9- የሚለንን ካደረግን የምንለው ይሆናል
በጸሎት ውስጥ ሊታሰቡ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነው ። እመቤታችን ፡- “የሚላችሁን አድርጉ” ማለቷ ካላደረጉ ፍላጎታቸው አይሞላም ማለት ነው ። የሚላቸው ደግሞ ውኃ ሙሉ ነው ። “እንዴት ወይን ጠጅ አልቆ ውኃ ሙሉ ይለናል ? ይህ የልጅ ሥራ አይሆንም ወይ ?” አላሉም ። እርሱ ያዘዘንን ስናደርግ እኛም የለመነው ይደረጋል ። የለመንኩትን አልሰማኝም እያልን ብዙ ጊዜ እናጉረመርማለን ። ብዙ የጸሎት አኩራፊዎችም እንኖራለን ። እኛስ እርሱ ያለንን ፈጽመናል ወይ? የበዳይ አኩራፊ እንዳንሆን ማሰብ ይገባናል ። ሊቀየም የሚገባው ሳይቀየም እኛ ተቀያሚ መሆናችን ይገርማል ። እመቤታችን የሰጠችው መመሪያ የሚላችሁን አድርጉ የሚል ነው ።
መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የተለያዩ መርጃዎች መዝገበ ቃላት ፥ የትርጓሜ መጻሕፍት ፥ መምህራን አስፈላጊ ናቸው ። ትልቁ መፍቻ ግን መታዘዝ ነው ። ምክንያቱም ቃሉ የተሰጠው ለመታዘዝ ስለሆነ ስንታዘዝ የበለጠ እየገባን ይመጣል ። እንዲሁም የለመንነው እንዲሆን ያዘዘንን ማድረግ ቁልፍ ነው ። “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል” ይላል /ዮሐ. 15፥7/ ። በነቢዩ በኢሳይያስም ፡- “የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፥ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ” ይላል /ኢሳ. 45፥11/። ምልጃ ስለ ልጆቹና ስለ እጁ ሥራዎች መለመን ነው ። አዎ ያለንን ስናደርግ ያልነውን ያደርጋል ። ኤልያስ ሰማይን የለጎመው ፥ የተለጎመውንም የፈታው ከእግዚአብሔር ጋር በመስማማት ደግሞም ለአምልኮቱ በመቅናት ነው ። እግዚአብሔር ዛሬም ሕያው ነው ፥ ይሠራል ። ብቻ የሚለንን እናድርግ ። ሞኝነት ለሚመስለው ለእርሱ ነገር እንታዘዝ ። ያለቀውን ይቀጥላል ። ውኃውን ወይን አድርጎ ይለውጣል ።
10- የልብ አምልኮ እንጂ የታይታ ግርግር የለበትም
እመቤታችን ስትጸልይም ሆነ ሲመለስላት ተረጋግታ ትታያለች ። ፎክራ ወደ ልጇ አልመጣችም ፥ እዩት ልጄን ከሠላሳ ዓመት በፊት መልአኩ የነገረኝ ይኸው ተፈጸመ አላለችም ። በእርሷ ላይ ምንጊዜም የሚታየው የሴትነት ወይም የእናትነት ወይም የእስራኤላዊነት ጠባይ ሳይሆን የአማኝ ጠባይ ነው ። እኛ የጸሎት መልሶቻችንን ለማብሸቅ እንጠቀምበታለን ። አንዳንዴ ዝማሬው አሽሙር ነው ። በጌታ የጦር ዕቃ ለራሳችን እንዋጋለን ። የጸሎታችን መልስ ግን ሌሎችን የምናሳንስበት ፥ የራሳችንን ብቃት የምናሳይበት መሆን የለበትም ። ይህን መርሕ የምናገኘው ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ነው ።
11- የጌታን ክብር መገለጥ የሚናፍቅ ነው
እመቤታችን ድንግል ማርያምን ያሳሰባት ታዳሚው ስለሚለው ሳይሆን ስለ ሰርገኞቹ ጭንቀት ነው ። እውነተኛ ችግረኞችን ለይታ አውቃለች ። ወረኞች ችግረኞች ሳይሆኑ ችግር ፈጥረው የሚያውኩ ናቸው ። የታወኩ እየመሰሉም ሌላውን በእውነት የሚያውኩ ፥ አእምሮን የሚያቆሽሹ ፥ ሌላውን በማራከስ የበታችነት ስሜታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚሞክሩ ናቸው።የእመቤታችን የልመናዋ ግብ የሰርገኞቹ ልቆ መታየት ሳይሆን የልጇ ክብር መገለጥ ነው ። ጸሎት እውነተኛውን ችግር ለይቶ ማወቅ አለበት ። ግቡም የእግዚአብሔር ክብር ብቻ ሊሆን ይገባዋል ።
12- የጸሎቱ መልስ ክብሩ ለመላሹ ነው
የእኔ ጸሎት ጠብ አትልም የምንልበት ሳይሆን ምስጋናውን ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት ነው ። ምክንያቱም ጸሎት የጸጋ መንገድ እንጂ የጥረት መንገድ አይደለምና ። ጸሎት የእግዚአብሔር ቸርነት የሚታሰብበትና የሚታወጅበት ነው ። ጸጋው የሚፈስስበት አንዱ ቦይ ነው ።
13- ጸሎት ስለሌሎች መማለድ ያለበት ነው
እመቤታችን የማለደችው ሳይነግሯት ነው ። ጓዳውን ዘልቃ አይታ ፥ ጭንቀታቸውን ከገጽታቸው አንብባ ፥ ለማንም ሳይነግሩ የሚተራመሱትን ትርምስ ተገንዝባ በስውር ለልጇ ነገረችው ። እርሱም በአደባባይ መለሰ ። ምልጃ የጸሎት አንዱ ክፍል ነው ። ስለ ሌሎች መጸለይ ያለብን ሳይነግሩን ሁኔታቸውን ፥ አረማመዳቸውን ፥ ስሜታቸውን ተገንዝበን ሊሆን ይገባዋል ። ምልጃ ፍቅር ነው ። ራስን በሌሎች ጉዳት ላይ አስቀምጦ ማየት ነው ።
14- ብዙ ቃላት ሳይሆን ብዙ ፍቅር ነው
“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ብዙ ቃላት አይደለም ። ግን ብዙ ሥራ የሠራ ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ ሰዓት በጸሎት መነጋገር የኅብረት መገለጫ ነው ። ጸሎታችን ግን የሚሰማው በእምነት ስንናገር ነው ። በእግዚአብሔር ፊት መልስ የሚያገኘው ልባችን የወደቀበት ጸሎት እንደሆነ አባቶች ያስተምራሉ ። በአንደበታችንም የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ ክፉ አጋንንት ይርቃሉና አፍ ከልብ አልሆንኩም ብለን ጸሎት ማቆም የለብንም ። ስረጋጋ እጸልያለሁ ማለትም ሞኝነት ነው ፥ የሚያረጋጋው ጸሎት ነውና ።
ፈሪሳውያን አንድን ነገር በመደጋገም ብዛት የሚሰሙ ይመስላቸው ነበር። ሳይታክቱ መጸለይ እምነት ሲሆን በመደጋገም ብዛት እሰማለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ። ጌታችን ፡- “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ” ብሏል /ማቴ. 6፥7/። ጌታ ለአሕዛዝ እምነትና ጣዖታት እውቅና እየሰጠ ነው ያለው ? አሕዛብ የማያምኑ ማለት ነው ። ስለዚህ ፈሪሳውያንን በግብራቸው አሕዛብ እያለ እየጠራ ነው ። መድገም ማለት መጽሐፍ ማንበብ ማለት አይደለም ። ልብ የሸፈተበት ፥ እምነት የራቀበት ጸሎት በቃልም ቢሆን መድገም ነው ።
15- በእግዚአብሔር ጊዜ የሚመለስ ነው
ጌታችን ለተወዳጅ እናቱ ፡- “ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ዮሐ. 2፥4/። ይህ የሚያሳየን ጸሎት በእግዚአብሔር ጊዜ የሚመለስ መሆኑን ነው ። ጸሎት ሦስት ዓይነት መልሶች አሉት ፡-
– ለምን ይሰጥሃል
– ጠብቅ ታገኛለህ
– አይሰጥህም አይጠቅምህም
በዚህ መሠረት ጸሎት መቀበል ፥ መታገሥ ፥ ሲከለክለን ማመስገን ያለበት ነው ። እግዚአብሔርን ከለመንን በኋላ መታገሥ የሚያስፈልገን ሥራን የሚሠራው በራሱ ጊዜ ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር የሚዘገየው ጉዳዩን ሲያበስል አሊያም እኛን ሲያበስል ነው ። የእመቤታችን ጸሎት በትዕግሥት መጠበቅን ያስተምረናል ።
16- ለሌሎች እምነት ሊሆን ይችላል
በእመቤታችን ጸሎት በተደረገው ተአምራት ደቀ መዛሙርቱ አምነዋል። በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ አምላክነቱን ያመነች እናቱ ብቻ ነበረች። አንዱ አሳቧም ክብሩን ዓለም እንዲያውቀው ነው ። በገለጠችው ቊጥር መስቀሉ ይፋጠናል ። ነገር ግን ክብሩ መሰወሩ እጅግ አሳስቧታል ። በዚህም ደቀ መዛሙርቱ አምነዋል ። ከቃና ሰርገኞች ይልቅ የደቀ መዛሙርቱ ማመን ተጽፎአል ። የተደረገላቸው ላያምኑ ይችሉ ይሆናል ። በዙሪያው ያሉት ግን እጃቸውን ለእምነት ይሰጣሉ ። በጸሎታችን ላይ በሚገለጠው የእግዚአብሔር ክብር ብዙዎች ሊያምኑ ይችላሉና ተግተን መጸለይ ይገባናል ።
17- ተአምራቶች ምልክት እንጂ ፍጻሜ አይደሉም
በጸሎታችን የሚገለጡት ተአምራቶች የበለጠ የነፍስ ዋጋ እንዳለ የሚያነቃቁ እንጂ ተአምሩ ላይ የሚያስቀሩ መሆን የለባቸውም /ዮሐ. 2፥11/። የቃና ሰርገኞች ከተአምሩ በኋላ የወይን ጠጁን ወደ መጠጣት ከማድላት ይልቅ በጌታችን ማንነት ላይ ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ ። እግዚአብሔር በመካከላቸው ምን እያደረገ እንዳለ መመራመር ይጀምራሉ ። ተአምራት ወደ ተአምር አድራጊው ካላመለከተን አደጋ ክልል ውስጥ ነን ። አሁንም እንጸልይ ብዙ ተአምራቶችን እናያለን ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ያለን ክብርና ፍቅር ማደግ አለበት። በእመቤታችን ጸሎት እነዚህ 17 የጸሎት መርሖችን እንማራለን ።