መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት የሚያስተምር ብቻ ሳይሆን አስደናቂ ጸሎቶችን የያዘም መዝገበ ጸሎት ነው ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃና ጸሎት ተጠቃሽ ነው ። እንዲሁም ያቤጽ የጸለየው ጸሎት አጭር ነው ፥ ግን ተወዳጅ ጸሎት ነው ። የያቤጽ ጸሎት ፡- “እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው” ይላል /1ነገሥ. 4፥10/ ። ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም የተሰኘውም ድንቅ ጸሎት ሲሆን የቃና ዘገሊላው ጸሎት ግን አጭር ሲሆን በውስጡ ብዙ ፍቺዎችን ይዟል ። “የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ፡- የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ዮሐ. 2፥3/ ። ይህ የድንግል ጸሎት ፥ ስለ ጸሎት ምንነት የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው ። የጸሎትን መርሖች የምናገኝበት ምሥጢር ነው ። ጸሎቱ የቀረበው በታላቅ እምነትና አክብሮት ነው ። በዚህ አጭር ጸሎት ውስጥ 17 የሚጠጉ የጸሎት መርሖችን ማግኘት እንችላለን ። ጸሎት ምንድነው ? ለሚል ጠያቂ ፡-
1- ትክክለኛውን ጥያቄ ለትክክለኛው መላሽ ማቅረብ ነው
እመቤታችን ድንግል ማርያም ያቀረበችው ልመና አስደናቂ ነው ። ጥያቄዋ የሚያራራ ነው ። ትክክለኛውን ጥያቄዋን ለትክክለኛው አምላክ አቀረበች ። ጸሎቱ ትክክል ነው ወይ ? ለማለት መመዘኛዎች አሉት ። ችግሩ በትክክል አለ ወይ ? የሚለው የመጀመሪያው ነው ። እመቤታችን ትክክለኛ ልመና አቀረበች ። ችግሩ በትክክል ነበረ ። ሰዎች ራበኝ ሳይሆን ሊርበኝ ነው የሚል ጸሎት ያቀርባሉ ። ሰዎች ጭንቀታቸውና ጭንቀታቸውን የሚያቀርቡበት ስፍራ ትክክል ላይሆን ይችላል ። ከእነርሱ የበለጠ ተጨናቂ ለሆኑ ሰዎች ሊናገሩ ይችላሉ ። እነኛን ሰዎች ማባበል ይተርፋቸዋል ። ወይም ችግራቸውን በአጉሊ መነጽር እያሳዩ መልሰው ያስጨንቋቸዋል ። አሊያም የነገሩአቸውን ችግር የሐሜት ማጣፈጫ ያደርጉታል ። አንዳንዴም ሊታዘቡ ይችላሉ ። እውነተኛው የጸሎት አድራሻ መድኃኔዓለም ነው ። ነቢዩ ፡- “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል” ይላል /መዝ. 64፥2/ ። ጸሎትን የማይሰሙ የአሕዛብ አማልክት ፥ ጣዖታት አሉ ። እግዚአብሔር ግን ሰምቶ የሚመልስ ነው ። ጸሎት ማለት በነፍስ ወደ እግዚአብሔር መገስገስ ነው ። በነፍስ ሩጫ ወደ እግዚአብሔር እቅፍ መግባት ነው ። እመቤታችን ትክክለኛውን ጸሎት ለትክክለኛው መላሽ አቀረበች።
2- ጸሎት ፍጹም መረጋጋት ያለበት ነው
ሕጻን ልጅ አጥፍቶ ሲያባርሩት አንዳንዴም ያለ ጥፋቱ ሲያሳድዱት የሚሮጠው ወደ አባቱ እቅፍ ነው ። ወደ አባቱ እቅፍ ከገባ በኋላ ግን ውጊያው የእርሱ ሳይሆን የአባቱ ነውና የሚደልቅ ልቡን ለማብረድ ብቻ ያስባል ። ጸሎትም በኃጢአትም በጽድቅም ሲያሳድዱን የእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ መግባት ነው ። ከጸለይን በኋላ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው ። ለመንግሥት ካሳወቅን በኋላ መንግሥት ጠላቶቻችንን እንደሚከታተል እግዚአብሔርም መንግሥት ነውና የሚያሳድዱንን ያሳድዳል ። ከጸለይን በኋላ ስሜታችን ከመጸለያችን በፊት እንዳለው ሊሆን አይገባውም ። በመጸለይና ባለመጸለይ መካከል ልዩነት መኖር አለበት ። ጸሎት መለወጥ ነው ። መጀመሪያ እኛ ፥ ቀጥሎ ጉዳዩ የሚለወጥበት ነው ። የሚጨነቀው ከጸለየ በኋላ ያርፋል ። መፈጸም አለመፈጸሙ ሁለተኛ ሂደት ሲሆን የመጀመሪያው መደመጥ ነው ። እግዚአብሔር ሰምቶናል ። በሕግ አግባብ መጀመሪያ የጥፋተኝነት ውሳኔ ይወሰናል ፥ ሁለተኛ የቅጣት ውሳኔ ይወሰናል ። እንዲሁም በጸሎት አግባብ መጀመሪያ እንደመጣለን ፥ ቀጥሎ ይፈጸማል ። በመደመጣችን ደስ ሊለን ይገባል ። የአገር መሪ ጊዜ ሰጥቶ ቢሰማን ባይፈጽምልን እንኳ ደስታችን ትልቅ ነው ። እግዚአብሔርም ባይፈጽምልን እንኳ አክብሮ አፍቅሮ ስለሰማን ደስ ሊለን ይገባል ። በዚህ ዓለም ላይ ጆሮን የተነፈግን ነን ፥ የቅርብ ሰዎች ሳይቀር ጆሮ የነፈጉን ሰዎች ነን ። ጌታችን ግን ይሰማናል ። ስለዚህ ጸሎታችን ፍጹም መረጋጋት ያለበት ሊሆን ይገባዋል ። የጸሎት መምህርት የሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም በፍጹም እርጋታ ፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” አለችው ። ለእኛ ትልቅ ትምህርት አለው ። ከልመናችን ፥ ከሥነ ሥርዓታችን ጀምሮ መረጋጋት ያስፈልገናል ።
ነቢይት ሃና እስክትጸልይ በብዙ አነባች ። ከጸለየች በኋላ ግን ዳግመኛ ፊቷ ኀዘነተኛ መስሎ አልታየም /1ሳሙ. 1፥18/ ። ውጤቱም ነቢዩን ሳሙኤልን መታቀፍ ሆነ ። የጸሎቷ መልስ ለአገር የሚተርፍ መፍትሔ ሆነ። እስክንጸልይ ልናዝን እንችላለን ። ከጸለይን በኋላ ግን ፍጹም ማረፍ ይገባናል። እግዚአብሔር ድምፁን የሚያሰማን በእርጋታ ውስጥ ነውና ። በልብ ዕረፍት ውስጥ መሆን የጸሎትን መልስ ለመቀበል ይረዳል ።
3- የክርስቶስን ሁሉን ቻይነት ያመነ ነው
እመቤታችን ያለቀውን ነገር መቀጠል ይችላል ብላ ነው ልመናዋን ያቀረበችው ። ሀብት የሚመልሰው ፥ እውቀት የሚመልሰው ሳይሆን አምላክነቱ የሚመልሰው ጥያቄ ነበር ። ስለዚህ ያመነችው በአምላክነቱ ነው ። ጸልየን ማመን ሳይሆን አምነን መጸለይ ትልቅ ዋጋ አለው ። እግዚአብሔር ሊሰማኝ ፈቃድ ፥ ሊፈጽምልኝ ኃይል አለው ብለን ማመን ይገባናል ። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ፥ ሁሉን ባንችል እንኳ ሁሉን የሚችል አምላክ አለን ። ሁሉን ቻይ ነው ስንል በጊዜ፥ በቦታና በሁኔታ አይወሰንም ማለታችን ነው ። ጸሎት በጊዜ፥ በቦታና በሁኔታ የተወሰንነው እኛ ብርቱ የምንሆንበት ምሥጢር ነው ። በማንደርስበት የምድር ዳርቻ ፥ በተቆለፈ እስር ቤት ላይ የእግዚአብሔርን እጅ መዘርጋት ነው ። ውስኑ ሰው ምሉዕ በኩለሄ የሚሆነው በጸሎት ነው ። አሁን በአቅማችን ልንረዳቸው የማንችላቸው ሩቅ አገር ፥ ወይም እስር ላይ ያሉ ወገኖች ቢኖሩ በጸሎት ግን መርዳት እንችላለን ። በእውነት በጸሎት ልናገኘው የሚገባንን ከመቶ አንዱን እጅ አላገኘንም ። የእመቤታችን ጸሎት ግን ሁሉን ቻይነቱን ያመነ ነው ።