የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ

“ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ዮሐ. 2፡11/ ፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ያመኑት በመጀመሪያው ቀን በተደረገው ተአምራት ነው ፡፡ እስካሁን አላመኑትም ነበር ወይ?  ቢባል ደቀ መዛሙርቱ ገና ጌታን ከተከተሉ አንድ ቀን ሁኗቸዋል ፡፡ በቃና ዘገሊላ የተደረገው ተአምራት የሰርገኞቹን የሥጋ ጉድለት ሲሞላ የደቀ መዛሙርትን የእምነት ሸለቆ ሞልቷል ፡፡ ማመን መቅረብ ፣ ማመን መጣበቅ ፣ ማመን መሥዋዕትነት መክፈል ነው ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ አምነው ቀርበዋል ፤ ዛሬ ግን ተጣብቀዋል፡፡ በሌላ ዘመን ደግሞ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነት ብዙ ይናገራል ፡፡ እምነት ሦስት ክፍሎች አሉት ፡-
1-  የሚያድን እምነት
2-  የሚያኖር እምነት
3-  የሚያስችል እምነት
1-  የሚያድን እምነት ፡-
በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ህልውና ፣ በአንድነቱና በሦስትነቱ ፣ በክርስቶስ አምላክነትና መድኃኒትነት ማመን የሚያድን እምነት ነው ፡፡ በዚህ እምነት ተመሥርተን ምሥጢራትን እንፈጽማለን፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ኅብረት እናደርጋለን ፡፡ አባቶች እንደ ዋዛ የሚናገሩት ቃለ አሚን የእግዚአብሔርን ማንነትና ግብር የክርስትናንም መሠረት ይገልጣል ፡፡ “የጌትነቱ ክብር ፣ የበጎነቱ ግብር” በማለት ይገልጣሉ ፡፡ ይህ አጭር አገላለጥ ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያብራራ ነው ፡፡ የጌትነቱ ክብር አንድነቱ ሦስትነቱ ነው ፡፡ የበጎነቱ ግብር እኛን ለማዳን ሰው መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የጌትነቱ ክብር ከራሱ የሚመነጭ ነው ፡፡ ለእኛ ያደረገው ተግባርም ከበጎነቱ የሚመነጭ እንጂ የእኛን ማንነት ያገናዘበ አይደለም ፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”  በማለት ይህን የበጎነት ግብር ገልጦታል /ዮሐ. 3፡16/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ማዳን የእግዚአብሔር ነውና ክርስቶስ ሰው ሁኖ በፈጸመው ተግባርም አብና መንፈስ ቅዱስም አዳኝ እንደሚባሉ እንረዳለን ፡፡ አብ ዓለምን አፈቀረ ፣ ወልድ በመስቀል ላይ ሞተ ፣ መንፈስ ቅዱስ የቤዛነቱን ዋጋ እንዲቀበሉ ሰዎችን አገዘ፡፡ እግዚአብሔር በፍቅሩም በአዳኝነቱም አንድ ነው ፡፡ የሚያድነን እምነት በሥላሴ እንዲሁም በክርስቶስ ሥጋዌ ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሲል የመጀመሪያው የሚያድነውን እምነት እየገለጠ ነው ፡፡
2-  የሚያኖር እምነት ፡-
 “ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና” /ሮሜ 1፡17/ ፡፡ ይህ ቃል መጀመሪያ የተነገረው ለነቢዩ ዕንባቆም ነው ፡፡ ነቢዩ ዕንባቆም የሰው ግፍና የእግዚአብሔር መዘግየት ጥያቄ ሁኖበት ብርቱ ትግል ገጥሞ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ግን የሰጠው ምላሽ ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት እንደሚኖር ነው፡፡ እነዚህ ሙግቶች በእምነት ካልታዩ ወደ መንፈሳዊ ሞት ይወስዳሉ ፡፡ ከፍ ያለው ዝቅ ያለውን ለምን ያስጨንቀዋል ? ግፍ በከተማው ሲንሰራፋ ያ ደግ እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል ? ገዢዎች ጉቦ በልተው ፍትሕን ሲሸጡ ይህች ዓለም ባለቤት የላትም ወይ ? አፍቃሪዎችና ደጎች ሁልጊዜ ሲያለቅሱ እግዚአብሔር ለገዛ ቃሉ ግድ አይለውም ወይ ? የሚሉ አሳቦች ይሞግቱት ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ግን ያሳየው ትዕግሥት ከነገሩ ጋር መስማማት ሳይሆን ለንስሐ ጊዜ መስጠት ነበር ፡፡ በቁጣ ከመጣም የሚመልሰው የለም ፡፡ ለነቢዩ ግን ጻድቅ በእምነት ይኖራል አለው ፡፡ እምነት የአንድ ቀን አዋጅ ብቻ ሳይሆን ዕለት ዕለትም በቅድስና የምንገለጥበት በመሥዋዕትነት የምናብብበት ነው ፡፡
3-  የሚያስችል እምነት ፡-
 ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት አንዱ ስጦታ መሆኑን ይናገራል ፡፡ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው” ይላል /ሮሜ. 12፡3/ ፡፡ ይህ እምነት የሥጦታ እምነት ሲሆን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከፍ ብሎ ይታያል ፡፡ ታላላቅ ነገሮችን ለማድረግ ልባቸው ሙሉ ነው ፡፡ ይህ እንዲህ ይሆናል በማለት ተራራን የሚደረምስ እምነት አላቸው ፡፡ ይህ የስጦታ እምነት ነው ፡፡
 ደቀ መዛሙርቱ በጌታችን አመኑ ፡፡ የክብሩ መገለጥ ደቀ መዛሙርትን ከግንዱ ጋር ቅርንጫፍ ለመሆን የሚያጣብቅ እምነትን ሰጣቸው ፡፡ እምነት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው ፡፡ እምነት ስንል ሁለት ነገሮችን እየገለጥን ነው ፡፡
1-  የምናምንበትን አምላክ
2-  የሚያምነውን ልባችንን
 እምነታችንን እውነተኛ የሚያደርገው የምናምንበት ነገር ትክክል መሆኑ እንጂ እምነታችን ብቻ አይደለም ፡፡ ሰዎች ከልባቸው ጣዖታትን ያምናሉ ፡፡ ይህ ማለት እምነታቸው ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም ፡፡ ከልብ ማመን የሚያምኑበትን ትክክለኛ አያደርግም ፡፡ የሚምኑበት ነገር ትክክለኛነት ግን እምነታችንን እውነተኛ ያደርገዋል ፡፡ የእውነተኛ እምነት መሠረቱ የእግዚአብሔር ቃል ነው ፡፡ “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው”ይላል /ሮሜ 10፡17/፡፡ የምንሰማው ሁሉ እምነትን አያመጣም ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ግን እምነትን ማግኘት ይቻላል ፡፡ እምነት መሠረቱ ፍልስፍና ወይም የሰው ልብ ያነቃው አይደለም፡፡ የእምነት መሠረቱ የእግዚአብሔር ቃል ነው ፡፡
 አንድን ነገር በመጀመሪያ እናውቀዋለን ፤ ስናውቀው እንወደዋለን ፣ ስንወደው እናምነዋለን ፣ ስናምነው እንኖርለታለን ፡፡ ማወቅ መሠረት ነው ፡፡ ማወቅን የሚጠላ ወደ እውነተኛ እምነት ሊደርስ አይችልም ፡፡ አለማወቅ ጠባቂ ማወቅ አሳሳች ተደርጎ መታሰብ የለበትም ፡፡ በነቢዩ በሆሴዕ ፡- “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ” ይላል /ሆሴ. 4፡6/፡፡ እውቀትን መጥላት ትክክለኛ ማንነት አይደለም ፡፡ ጌታችንም የዘላለም ሕይወት አብና ወልድን በማወቅ ላይ እንደ ተመሠረተ ተናግሯል /ዮሐ. 17፡3/ ፡፡
 ከላይ የተጠቀሱት ሦስት የእምነት ክፍሎች ዛሬም ያልደረሱባቸው ወገኖች አሉ ፡፡ በሥላሴ ደግሞም በክርስቶስ የማያምኑ ብዙዎች አሉ ፡፡ እነዚህ ሰዎች መዳናቸውን እየጣሉ ነውና ልንደርስላቸው ወደ እውነትም ልንመራቸው ይገባል ፡፡ በሥላሴ አምነው በክርስቶስ አዳኝነት ተማጽነው ነገር ግን ፍሬ የሌላቸው አሉ ፡፡ እነዚህም ከእምነት ወደሚነሣው መታዘዝ እንዲገቡ ሊመከሩ ይገባል /ሮሜ. 1፡5/ ፡፡ በታላላቅ ችግሮች ውስጥ የእግዚአብሔርን ትልቅነት በማየት መጽናት ያቃታቸው አያሌ ሰዎች አሉ ፡፡ እግዚአብሔር በእርሱ የመደገፍን የእምነት መጠን እንዲያበዛ መለመን ያስፈልጋል ፡፡ ትልቅ ችግር በትንሽ እምነት ፊት መቆም አይችልም ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በክርስቶስ አመኑ ፡፡ እኛስ የጎደለን የትኛው እምነት ነው? ወደሚያኖርና ወደሚያስችለው እምነት ለመቅረብ የሚያድነውን እምነት ከልባችን መያዝ ይገባል ፡፡   
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ