የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንቺ ሴት

“ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ዮሐ. 2፥4 / ።
“የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” ወይን ጠጅ ገና እየታደለ ነው ። ግማሹ ይዞ ግማሹ ይጠብቃል ። በእስራኤላውያን ሰርግ ላይ ወይን ጠጅ ዋናው ነገር ነው ። አንድን ድግስ ልከኛ የሚያደርገው የወይን ጠጅ ግብዣ ነው ። ተጠሪው ገብቶ ሳያልቅ ወይን ጠጁ አለቀ ። ይህን ነገር ያውቁ የነበሩት የሚቀዱት አገልጋዮች ነበሩ ። ይህን ነገርም እመቤታችን አውቃለች ። እመቤታችን ላቀረበችው ጥያቄ ጌታ የሰጠው መልስ የንቀት ፥ የእምቢታ አይደለም ። ይህ የእርሱን የቅድስና ክብር ፥ የእስራኤላውያንን የአነጋገር ዘይቤ ፥ የቃሉንም ፍቺ አለመገንዘብ ነው ። እናቱን በሚመለከት የሚነሡ ሌሎች ጥቅሶችም አሉ። ወንጌላዊው ማቴዎስ የዘገበውን ቀጥሎ እንመልከት ።

“ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንዱም ፡- እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፡- እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ” /ማቴ . 12፥46-50/ ።
ይህን ጥቅስ በመጥቀስ ኢየሱስ ለእናቱ ምንም ክብር እንዳልነበረው የሚናገሩ ሰዎች አሉ ። ጥቅሱ ግን የሚያሳየን ምንድነው ?
1-  “ገናም ለሕዝቡ ሲናገር” ይላል ። ቃለ እግዚአብሔር ከተጀመረ በኋላ መነጋገር እንደማይፈቀድ ፥ ይህ ንጉሣዊ አዋጅ እስኪፈጸም ጽሞና እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው ። ዛሬም ቃለ እግዚአብሔር ከተጀመረ በኋላ ንጉሥ ፥ ጳጳስ ቢመጣ ማቋረጥ አይገባም ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተማሪዎች ሲመገቡ ደረሱና ሁሉም ተማሪ ተነሥቶ ሲቀበላቸው አንዱ ተማሪ ግን መመገቡን ቀጠለ ። እርሳቸውም ጠጋ ብለው፡- “እነዚህ ሁሉ ሲነሡ አንተ ግን ያልተነሣኸው ለምንድነው ?” አሉት ። ተማሪውም፡- “ወላጆቼ ገበታ ንጉሥ ነው” ብለውኛል አላቸው ። ንጉሡም፡- “ትልቅ ወላጅ ነው ያሳደገህ” ብለው አድንቀውታል ። የምድሩ ገበታ እንዲህ ክቡር ከሆነ የሰማዩ ገበታ የበለጠ የከበረ ነው።
2-   “አንዱም” ይላል ። ያ ስሙ እንኳ ያልተጠቀሰው ሰው አቀራረቡ ቀናነት ያልተላበሰ ነው ። ምናልባት ይሁዳ ይሆናል ብለን እንገምት። ኢየሱስ ክርስቶስን ከደቀ መዛሙርቱ የሚለይ ንግግር ነው። ወገናዊነትን በማስተጋባት በጉባዔ ተናገረ ። የጉባዔ ስህተት በጉባዔ መታረም አለውና ጌታ መልስ ሰጠ ። ቀና ሰው ቢሆን ኑሮ የመጀመሪያ ትምህርቱ እስኪያልቅ እንግዶችን ማቆየት ነበረበት ። ሁለተኛ ጠጋ ብሎ ለጌታ ብቻ መንገር ነበረበት ። ይህ ሰው ግን የማሳጣት በሚመስል ድምፅ ተናገረ ።
3-  “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው።” ጌታችን እናቱን መካዱ አይደለም ። ዝምድና የሥጋ ብቻ ሳይሆን የዓላማም መሆኑን ለመግለጥ ነው ። በዓላማ የተዛመደም እናት ፥ ወንድም ፥ እኅት ነው ። ጠባብ ሰዎች ግን የዓላማን ዝምድና አያውቁም ። በርግጥም ጌታ እንዲህ ሊባል አይገባውም ። እየኖረ ያለው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነውና ። አንዳንድ መምህራን ከአገር ተሰደው ደቀ መዛሙርትን ዘመድ አድርገው ሲያስተምሩ “ዘመዶችዎ መጡ” ሲሏቸው ይበሳጫሉ ። “እኔ እኮ የኖርኩት እናንተን ዘመድ አድርጌ ነው” ይላሉ። ይህ ብዙ ጊዜ ይገጥመናል ። የጌታም ንግግር ይህን የሚገልጥ ነው።
ስለዚህ ይህ ክፍል እናቱን ለማቃለል ተናገረ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ቅድስናውን እየካዱ ነው ። በዚህ ጠላቶችም አላሙትም ። የቃና ዘገሊላው ምላሽም ንቀት የመሰላቸው ወገኖች አሉ ። “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ዮሐ. 2፥4 / ። ይህ ንግግር ንቀት የማይሆንበትን ምክንያት እናቅርብ ፡-
1-  ቅድስናው የባሕርዩ የሆነው አምላክ ቅድስና ስጦታችን የሆነውን እኛን “አባትህንናእናትህን አክብር” ብሎ ትእዛዝ ከሰጠ እንዴት እርሱ የወለደችውን ያቃልላል ?
2-  ፈሪሳውያንን የወቀሰበት ንግግር ለወላጆች ክብር የቆመ መሆኑን ይገልጣል ። “እግዚአብሔር፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ፡- አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤ እናንተ ግን፡- አባቱን ወይም እናቱን፡- ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ” ብሏል /ማቴ. 15፥4-6/ ። ምን ማለት ነው ? ወላጆቹ አንድ ነገር ቢለምኑት ይህ ነገር መባ ነው ካለ ነጻ እንደሆነ ፈሪሳውያን ያስተምሩ ነበር ። ወላጆችን ላለመርዳት ሰበብ የሚያበጁትን የሚወቅስ ንግግር ነው ። ለሕጉ የርቀት አጥር ነው ያሉት ወግ ሕጉን የሚያፈርስ ነበረ ።
3-  ጌታችን እናቱን እንደሚያከብር በመስቀል ላይ ሳለ አሳይቷል /ዮሐ. 19፥26/ ። በመስቀል ላይ ከተነገሩት ቃሎች ሦስተኛው እናቱን የሚመለከት ነው ። እናቱን ለዮሐንስ በአደራ መልክ ሰጥቷል ። ለእርሱ በሚታሰብበት ሰዓት ለእናቱ ማሰቡ ክብሩ እስከዚህ ድረስ እንደ ነበር ያሳያል ። ተጠቅሞ ጥሏታል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ከጣላት እንዴት በመስቀል ላይ አሰባት ? ይህን ያደርግ ዘንድ በእርሱ ዘንድ የለም ።
በቃና ዘገሊላም፡- “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ማለቱ ለምንድነው ? /ዮሐ. 2፥4 / ። አንቺ ሴት የሚለው ንግግር ንቀትን የሚያሳይ ነው ወይ ? ሴት የጾታ ስም ብቻ ሳይሆን የሰብእና ስም ነው ። ሰው አንድ ነው ። የአንዱ ሰው ሁለት ክፍሎች ወንድና ሴት ናቸው ። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል /ዘፍ. 1፥27/ ። ሴት የሚለውን ስያሜ ለሔዋን ያወጣው ቀዳማዊ አዳም ነው ። “አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” /ዘፍ. 2፥23/ ። ሴት የሚለው የተፈጥሮ መጠሪያ ምትክነትን አመልካች ነው ። ሴት የሚለው በየትኛውም ስፍራ የንቀት አጠራር አይደለም ። ጌታችን ግን እናቱን ከቃና ዘገሊላ በኋላ አንቺ ሴት እያለ ይጠራታል ። ይህ አጠራር በመስቀል ላይም ተደግሟል ። ለምን እናቴ አላላትም ? ብንል እርሷ በመሢሕነቱ ለዓለም ገለጠችው ። ከዚህ በኋላ የቤት ልጅ መሆኑ ያበቃ እንደሆነ መሰከረች ። እርሱም እርሷን የብቻው እናትነቷ ማብቃቱን ለዓለም በሚገልጥ ቋንቋ “አንቺ ሴት” አላት ። ዓለም ከዚህ በኋላ በኢየሱስ እናትነቷ ብቻ አያውቃትም ። የሁሉም እናት ትሆናለች ። ቀዳማዊ አዳም ሴት የሚለውን ስም አወጣ ። ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ሴት በማለት ዳግሚት ሔዋን መሆኗን መሰከረ ። የመጀመሪያው የተስፋ ቃል ይህን ሴት የሚለውን መጠሪያ ይይዛል ፡-
 “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” /ዘፍ . 3፥15/ ።
–    ተናጋሪው ማነው ? እግዚአብሔር ።
–    ቀጥተኛ ሰሚው ማነው ? ሰይጣን ።
–    ተስፋነቱ ለማነው ? ለአዳምና ለሔዋን ።
–    የሴቲቱ ዘር የተባለው ማነው ? ክርስቶስ ።
–    ክርስቶስ ለምን በሴት ዘር በኩል መጣ ? ከአዳም ኃጢአት ንጹሕ መሆኑን ለመግለጥና የሴትን ዓለም ለመካስ ነው ።
–    ሴትን እንዲህ ሲያከብር አዳምን አላከበረውም ወይ ? በወንድ ጾታ ተገለጠ።
–    የሰይጣን ዘር የተባሉት እነማን ናቸው ? በክርስቶስ የማያመኑ ሁሉ ።
–    የሴቲቱ ዘር የተባለው ክርስቶስ ብቻ ነው ? በእርሱ የሚያምኑ ሁሉም።
–   ጠላትነቱ እስከ መቼ ነው ? እስከ ዘላለም ነው ። የክርስቶስ ሞትም ሰውና እግዚአብሔርን እንጂ ሰውና ሰይጣንን ያስታረቀ አይደለም ።
–    ራሱን የሚቀጠቅጠው ማነው ? ክርስቶስ ነው።
–    ራስን መቀጥቀጥ ማለት ምን ማለት ነው ? እባብ ራሱን ከተመታ ተስፋ የለውም ። ሰይጣንም በክርስቶስ ሞት አልሞተም ተስፋ የለሽ ግን ሁኗል ።
–    ሰኰናን የሚቀጠቅጠው ማነው ? ሰይጣን ነው ።
–    ሰኰናን መቀጥቀጥ ማለት ምንድነው ? ሰኰናው የተቀጠቀጠ መራመድ አይችልም ። እስኪድን ያነክሳል ። ሰይጣንም በአይሁድ ልብ አድሮ የክርስቶስን ሞት አሰናድቷል ። ሰኰናው ለሦስት ቀን ታሞ ከሞት ተነሥቷል ። በሚድን ቊስል የማይድን ቊስል ለጠላት ከፍሎታል ።
–    ይህን ተስፋ ለሰይጣን ለምን ነገረው ? አዳምና ሔዋንን በመጣሉ ፈጽሞ ደስ እንዳይለው ደስታውን ለማቋረጥ ነው ። የሴቲቱ ዘርም ደም መላሽ መሆኑን ለማሳወቅ ነው ። ስለዚህ ሰይጣን ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ሥጋት ገባው ። የሴቲቱን ዘር ለማጥፋትም ማሰስ ጀመረ ።
–    የተስፋውን ቃል ሲሰሙ አዳምና ሔዋን ምን ይሉ ይሆን ? ፍርዳቸውን ሳይሰሙ መዳናቸውን ሰሙ ። እግዚአብሔርም በመዓቱ ውስጥ ምሕረት እንዳለው ተገነዘቡ ።
 አንቺ ሴት የሚለው ንግግር ብዙ ትንቢቶችን የሚገልጥ ነው ። “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” ይላል /ኢሳ. 7፥14/ ። ድንግል በማለቱ ክርስቶስ ፍጹም የሴት ዘር መሆኑን ያስረዳል ። ሐዋርያው ጳውሎስም ፡- “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ይላል /ገላ. 4፥4/ ። ክርስቶስም አንቺ ሴት በማለቱ ይህን ሁሉ ምሥጢር ለማስተጋባት ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ