የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 14

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ የካቲት 10/2008 ዓ.ም.
“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” /ዮሐ. 1፡1/

ወንጌላዊው ዮሐንስ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” በማለት የቃልን ዘላለማዊ ህልውና ይናገራል። ከሁሉ የሚቀድመው ህልውናን መቀበል ነው። ያ ህልውና ደግሞ ከመቼና ከየት ልዩ ነው። የማይመረመር ህልውና፣ ጥያቄ የማይነሣበት ማንነት ነው። ይህ መጀመሪያነት ለመጀመሪያዎች ሁሉ መገኘትን የሰጠ መጀመሪያ ነው። ራሱ ቃለ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ” /ራእ. 1፡17/ በማለት ለዚህ ወንጌላዊ በራእይ ተናግሯል። ከአልፋ በፊት ፊደል፣ ከኦሜጋም በኋላ ፊደል እንደሌለ ከእርሱ በፊት የነበረ፣ እርሱንም አስረጅቶ የሚናገር ማንም የለም። እርሱ ግን በፈቀደ ጊዜ መጀመሪያነትን ይሰጣል፣ በፈረደ ጊዜም መጨረሻነትን ይከፍላል። ባሕረ ጥበባት ነውና በሽማግሌ፣ የማይደክም ብርቱ ነውና በጎበዝ ምሳሌ ቢታይም እርሱ እጅግ ያረጀ፣ እጅግ አዲስ የሆነ ነው። የወንጌላዊውን ፍርሃት የገሰጸው ፊተኛና ኋለኛ መሆኑን በመግለጥ ነው። የሰው ልጅ የመጀመርና የመፈጸም ፍርሃት አለበት። ይህን ፍርሃት የሚያስወግድ አልፋ ኦሜጋ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ወንጌላዊው ወልድን ቃል ብሎ መግለጡ ይደንቃል። ልዩ ሆኖ የሚታወቅበት ስሙ ነውና። በወልድነቱ ከአብ ጋር ብቻ ግንኙነት አለው። የአብ ልጅ እንጂ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ልጅ አይባልም። በቃልነቱ ግን የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ይባላል። በቃልነቱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከፍጥረት ጋር በፈጣሪነትና በአጽናኝነት ደግሞም በአስተዳዳሪነት ግንኙነት አለው። ሁሉ በእርሱ ሆኗልና /ዮሐ. 1፡3/። የዕብራውያን ፀሐፊ፡- “ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ” ይላል /ዕብ. 1፡3/። በቃልነቱ ዕለት ዕለት ከሥላሴ አካላት ጋር፣ ዕለት ዕለትም ከፍጥረተ ዓለሙ ጋር ግንኙነት አለው። አንድን ሰው አሳቡን የምናውቀው በቃሉ ነው። ቃሉ ማንነቱን ያብራራልናል። እንዲሁም አብን ያወቅነው በተረከው ቃሉ፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ. 1፡18/። ወንጌላዊው ቃል ብሎ መግለጡ በእውነት ድንቅ ነው። ቃል ከልብ ሳይለይ በቋንቋ ይገለጻል። ቃልና ቋንቋ ልዩነት አለው። ቃል ቋንቋ የለውም። በቋንቋ ግን ይገለጻል። ከልብ ላይ ያለው ቃል አፍ ላይ ሲደርስ በአማርኛ ወይም በኦሮምኛ ይገለጻል። ቃለ እግዚአብሔርም ከአብ ተገኝቶ ከአብ ጋር ሳይለይ ኖሮ በሥጋ መገለጥ በፈለገ ጊዜ ተገልጿል። ሥጋዌው ሰውን ያናገረበት ትልቅ ቋንቋ ነው።

ለምንስ ኢየሱስ ክርስቶስ አላለም? ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋዌ ስሙ ነው። መለኮትና ሰውነት ሲዋሐዱ የተሰየመ ስም ነው። ከሥጋዌ በፊት መለኮትም ሥጋም ለብቻ አልተጠሩበትም። ከተዋህዶ በኋላ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ መጠሪያ ስም ነው። ወንጌላዊው ከማይመረመረው ዘላለማዊ ልደት ወደሚያስደንቀው ሥጋዊ ልደት እየተረከ ነውና ቃል በማለት ተናገረ። ሦስቱም ወንጌላውያን ከሥጋ ልደቱና ከጥምቀቱ ሲጀምሩ ዮሐንስ ብቻ ከዘላለማዊ ልደቱ ይጀምራል። ቃል ከልብ ሲወጣ ከልብ ሳይለይ ነው። እንዲሁም የወልድ ልደት ከአብ ያለ ተከፍሎ ወይም ያለ መለየት ነው። አንድ ልጅ ከወላጁ ከተወለደ በኋላ በራሱ ይኖራል። ይህ ልደት መከፈል ያለው ነው። የወልድ ልደት ግን ያለ መለየት ነው። ከቤተ ልሔም በፊት ህልውና የለውም የሚሉ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” በሚለው ይረታሉ።
   “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” የሚለው የወንጌላዊው ሁለተኛው አስደናቂ ገለጻ ነው። ቃል በልብ ውስጥ ህልው ሆኖ ይኖራል። ቃል የተባለው ወልድም በአብ ውስጥ ህልው ሆኖ ይኖራል። በአብና በወልድ መካከል ጽኑ ኅብረትና ፍቅር አለ። ቃል ያለ ልብ እንደማይኖር ወልድም ያለ አብ አልነበረም፣ ቃል የሌለው ልብ እንደሌለ አብም ያለ ወልድ አልኖረም። ልብና ቃል እኩል እንደሆኑ አብና ወልድም በእኩያነት አብረው ይኖራሉ። አባትና ልጅ መባል በሰው ዓለም መቀዳደምን ያመለክታል። በሥላሴ መንግሥት ግን መተካከልን ያመለክታል። “ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ”ሲል የቃልን አካላዊነት እየገለጸ ነው። የእኛ ቃል በአካላችን ውስጥ ያለ ረቂቅ፣ ብትን ነው። የአብ ቃል የሆነው ወልድ ግን በአካሉ ምልዐት ከአብ አጠገብ ያለ ነው። በዚህም ገለጻ ቃል በተለየ አካሉ የሚኖር መሆኑን ይገልጻል። እግዚአብሔር አንድ አካል ነው የሚሉ ሰባልዮሳውያን በዚህ አሳብ ይረታሉ። እነዚህ ሰባልዮሳውያን እግዚአብሔር አንድ አካል ነው። አንድ ሰው የተጸውኦ፣ የግብር፣ የቅጽል ስም እንዳለው አንዱ ክርስቶስም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተብሏል ይላሉ። እነዚህ ሰባልዮሳውያን ወይም በዘመናችን የኦንሊ ጂሰስ እምነት ተከታዮች በዚህ በዮሐንስ ገለጻ ይረታሉ። አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ የክርስቶስ ሦስት መገለጫ ስሞች ናቸው ካሉ ኢየሱስ እኔ ልጅ ነኝ ብሏል። ልጅ ካለ አባት በግድ ይኖራል። ይህ ብቻ አይደለም እኔ ወደ አባቴ እሄዳለሁ ብሏል። ስለዚህ እኔ ወደ ራሴ እሄዳለሁ ማለቱ ነው? በሦስት አካላት በአንድ መለኮት እናምናለን። የክርስቲያን ዓለም ተብሎ የሚጠራም በሥላሴ የሚያምን ነው።

ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ከአብ ሳይለይ ነው። አብ መባል ኖሮ ኖሮ የመጣ ስም አይደለም። ወልድ መባልም ኋላ የተገኘ አይደለም። ከዘላለም የነበረ ነው። ቃል የአብ ባሕርያዊ ቃሉ ነው። ከአካሉ የተገኘ እኩያው ነው። አርዮሳውያን ቃልን ፈጥሮ በቃል መዶሻነት ዓለምን ፈጠረበት ይላሉ። ዘመን ለሌለው ቃል ዘመን ይሰጡታል። ይህ ግን “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” በሚለው ይፈርሳል። ደግሞም ቃል የአብ ፍጡር ከሆነ ዓለምም ደግሞ በቃል ከተፈጠረ ይህ ዓለም የፍጡር ፍጡር መሆኑ ነው። አብስ ባልፈጠረው ዓለም እንዴት ፈጣሪ ይባላል? ነቢዩ፡- “በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ” ይላል /መዝ. 134፡6/። ይህ ፈቃድ ይህ ውድ የአብ ነው። አብ ልብ ነውና። ወልድ የአብ ባሕርያዊ ቃሉ ካልሆነ አብ ፈጣሪ ሊባል አይችልም። ወልድ ግን የባሕርይ ቃሉ ስለሆነ በቀጥታ መስመር ፈጣሪ ተብሏል። ዳግመኛም በመዝሙር 148፡5 ላይ፡- “እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት” በማለት ስለ ወልድ ፈጣሪነት ይናገራል። አንድ ፈጣሪ ለማለት ወልድ የአብ ባሕርያዊ ቃሉ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ወልድን ዝቅ ማድረግ አብን ዝቅ ማድረግ ነው።

     ራሱ ጌታችንም፡- “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል” ብሏል /ዮሐ. 14፡10/። አብ በወልድ አለ፣ ወልድም በአብ ውስጥ አለ። ወልድ በቃልነቱ የሚናገረው ልቡ ከሆነው ከአብ ወስዶ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ የቃልን ዘላለማዊነት ከገለጠ በኋላ አካላዊነቱንም ገልጧል።

ምስጋና ለማይደፈረው የመለኮት ግርማ ይሁን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ