፈልን ።
ዛሬም እጃችን ከመስጠት መንጠቅ ፥ ከማንሣት መጣል ለምዶ ይሆን ? የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ተቆልፎ ይሆን ? ራሴን የምንልበት ሕመም አለን ? መወላወል ፥ መፍራት ፥ ከስፍራ መናወጥ ገጥሞን ይሆን ? እንደ ጴጥሮስ እንለምን ። እጄንም ራሴንም እጠበኝ እንበለው ። ጌታ ግን የችግሩን ምንጭ እግራችንን ያጥባል ። ቶሎ ከሚቆሽሹ የሰውነት ክፍሎቻችን አንዱ እጃችን ቢሆንም እግራችን ግን ብዙ ቆሻሻዎችን ይዞ ይመጣል ። እግርን መታጠብ ሁለንተናን እንደ መታጠብ ነው ። የደከመ ሰውም እግሩን ሲታጠብ ሁለንተናው ይበረታል ። እንቅልፍ የሚያስቸግራቸው ተማሪዎችም እግራቸውን ውኃ ውስጥ ሲያደርጉት ነቅተው ማጥናት ይችላሉ ። ታማሚዎች እግራቸውን ሲታሹ የውስጥ ሕመማቸው ሳይቀር መወገድ ይጀምራል ። የሰው ሁለንተና እግሩ ላይ አለ ። እግራችንን መታጠብ በዓላማችን መጽናትን ያመለክታል ። በዓላማችን ከጸናን ሌሎች ነገሮች ቀላል ናቸው ።
እግዚአብሔር ያግዘን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ