የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ

“እናቱም ለአገልጋዮቹ ፡- የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው”
 /ዮሐ. 2፡5/ ፡፡
እመቤታችን ድንግል ማርያም ለልጅዋ ለወዳጅዋ ካሳወቀች በኋላ አገልጋዮቹን አዘዘች ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰርገኞቹ ምንም አያውቁም ፡፡ የሚለምንላቸው ወገን ፣ የሚፈጽምላቸው አምላክ በመካከላቸው እንዳለ አልተገነዘቡም ፡፡ ሥራው ግን ውስጥ ለውስጥ እየተሠራ ነው ፡፡ ከሰርገኞቹ ይልቅ አገልጋዮቹ ምሥጢር ያውቃሉ ፡፡ መንፈሳዊ ሥራ እዩልኝ ፣ ስሙልኝ እየተባለ አይሠራም ፡፡ እየጸለይኩልህ ነው ብሎም ባለውለታነት አይሰማውም ፡፡ እወድሃለሁ ብሎም በፍቅሩ አይመካም ፡፡ ከመውደድ ውጭ የጥላቻ አማራጭ ክርስትና የለውምና ፡፡ ፈሪሳውያን ረጃጅም ጸሎትን የመበለቶችን ቤት ለመዝረፊያ ይጠቀሙበታል ፡፡ “እነርሱ እኮ ጸሎተኞች ናቸው” ለሚለው የወሬ ፍጆታ ያስተካክሉታል ፡፡ ማስታወቂያ የሚሠሩላቸው ሰዎች ቀጥረውም “እርሳቸው እኮ የበቁ ናቸው ፣ ይህን ቢያደርጉላቸው ጸሎታቸው ይረዳል” የሚል የገበያ ባለሙያ ያዘጋጃሉ ፡፡ በዚህም የሚዘርፉት መበለቶችን ነው ፡፡ መበለቶች ባሎቻቸው የሞቱ ወይም ትዳራቸው የፈረሰ ሲሆን ብዙ ኀዘንና የልብ ስብራት አላቸውና በቀላሉ እነርሱን ይበዘብዛሉ ፡፡ ጌታችን ለእነዚህ የጸሎት ነጋድያን ፡-“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ” በማለት አስጠንቅቋል /ማቴ. 23፡14/፡፡ እመቤታችን ግን ለሰርገኞቹ ፍጻሜውን ብቻ ለማሳየት መጀመሪያ ለልጅዋ በምሥጢር ነገረች ፤ ቀጥሎ አገልጋዮቹን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለች ፡፡ የጸሎት መሣሪያ ሲጥል እንጂ ሲተኮስ አይሰማም የሚባለው ለዚህ ነው ፡፡

እመቤታችን አገልጋዮቹን ለምን አስጠነቀቀች ? አገልጋዮች ከሆኑ ሥራቸው መታዘዝ አይደለም ወይ ? ብንል አገልጋዮቹ የሚያውቁት ጌታቸውን ነው ፡፡ የጌታቸውን ጌታ አያውቁም ፡፡ አገልጋይነት ውብ የሚሆነው ከቅርብ አለቃ በላይ የሰማይን አምላክ ማየት ሲችል ነው ፡፡ የቅርብ አለቃን መሰወር ፣ ማታለል ይቻላል ፡፡ አንዳንዴም ሱስና ጉቦ በማስለመድም ሎሌ ማድረግ ይቻላል ፡፡ የሰማዩ አምላክ ግን ሳይጠይቅ ስለ ሰው የሚያውቅ ነውና ደግሞም ጣራና መጋረጃም አይሸፍነውምና እርሱን ማየት እውነተኛ መታዘዝ ያመጣል ፡፡ እመቤታችን ለአገልጋዮቹ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው ፡፡ በዚህ ውስጥ የምንረዳው ነገር ፡-
1-  ጌታ ለልጆቹ የሚለው አለ ፡፡
2-  ጌታ ለልጆቹ የሚለውን ሁሉ እንጂ መርጦ መታዘዝ አይገባም ፡፡
3-  ጌታ ለልጆቹ የሚለው የእምነት መታዘዝ ወይም እምነት ያለበት መታዘዝ ነው ፡፡
4-  ጌታ የሚለን ወይም የሚናገረን እንድናደገው ነው ፡፡
1- ጌታ ለልጆቹ የሚለው አለ
የዕብራውያን ፀሐፊ ፡- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ” በማለት መልእክቱን ይጀምራል /ዕብ. 1፡1/፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚናገር አምላክ ነው ፡፡ ያልተናገረበት ዘመንም የለም ፡፡ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ለሕዝቡ ተናግሯል ፡፡ በሕልም ፣ በራእይ፣ በነቢያት ፣ በመጻሕፍት … ተናግሯል ፡፡ በዚህ ዘመን ግን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተናገረን የመጨረሻው መገለጥ ሆኗል ፡፡ አዲስ ነገር ልንሰማ አንችልም ፡፡ ለምእመናንም በመጻሕፍት በብሉያትና በሐዲሳት ይናገራቸዋል ፡፡ መዝሙረኛው ፡- “እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል” ይላል /መዝ.86፡6/፡፡ ሕዝቡም አለቆችም መጽሐፍ ምን ይላል ? ማለት ይገባቸዋል ፡፡ እግዚአብሔር በእርግጠኝነት የሚናገረው በተጻፈው ቃሉ በኩል ነው ፡፡ ሕልም ፣ ራእይ ፣ መገለጥ ቢኖር እንኳ ፡-
1-  በቃሉ መመዘን አለበት
2-  ከጠላትም ሊሆን ይችላል
3-  ከቃሉ በላይ መተረክ የለበትም ፡፡
በዚህ ዘመን ያለውን ክርስትና እየጎዳው ያለ ነገር ምንድነው ? ስንል የመጀመሪያው ሊቅ ነኝ ባይ መብዛቱና አለመናገር እንደ መሞት እየተቆጠረ ሁሉም አሳብ ሰጪ መሆኑ ነው ፡፡ ሁለተኛው የተቦጨቁ ጥቅሶች ያለ ቦታቸው መዋላቸው ነው ፡፡ ከተጻፈበት መሠረታዊ አሳብ ውጭ ጥቅሶች ምስክር ተደርገው ይጠራሉ ፡፡ ይህ የብዙ ኑፋቄ ምንጭ ነው ፡፡ ሦስተኛው ቃሉን አስማታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ነው ፡፡ ለምሳሌ ፡- “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ” የሚል ጥቅስ ሲሰሙ የጀመሩት የውጭ አገር ጉዳይ አልቆልኛል ፤ ምክንያቱም ጌታ ተናግሮኛል ፣ መንገዴን አደራ እሰጣለሁ የሚል እምነት መሳይ ነገር ይታያል ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙዎች ለከፍተኛ ቀቢጸ ተስፋ ተዳርገዋል ፡፡ ቃሉን ትንቢታዊ በሆነ ድምፅ የሚረዱ ሰዎች ለዚህ አደጋ ይጋለጣሉ ፡፡ ከመታዝዝ ይልቅ የተአምራት ናፍቆት ውስጥ ይገባሉ ፡፡ ለምሳሌ ፡- “ዕረፉ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” የሚል ጥቅስ ሲሰሙ ቤተ ክርስቲያን ይቀራሉ ፡፡ ጌታ ዕረፊ ፣ ዕረፍ ብሎኛል ይላሉ ፡፡ አንድን የአግዚአብሔር ቃል ለመረዳት ፡-
1-  የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ አሳብ መረዳት
2-  የክፍሉ አሳብ ምን እንደሆነ ማወቅ
3-  ከሐዋርያት በቅርብ ርቀት የነበሩ አባቶች የተረዱበትን መንገድ መመርመር ይገባል ፡፡
ይልቁንም እግዚአብሔር ሁለቱንም ኪዳናት ያለ ባለቤት አልተዋቸውም ፡፡ የብሉይ ኪዳን ባለ አደራ እስራኤል ናት ፡፡ ሕዝቦቹ አሉና እነርሱን መጠየቅ ይቻላል ፡፡ የሐዲስ ኪዳንም ባለቤት ቤተ ክርስቲያን ናትና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ምን እንደሚሉ መመርመር በጣም ወሳኝ ነው ፡፡ እነዚህን መንገዶች በጥንቃቄ መጠቀም ካልቻልን ክርስትናውን ጠላት ከሚጎዳው በላይ እኛው እንጎዳዋለን ፡፡
 ከእመቤታችን ንግግር እግዚአብሔር የሚናገር አምላክ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ እርሱ የሚናገረው ለጌቶች አይደለም ፡፡ ለአገልጋዮች ነው ፡፡ እግዚአብሐር እንደ አገልጋይ ዝቅ ያሉትን ሰዎች ይፈልጋል ፡፡ ለትሑታን ራሱን ያብራራል /ማቴ. 11፡25/ ፡፡
2- ጌታ ለልጆቹ የሚለውን ሁሉ እንጂ መርጦ መታዘዝ አይገባም
እመቤታችን የሚላችሁን ሁሉ ብላለች ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰፈፍ የሌለው ወለላ ፣ እንክርዳድ የሌለው ስንዴ ፣ እንከን የሌለው ንጹሕ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ቃሉን የሰጠን በሙሉነት እንድንታዘዝ እንጂ መርጠን እንድንታዘዝ አይደለም ፡፡ በቃሉ ውስጥ ሃይማኖት አለ ፣ ሥርዓት አለ ፣ ትእዛዝ አለ ፡፡ ይህን በሙሉነት ማድረግ ይገባናል ፡፡
3- ጌታ ለልጆቹ የሚለው የእምነት መታዘዝ ወይም እምነት ያለበት መታዘዝ ነው ፡፡
የሠራነውን ሥራ በምን መሠረትነት እንደ ሠራነው ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ተግባሮች ብቻቸውን ንጹሕ አይደሉም ፡፡ ደግነትን ብንወስድ አንዳንዴ ሱስ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ፡፡ ሌላ ጊዜ ለማስታወቂያ ሌላ ጊዜም ጉቦ ሊሆን ይችላል ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደው መታዘዝ እምነት ያለበት መታዘዝ ነው /ሮሜ .1፡5/ ፡፡ ምክንያቱም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና ፡፡ እመቤታችን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ያለችው የሚላቸው ነገር መናኛ የሚመስል ፣ ነገር ግን ሲታዘዙለት ትልቅ ተአምር የሚታይበት ነው ፡፡ በርግጥም ወይን ጠጅ ባለቀበት ግብዣ ላይ ውኃ ሙሉ ሲባሉ ቀልድ ይመስላል ፡፡ እግዚአብሔር ግን ትንሹን ለትልቅ ክብር ያውለዋል ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በተለመደው መታዘዝ ብቻ ሳይሆን አሁን በእምነት መታዘዝ አለባቸው ፡፡ የሶርያው ንዕማን ከለምፅ ለመዳን በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ በል ቢባል የአገሩን ከብርጭቆ ይልቅ የጠራውን ውኃ ማስታወስ ጀመረ /2ነገሥ. 5/፡፡ እግዚአብሔር ግን በሞኝነት ሲታዘዙለት ክብሩን ይገልጣል ፡፡
4- ጌታ የሚለን ወይም የሚናገረን እንድናደገው ነው ፡፡
እግዚአብሔር ቃሉን እንድናደንቅለት አልሰጠንም ፡፡ ወይም እንድንከራከርበት አሊያም ሌላውን እንድንተችበት አልሰጠንም ፡፡ ቃሉን የሰጠን እንድንታዘዘው ነው ፡፡ ቃሉ ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል ፡፡እመቤታችን ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ያለችው ለዚህ ነው ፡፡ ሰው ድርሻውን ሲወጣ እግዚአብሔር ክብሩን እንደሚገልጥ ቀጥሎ የምናየው ነው ፡፡ ሰው ድርሻውን ከተወጣ እግዚአብሔር ድርሻው አይጠፋውም ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ