የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአርምሞ ትሩፋቶች

1- ድንግልናዊ ሕይወት
ድንግልናዊ ሕይወት ከአርምሞ ትሩፋቶች አንዱ ነው ። አርምሞ በፍቅር ከሚሰማው ፥ በረድኤት ከሚመልሰው አምላክ ጋር ጉዳይ መያዝ ነው። ደርባባ አቡን እንደሚባሉ ሰዎች ከበሬታን በመናፈቅ የሚደረግ ስልት ሳይሆን ሰማያዊውን ኃይል ለመለማመድ የሚደረግ ዝምታ ፥ ውጫዊ ሕዋሳትን ዘግቶ የውስጡን መክፈቻ ነው ። ድንግልናዊ ሕይወትም ከአርምሞ ጋር የተያያዘ ነው ። ሁለቱም ማለት ድንግልናዊ ሕይወትም ሆነ አርምሞ ተያያዥና ምርጫ ናቸው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም አርምሞዋ የድንግልናዊ ሕይወትዋ መግለጫ ነው ። የእመቤታችን ክብር ሲነገር ክብሯን የሚያጎላው የራሱ የእግዚአብሔር ወልድ ክብር ነው ። ነቢያት በትንቢታቸው ፥ ሐዋርያት በስብከታቸው ፥ ሰማዕታት በመሥዋዕትነታቸው ክብራቸው ቢነገር የድንግል ማርያም ግን ክብሯ ወላዲተ አምላክ መሆኗ ነው ። ይህ የማይደገም ጸጋ ሲሆን ወላዲተ አምላክ የምትባል ከእርስዋ በቀር ማንም ሴት የለችም ፥ አትኖርምም ። ብዙ ሴቶች ነገሥታትን ቢወልዱ እቴጌ ተብለው ተከብረዋል ። እመ አምላክ መባል ግን ትልቅ ክብር ነው ።
ጌታችን በሥጋ ሲገለጥ እናቱን እንደ መረጠ ፥ ድንግልናዊ ልደትን መወለድ እንዳቀደ እንረዳለን ። ይህ የሥጋዌው አንዱ መንገድና የሰው ልጆችም ክብር ነው ። ድንግል ማርያም የሰው ወገን ስለሆነችና በእርስዋ በኩል እግዚአብሔር ስለተዛመደን ፥ የዓለሙንም አዳኝ ሁሉን ወክላ በሥጋ እንግድነት በመቀበሏ ደስ ይለናል ። አብርሃም እግዚአብሔርን በቤቱ ማስተናገዱ በዘመናት ሲነገር ኑሯል /ዘፍ. 18/። የአብርሃም ልጅ ድንግል ማርያም ግን በማኅፀኗ ወልድን አስተናግዳለች ። እናትነትን ከድንግልና ጋር ያስተባበረች ወልዳም ድንግል የምትባል እርስዋ ብቻ ናት ። ጌታችን በድንግልና መወለድን ለምን ፈለገ?
1-  አባቱ አንድ ስለሆነ ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ እናት ፥ በምድር አባት የለውም ። አባቱ አንድ ነው ። ከድንግል ማርያም ሥጋን ሲነሣም ያው አንድ የአብ ልጅ ነው ። በአብ ልጅና በድንግል ማርያም ልጅ መካከል ልዩነት የለም ። መልአኩ ገብርኤል የምትጸንሰው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ተናግሯል ፥ ኤልሳቤጥም የጌታዬ እናት በማለት በድንግል ማኅፀን ያለው ጌታ መሆኑን መስክራለች ። እርሱ አንድ የአብ ልጅ ነው ። ሁለት አባት የለውም፥ አብም ሁለት ልጆች የሉትም ። እግዚአብሐር አብ ከድንግል የተወለደው በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ቆሞ ሳለ ሳይለይ ልጄ በማለት መስክሮለታል ። እምነታችን ወልድ ዋሕድ ነው ። አንድ ልጅ ብለን እናምናለን ። በዚህም ከንስጥሮስና ከኬልቄዶን ማኅበርተኞች እንለያለን ።
2-  ዳግማዊ አዳም ስለሆነ ፡- አዳም ከወንድ ዘር አልተገኘም ። አዳም የተገኘው ከድንግል መሬት ነው ። እንዲሁም ሁለተኛው አዳምና የፍጥረት አዳሽ ክርስቶስም ከድንግል ማርያም ተወልዷል ። አዳምን በአንጻራዊነት መምሰል ነበረበት ። አዳም ከመሬት ሲፈጠር መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሰጪ ነበር /ዘፍ. 2፥7/ ። እንዲሁም ጌታችን ሥጋን ሲለብስ በማኅፀነ ማርያም መንፈስ ቅዱስ ሥጋን በመክፈል ፥ በማክበር ፥ በማዋሐድ ዋነኛ ሠራተኛ ነበር ።
3-  ንጹሕ ስለሆነ ፡- የአዳም ኃጢአት ይተላለፍ የነበረው በወንድ ዘር በኩል ስለነበር ጌታችን ከአዳም ኃጢአት ጋር ላለመወለዱ ምስክር አንደኛው ድንግልናዊ ልደቱ ነው ። የአዳም ኃጢአት ቢነካው ኑሮ ቤዛችን ለመሆን ባልተቻለው ነበር ። ቤዛ ንጹሕ መሆን አለበትና ።
4-  ትንሣኤውን ስለሚያበስር ፡- በተዘጋ መቃብር እንደሚወጣ ቀድሞ ያበሰረው በተዘጋ ማኅፀን መወለዱ ነው ። መቃብር ክፈቱልኝ ፥ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል መነሣቱን የሚያምን በሕቱም ድንግልና መወለዱንም ያምናል ።
5-  እጅግ ክብርና ውርደት ስለሚገልጥ፡- በጌታችን ሥጋዌ ውስጥ ከፍ ያለ ክብርና ከፍ ያለ ውርደት ይታያል ። ሁለቱንም የምንቀበለው በእምነትና በፍቅር ብቻ ነው ። ከፍ ያለ ክብሩን የሚገልጠው አንዱ ድንግልናዊ ልደቱ ነው ። ምስኪንና የሕማም ሰው መሆኑ ደግሞ ስለ እኛ ሲል መዋረዱን ያሳያል ።
ድንግልናዊ ልደቱ የመጀመሪያውን ተስፋ ያስታውሳል ። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” /ዘፍ. 3፥15/ ። አባቶች ይህን ጥቅስ የመጀመሪያው ወንጌል በማለት ይጠሩታል ። በጥቅሱ ውስጥ በሴት በኩል ሞት እንደ መጣ ሕይወትም በሴት በኩል እንዲመጣ እግዚአብሔር ያደረገው የፍቅር ካሣ እንዳለ ያስረዳል ። ሁለተኛው የጌታችን ልደት ድንግልናዊ ማለት ከሴት ዘር ብቻ መሆኑን ያሳያል ። ሐዋርያው የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ሲናገር ፡- “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ብሏል /ገላ. 4፥4/። በዚያ ዘመን ፍልስፍና ለመውለድ ሴት የምታዋጣው ምንም ነገር የለም ። ሙሉ በሙሉ ድርሻው የወንድ ዘር ነው ። ሴት ግን ከረጢት ከመሆን አታልፍም የሚል አስተሳሰብ ነበር ። ስለዚህ የሴት ዘር የሚለው ቃል ፍልስፍናን የሚረታ ፥ እምነትን የሚጠይቅ ነው ።
በእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና ላይ የተቃውሞ አሳብ በማምጣት የሚታወቀው በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ሄሊቪዲየስ የተባለው ሰው ነው ። ይህ ሰው ድንግልናዊ ሕይወትን በጣም ይቃወም የነበረ ሲሆን ድንግል ማርያምም ጌታን ከወለደች በኋላ ሌሎች ልጆችን ወልዳለች የሚል ትምህርት አስተምሯል ። የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና ግን በዘመናት የተነሡ ሐዋርያነ አበው ፥ ሊቃውንትና ጳጳሳት የመሰከሩት ነው ። የጌታችን በድንግልና መፀነስና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ከመዳናችን ጋር የተያያዘ  ነው ። ዘላለማዊ ድንግልናን ቀለሜንጦስ ፥ አውሳብዮስ ፥ ቄርሎስ ፥ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ፥ አምብሮስ በየድርሳናቸው አስተምረዋል ። የፕሮቴስታት እምነት አብዮተኞችም ይህን አልካዱም ። ማርቲን ሉተር ፥ ካልቪን ፥የስዊስ ተሐድሶ ትምህርት መሪ ዝዊንግሊ ይህን አምነዋል ። እንደውም ካልቪን በስሟ አይጠራትም ዘላለማዊት ድንግል ይላታል ።
በድንግልና ኖራለች የሚል ቃል ሲነሣ የሚደነግጡ ሰዎች ምክንያታቸው እንደዚህ መኖር አይቻልም የሚል አእምሮ ስለያዙ ነው ። የዕብራውያንን ባሕል ስናጠና ግን ከታላቅ መገለጥ በኋላ ከሁሉም ነገር ርቆ መኖር ይታይባቸዋል ። ከሙሴ ጋር በደብረ ሲና ስለተሳተፉት ሰባ ሽማግሌዎች አንድ የአይሁድ ትውፊት “የእነዚህ ሚስቶች ወዮላቸው” ይላል ። በድንግል ማርያም ላይም የተደረገው መገለጥ ትልቅ ነው ። እንደዚያ ትውልድ ስናስበው ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም ። ዮሴፍም ከዚህ አመለካከት ውጭ አይደለም ።
የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና በሚመለከት የሚነሡት መከራከሪያዎች የጌታ ወንድሞች ተብለው የተጠቀሱት ሰዎች ጉዳይ ነው ። ያዕቆብና ዮሳ ፥ ስምዖንና ይሁዳ ወንድሞች ተብለዋል /ማቴ. 13፥55/ ። እነዚህ የዮሴፍ ልጆችና ዮሴፍ ከሟች ሚስቱ የወለዳቸው እንደሆኑ ኤጲፋንዮስ ሲናገር ይህንንም የግብፅ ፥ የሶሪያ ፥ የግሪክ አብያተ ክርስቲያናት ይቀበሉታል ። ይህ ግን የማይሆንበት ሁለት ምክንያቶችን ብንጠቅስ ፡-
1-  ከአራቱ ልጆች አንዱ ዮሳ የሚል ነው ። ዮሳ ማለት ዮሴፍ ማለት ነው ። ስለዚህ ዮሴፍ ልጁን ዮሴፍ ሊለው አይችልም ።
2-  የያዕቆብና የዮሳ እናት መስቀሉ ሥር ከተገኙት ሴቶች ተጠቅሳለች /ማቴ. 27፥56/ ። ከሞተች እንዴት በዚህ ሰዓት ልትጠቀስ ትችላለች?
 ይህን የኤጲፋንዮስን ትንታኔ ማለት ዮሴፍ ከሞተች ሚስቱ የወለዳቸው ልጆች ናቸው የሚለውን በአራት ነገሮች ተቀባይነት እንደሌለው ዘመናውያን የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ይጠቅሳሉ፡-
1-  ወደ ግብፅ በተደረገው ጉዞ እመቤታችን ፥ ዮሴፍና ሕጻኑ ኢየሱስ ብቻ ይጠቀሳሉ እንጂ ወንድሞቹ አይጠቀሱም ። በቀጥታ የሥጋ ልጆች ቢሆኑ አብረው ይሄዱ ነበር ።
2-  ጌታችን በ12 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ሲወጣ አሁንም የተጠቀሱት ሦስቱ ብቻ ናቸው ። ማንኛውም እስራኤላዊ የፋሲካን በዓል በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ማክበር ግዴታው ነው ። በቤተሰባዊ ጉዞም ወንድሞች የተባሉት አልተጠቀሱም ።
3-  በማቴዎስ አንድ ላይ ስለ ዮሴፍ የዘር ሐረግ ሲናገር ፡- “ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ” ይላል /ማቴ. 1፥16/ ። የዮሴፍ ወራሽ ቀጥሎ አይጠቀስም ። ከዮሴፍ ቀጥሎ የሚጠራው ጌታ ነው ። ዮሴፍ ከኢየሱስ በዕድሜ የሚበልጡ ልጆች ቢኖሩት ኖሮ ያሳደገው ጌታ እንደ ወራሽ ሆኖ አይጠቀስም ነበር ።
  4-  ወንድሞች የተባሉት በቀጥታ የኢየሱስ የሥጋ ወንድሞች ቢሆኑ ኖሮ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ለዮሐንስ አደራ አይሰጣትም ነበር ። የመጀመሪያም የመጨረሻም ልጇ ኢየሱስ ብቻ ስለነበር ነው በማለት ይጠቅሳሉ ።
ወንድሞች የሚለውን ትንታኔ ቅዱስ ጀሮም በአራት ያየዋል፡-
    1-  የሥጋ
    2-  የዜግነት
    3-  የቅርብ ዝምድና
    4-  የጓደኝነት ። ስለዚህ በጌታና ወንድሞች በተባሉት ዘንድ ያለው ግንኙነት የቅርብ ዝምድና ነው ። ቅዱስ ጀሮም አብርሃምና ሎጥን ያነሣል ። ሎጥ የአብርሃም የወንድሙ ልጅ ቢሆንም ወንድም ተብሏል /ዘፍ. 13፥8/ ። ቅዱስ ጀሮም የኢየሱስ ወንድሞች የተባሉት የቀለዮጳ ሚስት የማርያም ልጆች ናቸው ይላል /ዮሐ. 19፥25/ ። በርግጥም የጌታ ወንድሞች የተባሉት አንድም ቦታ ላይ የዮሴፍ ልጆች ወይም የማርያም ልጆች ተብለው አልተጠቀሱም /ማቴ. 12፥46 ፤ 13፥55 ፤ ሉቃ. 8፥19 ፤ ዮሐ. 2፥12፤ 7፥3 /።
 አዎየአርምሞ ሕይወት የነበራት ድንግል ማርያም ድንግልናን ከእናትነት ጋር አስተባብራ ይዛለች ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ