የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” /ዮሐ. 1፡1/

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ የካቲት 12/2008 ዓ.ም.
 
ወንጌላዊው የቃልን ዘላለማዊነትና አካላዊነት ከገለጠ በኋላ ቃልም እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል። የቃልን ህልውና ካስረዳ በኋላ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ በማለት አካላዊ መሆኑን ገለጠ። በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው በጥገኝነት ነው? መላእክትም በእግዚአብሔር ዘንድ አሉ። ሎሌም በጌታው ዘንድ ይኖራል። ወልድ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው በእኩያነት በእግዚአብሔርነት ነው። ቃል የተባለው ወልድ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔርነት የባሕርይ ገንዘቡ እንጂ በሽልማት ያገኘው ሀብቱ አይደለም። አርዮሳውያን እንደሚገልጡትም ትንሹ እግዚአብሔር ወይም በመለኮቱ ፍጡር አይደለም። እርሱ ከጊዜ በፊት የነበረ ዘላለማዊ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የቃል ዘላለማዊነት የተገለጠው፡-
1-  አብን የሚያውቅና የሚተርክ በመሆኑ፡- እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ብቻ ይታወቃል። እግዚአብሔርም ራሱን ያውቃል። እግዚአብሔር ማለት ያወቅነው ያህል አይደለም፣ ለማመን የሚበቃን እውቀት በልካችን ተገልጦልናል። እግዚአብሔር ግን ያወቅነው ብቻ አይደለም። እግዚአብሔር ራሱን በብዙ መንገዶች ቢገልጥም በልጁ ግን እንደ ተገለጠው አልተገለጠም። ልጁ የአስተርእዮ/የመገለጥ/ ታላቅነትና ፍጻሜ የሆነው ለዚህ ነው። ልጁ የማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው /ቆላ. 1፡15/። የክብሩ ነፀብራቅና የባሕርዩ ምሳሌ ነው /ዕብ. 1፡3/። የመጨረሻው መገለጥ ነው /ዕብ. 1፡2/። መልእክት ይዞ የመጣ ሳይሆን ራሱ መልእክት ነው። ዮሐንስም፡- “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” ብሏል /ዮሐ.1፡18/
2-  አብን በክብር የሚተካከል በመሆኑ፡- ወልድን ማየት አብን ማየት ነው። ሥጋ በለበሰው ወልድ ሥጋ ያለበሱትን አብና መንፈስ ቅዱስን አይተናል። ለምን ስንል? አብ ባለበት ህልውና፣ መገኘት፣ አካልና ክብር ወልድም ስላለ ነው። እርሱ ራሱ፡- “እኔና አብ አንድ ነን”ብሏል /ዮሐ. 10፡30/። ዳግመኛም፡- “እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?” ብሏል /ዮሐ. 14፡9/።
3-  ተአምራቱና ሠራሄ ሕግ መሆኑ እግዚአብሔርነቱን ገልጧል፡- ተአምራቱ ሁሉ ምልክት ተብለው ተጠቅሰዋል። ምልክትነታቸውም ወደ ወልድ የሚያደርስና የእርሱን አምላክነት የሚያስረዱ ናቸው /ዮሐ. 2፡11/። ተአምራት እግዚአብሔር ለእኛ ያሰበው የመጨረሻው ግብ አይደለም። የሥጋ ፈውስም ወደ ነፍስ ፈውስ የሚያደርስ እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም። ጌታችን ተአምራትን ካደረገ በኋላ ሰዎች በእርሱ ያምኑ ነበር። የተአምራት ግብ እምነት ነው። አገልጋዮቹ ሁሉ በእርሱ ስም ተአምራት ያደርጋሉ፣ እርሱ ግን በሥልጣኑ ያደርጋል። ነቢያት ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ይላሉ። እርሱ ግን “እኔ ግን እላችኋለሁ” ይላል /ማቴ. 5፡21/። ለምን ሠራሄ ሕግ በመሆኑ ነው። ነቢያት ሁሉ መልእክቱን ይዘው መጥተዋል። እርሱ ግን ራሱ መልእክት ነው።
4-  በፈቃዱ የሞተና በሥልጣኑ ተነሣ በመሆኑ፡- ሞት ያልገዛው ከመቃብር በላይ የገነነ ነው። የመታመን መብትን የሚወስድ ነው ለሚያምኑትም የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ ነው። የዘላለሙ ጌታ ስለሆነ ዘላለምን መስጠት ይችላል /ዮሐ. 2፡19፤10፡18፤ 3፡16፤ 17፡3፤ 20፡31/።
5-  እግዚአብሔር ፈቃዱን ፍቅሩንና የዘላለም አሳቡን የገለጠበት ቃሉ ነው፡- የዘላለም ሕይወትን መስጠት የሚችል ሰዎችንም ወደ ራሱ የሚጠራ የሕይወት አድራሻ ነው። የእርሱ መጠጊያነትም አይደፈርም። ወደ እርሱ የመጣውን ማንም ወደ ደጅ አያወጣም። እርሱ እያንዳንዱ ቃሉና እንቅስቃሴው ከአብ ጋር የተገናኘ መሆኑን ተናግሯል /ዮሐ. 5፡30፤7፡17፤8፡28 ቁ. 42፤12፡49፤ 14፡10/።
6-  እርሱ የሕይወትና የእውነት መሠረት ነው፡- በማንም የማይደገፍ ህልውና አለው። ፍጥረትን ግን ደግፎ የያዘው እርሱ ነው። እርሱ ያለ እኛ ይኖራል እኛ ግን ያለ እርሱ አንኖርም። የእውነት መሠረትም ነው። ብዙ እውነቶች በዓለም ላይ አሉ። የሕይወት እውነት፣ ብርሃንነቱ የማይጨልም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለሚያምኑት ሁለት ትንሣኤን መስጠት ይችላል። ዛሬ ትንሣኤ ልቡናን ሰጥቶ በልጅነት ያከብራል። በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሥቶ በዘላለም ሕይወት ያከብራል። ይህን ሊያደርግ የተቻለው እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው /ዮሐ. 1፡4-5፤ 14፡6፤ 8፡12፤ 5፡25-29/።
  
7-  የጊዜ ባለቤት ነው፡- በጊዜ ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ጊዜ ያሳልፈው ነበረ። ጊዜ የማይጫነው ኃያል ነው። መጻሕፍትን ያተመ ነው ወይም እውነት ያሰኘ ነው /ዮሐ. 5፡39/። የመጻሕፍት ራስ ወይም ርእስ እርሱ ነው /መዝ. 39፡7/። በእርሱ ሰው መሆን ብሉይ ኪዳን ተአማኒነትን አግኝቷል። ነቢያት ስለ እርሱ ቢናገሩ ነቢያት ተብለዋል። ሐዋርያት ስለ እርሱ ቢመሰክሩ ሐዋርያት ተብለዋል። ሁሉ በእርሱ ይወደዳሉ፣ እርሱ ግን ስለ ራሱ ይወደዳል።
 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት ይመሰክራሉ። እነዚህ መጻሕፍት መለኮታዊ ስምንና ክብርን የወረሰ መሆኑን ይናገራሉ /ዕብ. 1፡4/። እግዚአብሔርን አባቴ በማለቱ እኩያነቱን ገለጠ /ዮሐ. 5፡18፤10፡33/። በብሉይ ኪዳን ዘመን ያህዌ ተብለው የተነገሩ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ወይም ጌታ ተብለው ተጠቅሰዋል /ኢዩ. 2፡32 እና የሐዋ. 2፡21/። በብሉይ ኪዳን ዘመን ፊተኛና ኋለኛ መባል የእግዚአብሔር ስም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ አልፋ ኦሜጋ ነኝ ብሏል /ኢሳ.44፡6፤ ራእ.1፡17/። የተስፋ ፍጻሜ፣ የአዲሱ ኪዳን መሥራች፣ የመዳን ራስ መሆኑን ይገልጣሉ። በምድር ላይ እንደ ሰው ቢመላለስም እንደ እግዚአብሔርነቱ ሠርቷል። አሁንም የቀረልን ተስፋ፣ የምንጠብቀው ሙሽራችን ነው።
 ወንጌላዊው፡- “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” አለ። “ነበረ” የሚለው ቃል ያለፈ ታሪክን የሚገልጥ አይደለም። ነበረ ሲል ያልነበረበት ጊዜ አለመኖሩን ለመግለጥ ነው። እግዚአብሔር የሚለው ስም ባሕርያዊ ስም ነው። ሦስቱም የሥላሴ አካላት በአንድነት የሚጠሩበት ስማቸው ነው። እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብንልም ሦስት እግዚአብሔር ለማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚለው ስም በአንድነት የሚጠሩበት ስም ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር የአንድነቱ ስሞች፡- ያህዌ፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ፣ አምላክ፣ መለኮት… ናቸው። የሦስትነቱ ስሞች የሚባሉት የአካላት ስሞች አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ። የግብር ስሞች፡- ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ይባላሉ። የኩነት ስሞች፡- ልብ፣ ቃል፣ እስትፋስ ይባላሉ። የምናመልከው አምላክ በአካላት ልዩ በመለኮት ግን አንድ ነው። እግዚአብሔር የሚለው ስምም የአንድነት ስም ነውና ሦስቱም አካላት ይጠሩበታል። የሦስትነት ስም ለየብቻ የሚጠሩበትና የሚታወቁበት ሲሆን የአንድነት ስም የሚባሉት ግን ሦስቱም አካላት በእኩልነት የሚጠሩበት ስም ነው። ለምሳሌ እኛ ሰው መባልን ሁላችን የምንጠራበት ስም ሲሆን አበበ፣ አየለ መባል ግን በግለሰብነታችን የምንጠራበት ስም ነው። ዶክተር፣ ኢንጂነር ደግሞ በሙያችን የምንጠራበት ስም ነው።
ቃል እግዚአብሔር ነው። ሁሉን ያስገኘ ፈጣሪ፣ ስግደትን የተቀበለ፣ መዳንን የፈጸመ፣ በሁሉ ሊፈርድ ሥልጣን ያለው ነው።
“በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ”  /ራእ. 5፡12/። እኛም አሜን እንላለን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ