የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ እሑድ የካቲት 6/2008 ዓ.ም.
ቃል ዘላለማዊ ነው
ወንጌላዊው ዮሐንስ ቃል ሥጋ መሆኑን ከመግለጡ በፊት ቃል ዘላለማዊ መሆኑን ይናገራል /ዮሐ. 1፡1/። ሁሉ በእርሱ ከመሆኑ በፊት እርሱ ከዘላለም ነበረ /ሚክ. 5፡2፤ዮሐ. 1፡3፤ዕብ. 13፡8/። ያው ቃል ሥጋ ነው ሥጋ ሆነው /ዮሐ. 1፡14/። ሥጋ በመሆኑም አምላክነቱን አልከሰረም። እርሱ ዝቅ አለ፣ እኛን ግን ከፍ አደረገን። ዘመን የማይቆጠርለት ቃል ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋን ተዋሐደ።
እያንዳንዱ የሥላሴ አካል በአካልነቱ፣ በግብሩና በኩነቱ የሚጠራበት ስም አለው። አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካላት ስም ነው። አብ፣ አብ የተባለው በአካሉ፣ በህልውናው ነው። አብ መባልም ከዘላለም ገንዘቡ ነው። ወልድ፣ ወልድ መባሉ የአካሉ የህልውናው ስም ነው። ወልድ መባሉም ከጊዜ በኋላ ሳይሆን ከዘላለም የሆነ ስሙ ነው። መንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ መባሉ የአካሉ የህልውናው ስም ነው።
የግብር ስም የሚባለው አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ መባሉ ነው። የግብር ስም የሚለውን ያመጣው፣ አብ መባል የአካሉ ስም ሲሆን ወልድን በመውለዱ ግን ወላዲ እንደ ተባለ ለመግለጥ ነው። መጀመሪያ የአካሉን ምልአት መቀበል ይገባል። የአካሉና የህላዌ ስሙ አብ ነው። የግብር ስሙ ግን ወልድን በመውለዱ ወላዲ ነው። ይህ ማለት እኛ ሰው የምንባለው በህልውናችን፣ ወላጅ የምንባለው በግብራችን፣ አናጢ ገበሬ የምንባለው በሆንነው አስተዋጽኦችን ነው። አብ፡- በአካሉ አብ፣ በግብሩ ወላዲ፣ በኩነቱ/በሁነቱ/ ልብ ይባላል።
የኩነት ስም የሚባለው አብ ልብ፣ ወልድ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ እስትፋስ መሆኑ ነው። አብ ልብ ነው ሲባል ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ማሰቢያቸው ነው። ስለዚህ ሥላሴ አንድ ልብ፣ አንድ ፈቃድ አላቸው። ወልድ ቃል መሆኑ በአብ መሠረትነት ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው፣ መናገሪያቸው፣ ማድረጊያቸው ነው። ለዚህም እግዚአብሔር በቃሉ “ይሁን” እያለ ዓለማትን ፈጥሮአል /ዘፍ. 1፡3፤ ዕብ. 11፡3/። መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ወይም ሕይወት ነው። በአብ መሠረትነት ለራሱ እስትንፋስ ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው፣ መኖሪያቸው ነው። ስለዚህ ሥላሴ አንድ ፈቃድ፣ አንድ ተግባርና አንድ ሕይወት አላቸው የሚባለው በኩነታት ነው። እያንዳንዱ የሥላሴ አካል የራሱ ልብ፣ ቃል፣ እስትፋስ አለው ማለት ሥላሴን ሦስት ፈቃድ፣ ሦስት ተግባርና ሕይወት አላቸው ማለት ነው። እንዲህ የሚያስቡ የዘጠኝ መለኮት ትምህርት አራማጅ ተብለው በአገራችን ይጠራሉ። ይወገዛሉ።
ኩነታት ወይም ልብ፣ ቃል፣ እስትፋስ የሥላሴን አካላት የሚያስተሳስሩ አንዱ በአንዱ ውስጥ ህልው እንዲሆን የሚያደርጉ ናቸው። ልብ ያለ ቃልና እስትፋስ እንደማይኖር አብም ያለ ወልድና ያለ መንፈስ ቅዱስ ለቅጽበት አልኖረም። አይኖርምም። ኩነታት ወይም ልብ፣ ቃል፣ እስትፋስ የሥላሴን አካላት እያገናዘቡ በመለኮት አንድ የሚያደርጋቸው ምሥጢር ነው። አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ ሲሆን ከወልድ ቃልን ከመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስን ይወስዳል። ሲሰጥ ኩነት የተባለው ሲቀበል ነሢዕ ይባላል። ሲሰጥ ልብ ነው፣ ሲቀበል ግን ቃልንና እስትንፋስን ይወስዳል። ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃል ሲሆን እርሱ ደግሞ ከአብ ልብን፣ ከመንፈስ ቅዱስ እስትፋስን ይወስዳል። መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ እስትንፋስ ሲሆን ከአብ ልብን፣ ከወልድ ቃልን ይወስዳል።
ወንጌላዊው ዮሐንስ፡- “በመጀመሪያው ወልድ ነበረ” ሳይሆን “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” በማለት መግለጥ የጀመረው በብዙ ምክንያቶች ነው /ዮሐ. 1፡1/። ወልድ ማለት ልጅ ማለት ነው። ልጆች የሚባሉ ብዙ ናቸው። አዳም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሏል /ሉቃ. 3፡38/፣ የሴት ዘሮችም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል /ዘፍ. 6፡2/። መላእክትም ልጆች ተብለዋል /ኢዮብ. 1፡6/። ወልድ ወይም ልጅ የሚባለው አጠራር አሻሚ እንዳይሆን “ቃል” በሚለው ገለጠ። ያ ቃልም አካላዊ እንደሆነ ከእኛ ውስጥ ከሚወጣው ቃል የተለየ እንደሆነ ይገልጣል። ይህን ወደ ኋላ እናየዋለን። የእኛ ቃል ዝርው ብትን ሲሆን የእርሱ ቃልነት ግን አካል ያለው ነው። ቃል በሚል የገለጠበት ሁለተኛው ምክንያት “መለኮት ሥጋ ሆነ” ቢል መለኮት ሦስቱም የሥላሴ አካላት የሚጠሩበት የአንድነት ስማቸው ነው። ሥላሴ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ በተለየ አካሉ በኩነት ስሙ “ቃል ሥጋ ሆነ” አለ /ዮሐ. 1፡14/። አብ ልብ የተባለበት ምክንያቱ ወልድ ቃል መባሉ ነው። ልብ የሌለው ቃል የለምና።
“ቃል” የሚለው አሁንም በመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት ነገሮችን ይገልጣል። አካላዊ ቃልን “ሎጎስ” ሲለው የተጻፈው ቃል ደግሞ በዕብራይስጡ “ዳቫር” ይባላል። የተጻፈውን ቃል ስንተነትን የሚመጣው መገለጥ ደግሞ “ሬማ” ይባላል። ዮሐንስ እየተናገረ ያለው ስለ አካላዊ ቃል ስለ ሎጎስ ነው። ሎጎስ በጥንታውያን ግሪኮች ዓለም የተፈጠረበት ምክንያትና የሚታየው ፍጥረት ከማይታየው ዓለም ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት መስመር እንደሆነ ይታሰባል። ይህ ሎጎስም አይሁዳውያን ሲቀበሉት መጽሐፋዊ አደረጉትና በብሉይ ኪዳን ዘመን የተገለጠውን፣ አርአያው የመልአክ፣ ድምፁ የአምላክ የሆነው አጋርን በምድረ በዳ፣ ሙሴን በኮሬብ ያናገረው ነው ብለው መተንተን ጀመሩ /ዘፍ. 16፡7፤ ዘፀ. 3፡2/። ስለዚህ ዮሐንስ መላው ዓለም በሚሰማው ቋንቋ ያ “ሎጎስ” ሥጋ የለበሰው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ይገልጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ፣ አካላዊና መለኮታዊ ነው።
ክብር ምስጋና ለጌትነቱ ይሁን።