የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአርምሞ ትሩፋቶች

1-    እምነት
እምነት በመስማት የምናገኘው ፥ በመመስከር የምናጸናው ፥ በመታዘዝ የምንፈጽመው ነው ። እምነት ጆሮን ለመስማት ፥ ልብን ለማመን ፥ አንደበትን ለመመስከር ፥ እጅን ለመስጠት ፥ ዓይንን የጌታን ክብር ለማየት ፥ እግርን ለአገልግሎት የሚያፋጥን ነው ። ይህንን እምነት ደግሞ መልሶ የሚጎዳው አንደበት ነው ። በአንደበት የጥርጣሬ ነገሮች እንደ ቀላል ሲዘሩ የተናገርነውን ማሰብ እንጀምራለን ። ያለንበትን አድራሻም ለጠላት እናሳውቃለን ። በዚህ ምክንያት ጥርጥርና ውጊያ እየበዛብን ይመጣል ። ለግዙፉ መርከብ ትንሿ መሪ ፥ ለብርቱው ፈረስ ቀጭኗ ልጓም አቅጣጫ እንደሚወስኑ ፥ አንደበትም በማነሷ ሳትናቅ የሕይወትን አቅጣጫ ትወስናለች። የምንጓዘው ወደ ተናገርነው ነገር ፍጻሜ ነው ። ምክንያቱም ሰው የአፉን ፍሬ የሚበላ ከሆነ አንደበት ዘር ነው ። ፍሬውን በመጀመሪያ የሚበላው የዘራው ገበሬ ነው ፥ ፍሬውንም የሚያጭደው በዘራው መሬት ላይ ነው ። አንደበትም ተናጋሪውን ጠልፎ ይጥላል ፥ በዚህችው ምድር ላይም የዘራውን ያጭዳል ። አርምሞ ይህን እምነት የመጠበቅ አቅም አለው ። እምነት በጽኑ የሚታየው አርምሞን በሚቀበሉ አብያተ ክርስቲያናት ነው።
 ስንናገር ብዙ አቅም እናባክናለን ። ሰባክያን መምህራን ብርቱ አቅም ያወጣሉ ። ቀኑን በሙሉ ድንጋይ የሚፈልጠው በፈለጠ ቊጥር ጡንቻው ይጠነክራል ። የሚናገረው ግን እየሳሳ ይመጣል ። ከግዙፉ ትርጉም ስናልፍ መንፈሳዊ አቅም በመለፍለፍ ይባክናል ። ያለ ዒላማ የሚተኩስ ጥይት እንደሚያባክን ከንቱ መለፍለፍም ብዙ ኪሣራ አለው ። “በተከፈተ አፍ ራስ ይታያል” እንደሚባለው በተናገርን ቊጥር በሌሎች መገመትን ያመጣል ። በርግጥ ንግግር እየተሳለ የሚመጣው ፥ ቃላትም በቀላሉ መመረት የሚጀምሩት የንግግር ልምምዶች ሲኖሩ ነው ። ሁልጊዜ መለፍለፍ ግን አቅምን ማባከን ነው ። ከንግግር ብዛትም የሚያጸጽት ነገር አይጠፋምና እምነት እየተናጋ ይመጣል ። ይልቁንም የአፋችን አቀማመጡ ወደ ውስጥም ወደ ውጭም ገደል ላይ ነው ። አፍ ያለው ካፋፍ ነው እንዲሉ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል ። በዚህ ቃላት ቆርጣሚ በበዛበት ዘመን ሌላውን ላለመጉዳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። በርግጥ ዝም ብለን መለፍለፍን ከመረጥን ሰርተፍኬት ያለው እብድ ሆነን እንቆጠራለንና የሚቀየመን አይኖርም ። ይህ ግን እያሉ መረሳት ነው ። ከዚህ ሁሉ የሚያድነው የአርምሞ ሕይወት ነው ። አርምሞ ሁለት ነገሮችን ያሟላል ፡-
1-  ከእግዚአብሔር እያዳመጠ ይናገራል ።
2-  ክርስቶስ በእኔ ቦታ ቢሆን ምን ይናገራል ? ብሎ ይናገራል ። አርምሞ ዝምታ ብቻ ሳይሆን ንግግርም ነው ። አርምሞ ወይም ዝምታ በዓለም ላይ ከባዱ ድምፅ ነው ።
 በብዙ ንግግር የእምነት ድንበሮችን ልናፈርስ እንችላለን ። ጻድቁ ዘካርያስ የምሥራቹን እስኪፈጸም ድረስ መልአኩ ዲዳ እንዲሆን ያደረገው በአንደበቱ የጥርጥር ነገር እንዳይናገር ነው ። ዲዳ መሆኑ ቅጣት አይደለም ። መጠበቂያ ነው ። አርምሞ አንደበት የሚናገርበትን ጊዜና ቦታ የሚለይ ነው። ሁሉንም መናገር ሁሉንም አለመናገር ሳይሆን የሚያስፈልጉበትን ቦታ መለየት እርሱ አርምሞ ይባላል ። ብዙ ለፍልፈን ስንገባ ፥ በከንቱ ክርክር የአንደበት ትግል ስናደርግ ውስጣችን ስንቅ ጨርሶ መዛል ፥ ትጥቅ ጨርሶ መውደቅ ይገጥመዋል ። አርምሞ ግን ወደ እምነት ይመራል ። እምነት እግዚአብሔርን መጠበቅና ከእኔ አቅም በላይም ይሠራል ብሎ መተማመን ነውና ። እምነት ድምፅ አልባ ፉከራ አለው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም የአርምሞ ሕይወት ብቻ አይደለም የታላቅ እምነትም ባለቤት ነበረች ።
መልአኩ ገብርኤል ይዞት የመጣው የምሥራች በአእምሮ ለመቀበል የሚከብድ ነው ። አንዲት ሴት ያለ ወንድ ዘር እንደምትፀንስ የሚናገር ነው። ዘካርያስ እንኳ በሽምግልና ዘመኑ እንደሚወልድ ሲነገረው መቀበል ከብዶታል። ዘካርያስ ለመቀበል ቢከብደው ከፊቱ አብርሃም ነበረለት ። የአብርሃምን እርጅና ፥ የሣራን መካንነት ማሰብ ይችላል ። ማጣቀሻ የነበረው ጻድቁ ዘካርያስ የምሥራቹን መቀበል አቃተው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን ያለ ወንድ ዘር የፀነሰች ሴት አታውቅም ። ምንም ማጣቀሻ በሌለበት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብላ በእምነት ተቀበለች ። እንዲህ ያለ እምነት ከዚህ በፊትም ከዚህ በኋላም አልታየም ። እግዚአብሔር ያለ ምክንያት መሥራት ይችላል ። የእግዚአብሔርን ተስፋ ለመቀበል መያዣ የሚፈልጉ እምነት ያለ መያዣ የምንቀበለው በእግዚአብሔር መቻል የምንደላደልበት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋቸዋል ።
የእምነት ሌላው መገለጫው መታዘዝ ነው ። ምግባር የሌለው እምነትና እምነት የሌለው ምግባር ሁለቱም አደገኛ ነው ። ምግባር የሌለው እምነት የአንደበት ቁማር ነው ። እምነት የሌለው ምግባርም ተስፋ የማይሰጥ ነው ።እምነት ያለ ምግባር ፥ ምግባርም ያለ እምነት ሌጣ ሁኖ አይገኝም ። ሥራ ያለው እምነትና እምነት ያለው ሥራ አስፈላጊ ነው ። ይህንን የምናገኘው በድንግል ማርያም ላይ ነው ። “እነሆኝ፥ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች /ሉቃ. 1፥38/ ። በንጉሣቸው ፊት እንደሚፎክሩ ለመታዘዝ ብቻ አይደለም ለመሞትም ዘራፍ እንደሚሉ ሠራዊት አለሁ ብላ ተነሣች ። ይህ ለመታዘዝ ቆራጥነት ነው ። እንዲህ ያለውን በጅምር የማይቆም መታዘዝ የሚሰጥ እምነት ነው ። ድንግል ማርያም በሕይወት ዘመኗ ሁሉ የደረሰባትን መከራ የተሸከመችው በዚህ ጽኑ እምነት ነው ። በዚህ እምነቷ ሰማይና ምድር የማይችለውን ጌታ በማኅፀኗ ለመሸከም እርሱ ከወደደ ይሁንልኝ አለች ። በእግዚአብሔር መቻልም ለክርክሯ ድንበር ሰጠች ። ይህን አሳቡን ለማገልገል ያለ መቆጠብ ተነሣች ።
የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሌላው እምነት ትንሣኤውን መቀበሏ ነው። ቀራንዮ ተገኝታ ጥልቅ ኀዘኗን ገልጣለች ። አብረዋትም ብዙ ሴቶች ነበሩ ። እነዚያ ሴቶች በሦስተኛው ቀን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ ሲሄዱ  እርሷ አልሄደችም ። ለምን ? ስንል ትንሣኤውን ታምን ስለነበር ነው ። ከቅርብ ቤተሰብ በፊት ማንም ወደ መቃብር አይሄድም ። እርስዋ ግን ልጇ እንደሚነሣ ታምን ነበር ። ስለዚህ ሕያውን ከሙታን መካከል  አልፈለገችውም ። እምነት ባለቀው ነገር ላይ እግዚአብሔር መጀመር እንደሚችል መቀበል ነው ። ለእርሱ ከሕመም መጀመርም ከሞት መጀመርም ሁለቱም ያው ነው ። ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሁለት ታላላቅ እምነቶችን እናገኛለን ። እግዚአብሔር ያለ ምክንያት እንደሚሠራና ባለቀ ነገር እንደሚጀምር ነው ። እነዚህን ነገሮች ማመን ከፍርሃት ያድናል ።
እምነት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ረቂቅ ድልድይ ነው ። እግዚአብሔርን የምናይበትና ሥራውን የምናስተውልበት መንፈሳዊ መነጽር ነው። ያለ እምነት መንፈሳዊውን ነገር መረዳት አንችልም ። መንፈሳዊው ነገር ከእውቀት የዘለለ ነውና ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ