“ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ዮሐ. 2፡11/ ፡፡
ጌታችን በቃና ዘገሊላ ያደረገው ተአምራት የመጀመሪያ ተብሏል ፡፡ ከዚያ በፊት ተአምራት አላደረገም ወይ ? ቢባል ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከዚያ በፊት ተአምራት አድርጎ ቢሆን አይሁድ ሊገድሉት ፣ በሕጻንነቱም ሊያጠፉት ይነሡ ነበር ብሏል ፡፡ በርግጥ የጌታችን ድንግልናዊ ልደቱ በልደቱ ዙሪያም የታዩት ክስተቶች ተአምራት አይደሉም ወይ ? ቢባል አዎ አምላካዊ ክብር የተገለጠባቸው ናቸው ፡፡ ጌታችን ግን ለሕዝብ ከተገለጠ በኋላ ያደረገው የቃና ዘገሊላው የመጀመሪያ ምልክት ነው ፡፡ የመጀመሪያ ምልክት መባሉ ሌሎች እንዳሉ ያስረዳል ፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ የጌታችንን አምላክነት ለማስረዳት የገለጣቸው ሰባት ተአምራት አሉ ፡፡ ከእነዚህ ተአምራት ዮሐንስ ብቻ የዘገባቸው ሁለቱን ብንጠቅስ ቃና ዘገሊላና የመጻጉዕ መፈወስ ናቸው ፡፡
ጌታችን በቃና ዘገሊላ ባደረገው ምልክት ክብሩን እንደ ገለጠ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔር ክብሩን እንዲገልጥ በዘመናት የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ለምነዋል ፡፡ ከእነዚያ አንዱ ሙሴ ነው ፡፡ ሙሴ ባለሟልነትን ያገኘ ሲሆን የእግዚአብሔርን ድምፅ ከመስማቱ የተነሣ በዓይኑ ሊያየው እንደሚፈልግ ገለጠ ፡፡ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ” /ዘጸ. 33፡18/ ፡፡ ሙሴ የጠየቀው እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ለማየት ነው ፡፡ ድምፁን ሲሰማ መልኩን ናፈቀ፡፡ የሙሴ ጸሎት ከፍቅር የመነጨ ነው ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን አልነቀፈም፤ ነገር ግን የፀሐይን አካል በቀትር ማየት እንደማይቻል የፀሐይን ፈጣሪም ማየት አይቻልም ፡፡ እግዚአብሔርም ሙሴን ለናቁትና ለነቀፉት ለአሮንና ለሙሴ በተናገረው ቃል ሙሴ የእግዚአብሔር ፊት እንደሚያይ ገለጠ /ዘኁ. 12፡8/፡፡ ሙሴ ግን የእግዚአብሔርን ፊት ሳያይ ሞተ ፡፡ አምላክ በተዋሕዶ ሰው በሆነ ጊዜ በደብረ ታቦር ይህን ክብር ለማየት ሙሴ ከመቃብር ተነሣ ፡፡ ደብረ ታቦር የክብር መገለጫ ነው ፡፡ ጌታችን ደብረ ታቦር ላይ ክብረ መንግሥቱን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው በብዙ ምክንያቶች ቢሆንም ጠቅላይ አሳቡ ግን ክብሩን መግለጥ ነው ፡፡ በደብረ ታቦር ላይ ክብሩን መግለጥ ለምን አስፈለገው ? ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው ፡፡
1- ሙሴ ክብርህን አሳየኝ ብሎ ለምኖ ነበርና ክብሩን ፊቱን እንዲያይ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን ገለጠ፡፡ በዚህም ከተጸለየ 1500 ዓመታት የሆነው ጸሎት ተፈጸመ ፡፡ እግዚአብሔር ዘመናት ቢረዝሙም ጸሎትን አይረሳም ፡፡ ዘመኔ አለፈ ፣ ጸሎቴ ተረሳ ለሚሉ እግዚአብሔር ከሞት ቀስቅሶ የሚያበላ የሺህ ዓመታትን ጸሎት የሚመልስ መሆኑን ሊያስታውሱ ይገባል ፡፡ አዳምና ሔዋንን ከ5500 ዓመታት በኋላ መጻጉዕን ከ38 ዓመታት በኋላ ሙሴን ከ1500 ዓመታት በኋላ አሰበ ፤ ልመናቸውን ፈጸመ ፡፡
2- ተስፋውን ሊፈጽም በደብረ ታቦር ክብሩን ገለጠ ፡፡ ሙሴ በምሳሌ አይደለም የእግዚአብሔርን መልክ ያያል ተብሎ ነበርና ቃሉን አክባሪ ጌታ ጸሎቱን ሊመልስ ፈቀደ ፡፡ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም የመርሳት ምክንያት ፣ ያለ መቻል እጥረት የለበትም ፡፡
3- በደብረ ታቦር ክብሩን መግለጡ ብቻ ሳይሆን የሞተውን ሙሴ ከመቃብር ያልሞተውን ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ማቆሙ ገናንነቱን ያመለክታል ፡፡ በዚህም የቤተ ክርስቲያንን መልክ ያሳያል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሕያዋን ማለት ገና ተጋድሎአቸውን ያልፈጸሙ ፣ የሙታን ማለት ተጋድሎአቸውን ፈጽመው በክብር ያሉ ቅዱሳን አንድነት ናት ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የሕያዋንና የሙታን ጌታ ነው የሚባለው በቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው ፡፡ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋንና የሙታን ጌታ መሆኑን ገለጠ ፡፡
4- ኤልያስ ኤልዛቤልን ፈርቶ ሞትን የለመነ ነቢይ ነው /1ነገሥ. 19፡3/፡፡ እግዚአብሔር ግን ከለመነው በላይ ሰጥቶት ሞትን ሳያይ በእሳት ሰረገላ ተነጥቋል /2ነገሥ. 2፡11/ ፡፡ ያንን ኤልያስን በደብረ ታቦር አምጥቶ ክብሩን ገልጦለታል ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ልመናችንን አስተካክሎ እንደሚሰማን ፣ እንደ ፈቃዱ የሚሰጠንም ከምኞታችን በላይ መሆኑን እንረዳለን ፡፡
5- ጌታችን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ? ብሎ በጠየቀ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ እንደሚሉት ደቀ መዛሙርቱ ተናግረው ነበር /ማቴ. 16፡14/ ፡፡ ሙሴና ኤልያስን በደብረ ታቦር ማምጣቱ የሙሴና የኤልያስ አምላክ መሆኑን ለመግለጥ ነው /ማቴ. 17፡1-8/ ፡፡
6- ጴጥሮስ በሰማያዊ መገለጥ ሁኖ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ መስክሮ ነበርና ሳያይ ያመነውን በማሳየት ዋጋ ሊከፍለው ነው ፡፡ የጴጥሮስን እምነት ሊያጸና በደብረ ታቦር ክብሩን ገለጠ ፡፡
እግዚአብሔር ክብሩን የገለጠውና የዘመናትን ጥያቄ የመለሰው በክርስቶስ ሰው መሆን ነው ፡፡ ለዚህም እባክህ ክብርህን አሳየኝ ያለውን ሙሴን ፣ በደብረ ታቦር የተገለጠውን ብርሃን ፣ በቃና ዘገሊላ የተፈጸመውን ተአምራት ማየት በቂ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥ የዘመናት ጸሎት ይመለሳል፤ ተስፋ ይፈጸማል ፤ ፍርሃት ይወገዳል ፤ እምነት ይጸናል ፡፡
የእግዚአብሔር ሥራ የእግዚአብሔር ክብር ነው ፡፡ በሥራው ይመሰገናልና ሥራው ክብሩ ነው ፡፡ እኛም በጎደለን ነገር ሲሞላልን ፣ ባለቀው ነገር ሲቀጥልልን ፣ በከበደን ነገር ሲያቀልልን ፣ ባሳዘነን ነገር ሲያጽናናን ፣ ባሸነፈን ነገር ባለ ድል ሲያደርገን ክብሩን አይተናል ፡፡ ልናመሰግነው ልናከብረው ይገባናል ፡፡
ክብሩ ሲገለጥ ፡-
1- ትሑት እንሆናለን ፡- ሙሴ ይህን ክብር የናፈቀ ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው ፡፡ ሙሴ ኃያል ሰው ቢሆንም ትሑት ነበረ /ዘኁ. 12፡3/ ፡፡ የትሕትናው ምሥጢር የእግዚአብሔርን ክብር የሚያውቅ መሆኑ ነው ፡፡ ምናልባት አጠገባችን ያሉትን ሰዎች እያየን በእውቀትም በመንፈሳዊነትም የተሻልን እንደ ሆንን እናስብ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔርን ስናስብ ግን በፍጹም ትሑታን እንሆናለን፤ ትሕትና የእግዚአብሔርን ክብር የማየት ውጤት ነው ፡፡
2- በጌታ እናርፋለን ፡- ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ካየው ክብር የተነሣ በዚያ መሆን መልካም እንደሆነ ተናገረ ፡፡ ሦስት ዳስ እንሥራ አንዱን ላንተ ማለት ለጌታ ፣ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ አለ /ማቴ. 17፡4/ ፡፡ ጴጥሮስ ራሱን ያዕቆብንና ዮሐንስን የት ሊያደርጋቸው ነው ? ቢባል የጌታ ዳስ ውስጥ እንገባለን ብሎ ነው ፡፡ ክብሩ ሲገለጥ የጌታ የሆነው የእኔ ነው የሚል ዕረፍት ይመጣል ፡፡
3- በክርስቶስ ማመን ይከሰታል ፡- በቃና ዘገሊላ በተፈጸመው ተአምራት ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አመኑ ይላል /ዮሐ. 2፡11/ ፡፡ የክብሩ መገለጥ ፍጻሜው እምነት ነው ፡፡
ዛሬም እግዚአብሔር በአገልግሎታችን ክብሩን እንዲገልጥ እንመኝ ይሆናል ፡፡ ክብሩን መግለጡ ተገቢ ነው ፡፡ ክብሩ እንዲገለጥ የምንመኘው ግን ሰዎች በእርሱ አምነው እንዲጠቀሙ እንጂ እኛ ዝነኛ እንድንሆን በማሰብ ሊሆን አይገባውም ፡፡