የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አርምሞ ትሩፋቶች….ትዕግሥት

2- የስምዖን ትንቢት
 እመቤታችን በነፍሷ ሰይፍ ያለፈው አንዱ ስምዖን ስለ ልጇ መከራ ስለ እርስዋ ኀዘን በነገራት ጊዜ ነው /ሉቃ. 2፥34-35/ ። በከብቶች በረት ልጅን መውለድም አንዱ የመስቀል አካል ነው ። እስካሁን መንገድ ላይ ስለተወለዱ ሰዎች ሰምተናል ። በረት ውስጥ ስለ ተወለደ ንጉሥ ግን አልሰማንም ። ጌታ ግን የተወለደው በበረት ነው ። በጌታ ላይ የሚሆኑት ሁሉ ለማመን የሚያዳግቱ ናቸው ። የመልአክ ብሥራት ይሰማል ፥ በተቃራኒው የአይሁድ ሴራ ይሰጋል ። በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ጠፍቷል ፥ በተቃራኒው ሰማይ ተከፍቶ ምስጋና ይሰማል ። ከብቶች እስትንፋሳቸውን ይገብራሉ ፥ በተቃራኒው ደግሞ ነገሥታት ከሩቅ አገር መጥተው ይሰግዳሉ ። ግብር ይቀርብለታል ፥ በተቃራኒው የድሃ መሥዋዕት ርግብና ዋኖስ ይዘው ወደ መቅደስ ያወጡታል ። ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ይነገራል ፥ ስምዖን ደግሞ የሕማም ሰው መሆኑን ያውጃል ። እጅግ ከፍ ያለ ክብርና እጅግ ዝቅ ያለ ትሕትና ቢታይም ድንግል ማርያም ግን አልተደናገረችም ። ፍጹም በሆነ ሰላም ውስጥ ትኖራለች ። ቢሆንም ለሥጋ ልደቱ ዐርባ ቀን የተቆጠረለት ልጇ ቀጣይ ዘመኑ የመስቀል ጉዞ ያለበት መሆኑን ስምዖን ሲነግራት ልቧ በዚያ ሰይፍ ይወጋል ። መስቀሉ በዕለተ ዓርብ ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ ክርስቶስ የሚጎነጨው ጽዋ መሆኑን ስትሰማ አዝናለች ። ይህን ሁሉ አርምሞ ባለው ትዕግሥት ተቀብላለች ።

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የሚናገረንና የሚሆነው ሊለያይብንና ግራ ሊገባን ይችላል። ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው ። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሁኖ በቤተሰብ መካከል ከተቀባ በኋላ ስደተኛ ሆነ ። ከቅባት በኋላ ዙፋን ሳይሆን ስደት ሲመጣ ግር ይላል ። ነቢዩ ኤልያስም 3 ዓመት ከመንፈቅ የጠፋው ዝናብ በሰማርያ ከዘነበ በኋላ ሕዝቡም ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከተመለሰና የሐሰት ነቢያት ከጠፉ በኋላ በማግሥቱ ታላቅ ተስፋ መቊረጥ ገጠመው ። ግደለኝ እያለ መጸለይ ጀመረ ። ከታላቅ ድል በኋላ ታላቅ ተስፋ መቊረጥ ይመጣል ። ጌታችንም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በዮርዳኖስ አባቱ ከመሰከረለት በኋላ ወዲያው በሰይጣን ለመፈተን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ ። ከታላቅ ምስክርነት በኋላ ታላቅ ፈተና መጣ ። ልጄ የተባለው ጌታችን “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ” የሚል የጠላት ድምፅ ፥ የጥርጥር ቃል መጣበት ። ሐዋርያት በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ ሕዝብ በአጠቃላይ ሺህ ሕዝብ ባሳመኑ ሰዓት ሃይማኖታቸው ብሔራዊ ሃይማኖት ሁኖ አልጸደቀም ። ወዲያው ስደት መጣ ። በዓለም ሁሉ ተበተኑ ። ከታላላቅ ቅባቶች ፥ ድሎች ፥ ምስክርነቶች ፥ ምርኮዎች በኋላ የሚመጡትን ፈተናዎች መገንዘብ ያስፈልጋል ። ብዙዎች ተደናግረዋል ። የሰማሁት ድምፅ ፥ የተቀባሁት ቅባት ሐሰት ነበረ ወይ ? የሚል መደናገር ውስጥ ገብተዋል ። ይህን መደናገር ለማራቅ ከድንግል ማርያም ሕይወት መማር ያስፈልጋል ።
3- የግብፅ ስደት
አዳምና ሔዋን በኃጢአት በወደቁ ጊዜ ፍርዱን በመጀመሪያ የተቀበለው የተንኮሉ ጠንሳሽ የሆነው ሰይጣን ነው ። ታላቁ ተስፋ የመዳንም የምሥራች የተነገረው ሰይጣን ርግማንን ሲቀበል ነው ። በዚህም ሁለት ነገሮች እንረዳለን። የመጀመሪያው አዳምና ሔዋን ፍርዳቸውን ሳይሰሙ መዳናቸውን ሰሙ ። ሁለተኛ ሰይጣን በመጣሉ ፈጽሞ ደስ እንዳይለው ደስታውን አቋረጠበት፥ አዳምና ሔዋንም በመውደቃቸው ፈጽሞ እንዳያዝኑ ኀዘናቸውን ገደበው ።
የመጀመሪያው የተስፋ ቃል የመጀመሪያው ወንጌል ተብሎ የሚጠራው ዘፍጥረት 3፥15 ላይ ያለው የድኅነት ዜና ነው ። የጸጋን ትርጉም የሚነግረንም ይህ ክፍል ነው ። ጸጋ ማለት የማይገባ ደግነት ማለት ነው ።አዳምና ሔዋን ፍርድ በሚሰሙበት ሰዓት መዳንን ሰሙ ። ይህ ጸጋ ወይም የማይገባ ደግነት ነው ። ቃሉ ፡- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ይላል ። ሰይጣን ይህን ድምፅ ከሰማበት ጊዜ አንሥቶ የሴቲቱን ዘር የሚወጣበትን መስመር ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል ። ለምሳሌ ፡-
–    በዮሴፍ ዘመን በዓለም ሁሉ የተነሣው ረሀብ ይህን ዘር ሊያጠፋ የተቃረበ ነበር ። እግዚአብሔር ግን በተሸጠው በዮሴፍ አማካይነት ያንን ዘር ከጥፋት ታድጎታል ።
–    በፈርዖን አማካኝነት የእስራኤል ወንድ ሁሉ እንዲገደል አዋጅ ተነግሯል። ዓላማውም ያንን ዘር ማጥፋት ነበር ።
–    አሦራውያን በ722 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ እስራኤልን ለመበረዝ ሙከራ አድርገዋል ። በዚህም ውስጥ የጠላት አሳብ ያንን ዘር ባገኝ ብሎ ነው ። አሦራውያን ግን መሢሑ የሚወጣበትን የይሁዳ ዘር አልነኩም ።
–    በ586 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ባቢሎናውያን እስራኤልን አገርና መቅደስ አልባ አድርገው ለማጥፋት ሞክረዋል ። ከሰባ ዓመት በኋላ እንደገና ተመሥርተዋል ።
–    በ70 ዓ.ም. ሁለተኛው መቅደስ ሲፈርስ የእስራኤል ልጆች በሮማውያን ሰይፍ አልቀዋል ። ከሞት የተረፉትን ለግብጻውያን ባሮች አድርገው ሸጠዋቸዋል ። ባሪያ አንገዛም ሲሉም ምርቃት አድርገው ሰጥተዋቸዋል።
–    በቅርብ ዘመናት እንኳ በእስራኤል ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ነበር ። ከኢትዮጵያም ጋር ተመሳሳይ ዕድል ታይቷል ። ሃይማኖታችንም ባሕላችንም ከእስራኤል ጋር ተመሳሳይነት አለውና መከራችንም ይመሳሰላል ። ፋሽስት ኢጣልያ ከ1928-33 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወርሮ በመርዝ ጋዝ ሕዝቡን በሚፈጅበት በዚያው ጊዜ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1939 ህዳር 9 ለህዳር 10 አጥቢያ የጀርመን ናዚ በአንድ ቀን 30ሺህ ወንድ አይሁዳውያንን ወደ ማጎሪያ ካምፕ ወስደዋል ። በመርዝም ፈጅተዋል ። ፋሽስት ኢጣልያ በዚያው ዘመን በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ገድሏል ። ገዳማትና አድባራትን አቃጥሏል ። በጀርመንም የሚገኙ የአይሁድ ምኩራቦች ተቃጥለዋል ። የዕብራይስጥ ቅዱሳት ጽሑፎች እየተቀደዱ እየተቃጠሉ አክራሪ ጀርመናውያን ስጦታ ተለዋውጠዋቸዋል ። ከስድስት ሚሊየን በላይ አይሁዳውያን ሲጨፈጨፉ በጀርመን የሚገኙ ዲፕሎማቶች አይተው እንዳላየ ከመሆን ሪፖርቱን ለአገራቸው መንግሥት ከማውራት ባሻገር ለመርዳትና ይብቃ ለማለት ፈቃደኛ አልነበሩም ። ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አምባሳደሯን ከጀርመን አስወጥታለች ። ብሪታንያም ስደተኞችን ትረዳ ነበር ። በተለይ  ሕጻነትን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆኗ 10ሺህ ሕጻናትን ተቀብላለች ። ዓለም ሁሉ የአይሁዳውያንን ግፍ በዝምታ አለፈ ። በኢትዮጵያም ፋሽስት ኢጣልያ ያን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም ተው ያለው አልነበረም ። ብሪታንያም ንጉሡን ለአምስት ዓመት አስጠግታለች ። ታዲያ በጄኔቫ ጉባዔ ድምፃቸውን ያሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፡- “ፍርዳችሁን ታሪክና እግዚአብሔር ሲያስታውሱት ይኖራሉ” በማለት ትንቢት ተናግረዋል ። ብዙም ሳይቆይ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ ። በ1938 ዓ.ም. አይሁዳውያን ላይ ያ ሁሉ ግፍ ተፈጸመ ። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በ1939 ዓ.ም ተጀመረ ። እስከ 1945 ዓ.ም የቆየው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ50 እስከ 80 ሚሊየን ሕዝብ ያለቀበት ነበር ። ኢትዮጵያ በ1933 ዓ.ም. ነጻነቷ ተመለሰ ። እስራኤልም በ1948 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነጻ መንግሥት ሆና ተመሠረተች፡፡
 በገነት የተሰማውን ያንን የሴቲቱ ዘር የሚለውን ተስፋ ለማጨለም ሰይጣን አልሞ ተነሣ ። ዓሣውን ለማጥፋት ውኃውን ማድረቅ በሚል መርህ በቊጣ ወጣ ። በእስራኤል ላይ የሚሆኑት ነገሮች የሰይጣን ብቀላ ናቸው ። መሢሑ ሳይመጣ ዘሩን ለማጥፋት ፥ መሢሑ ከመጣ በኋላም በቀል ነው ። ሄሮድስም የቤተ ልሔም ሕጻናትን ለመፍጀት ሲነሣ በውስጡ የጠላት ሥራ ነበረው ። እመቤታችንም አዳኝ የሆነውን ዘር ይዛ ወደ ግብጽ ተሰደደች ። የግብጽ ስደት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መናገር ይከብዳል ። የሲና በረሃ ዛሬ እንኳ ምቾት ባላቸው መኪናዎች ለማቋረጥ አስፈሪ ነው ። ያንን በረሃ አቋርጣ በግብጽ በስደት ኖረች ። ይህ በነፍሷ ካለፈው ሰይፍ አንዱ ነበር ። ይህንን ሁሉ መከራ አርምሞ ባለው ትዕግሥት ተቀብላለች ።
 ነቢዩ ዳዊት ፡- “አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና። ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት” ብሏል /መዝ. 8፥1-2/ ። ያ ጠላትና ቂመኛ ሰይጣን ነው ። ለአዳም የሆነለትን ክብርና ስጦታ በቂም ዓይን ተመልክቷል ። ጌታችን ይህ ቂመኛ ለማጥፋት የእኛን ሥጋ ለብሶ ሆሳዕና እየተባለ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ ። ጠላትም ሊያየው የማይፈልገውን አየ ። ጠላትና ቂመኛ አለብንና ጠንቃቆች መሆን ይገባናል ። ይልቁንም ብዙዎችን ወደ ሕይወት የምትመልሱ አገልጋዮች የጠላት ቂም ስላለ በማስተዋልና በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋችኋል። የግብጹ ስደት ይህን የጠላት ቂም ያስታውሳል ። በጸጋው ያግዘን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ