የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ የካቲት 14/2008 ዓ.ም.
ቅዱስ አትናቴዎስ፡- “የእግዚአብሔር ቃል እኛን ለመፍጠር የተፈጠረ አይደለም። እኛ በእርሱ ተፈጠርን እንጂ በእርሱ ሁሉ ተፈጠረ ለእኛ ለድኩማን መፈጠሪያ እንዲሆን ልዑሉንና ኃያሉን እንደ አገልግሎት መሣሪያ ተፈጠረ ብሎ ማውራት ከደካማ አስተሳሰብ የተገኘ ነው። ዓለምን እንደ ፈጠረ አያጠራጥርም። ቃል ምንጊዜም ነበርና፤ ምን ጊዜም ባሕርያዊ ነው፤ በእርግጥም ያለ ቃል ምንም አልተፈጠረም። ያለ እጅ ምንም መሥራት እንደማይቻል እጁ ይባላልና /መዝ. 143፡7/።
አብ በወልድ ዓለምን ፈጠረ። በእጅ ጥልፍ እንደ መጥለፍ፣ ሥዕል እንደ መሣል ነው። እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” አለ። ቃሉን ሰምቶ ትእዛዙን ሊፈጽም የሚሮጥ ተወራጅ አሽከር ነበር ማለት አይደለም። ይህ በሰዎች ዘንድ ባሕርይ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ራሱ ፈጣሪ ነው። የአብ ፈቃድ እርሱ ራሱ ነው።…እግዚአብሔር ራሱ ዓለምን ፈጠረ እንጂ ሌላ የሚፈጥር አላስፈለገውም። እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠር እስካልቻለ ደርሶ ደካማ ወይም ዓለምን ለመፍጠር እስካለመፍቀድ ደርሶ ትዕቢተኛ አይደለም። በማለት እግዚአብሔር ለፍጥረቱ እንደሚያስብና ካለመኖርም ወደ መኖር እንዳመጣው ያስተምራል።”
ወንጌላዊው ዮሐንስ በአጭር ዐረፍተ ነገሮች የዘመናትን ስህተት እየናደ ነው። የእውነት ቃል ዝርዝር የለውም። እውነት ነውና ዝርዝር አያስፈልገውም። ሰዎች እግዚአብሔርን ለመሳደብ መቶ ገጽ ይጽፋሉ። ውሸት ነውና ብዙ ማውራት ጠይቋቸው ነው። ዮሐንስ ግን፡- “ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በማለት እንደገና አጽንኦት ይሰጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተደገመ ነገር ሲገጥመን ለማጽናት ነው። “አብርሃም አብርሃም” ሲል “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ሲል ቀጥሎ ያለው ጽኑ መልእክት ነው ማለት ነው። ዮሐንስም ከቃል ዘላለማዊነት ይልቅ አካላዊነቱንና ፈጣሪነቱን ደግሞ ይናገራል። በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ የሚለው ኅብረቱን የሚያመለክት ነው። የወልድ ጸዓት ወይም መውጣት ቃል ከልብ እንደሚወጣ ነው። የእኛ ቃል ከአካል ውስጥ የሚወጣ አካል የለሽ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ወልድ ግን አካላዊ ነው። እኛ ልጅ ስንወልድ አካል አለው፣ አካሉ ግን መለየት ስለሚገጥመው በራሱ ይኖራል እንጂ የእኛ ጥገኛ አይደለም። ቃል ግን ከአብ ሲወለድ ያለተከፍሎ /ያለመለየት/ ነው። ስለዚህ ምድራዊ ልደት ምሳሌ ለማይሆነው ለወልድ ተወላዲነት፣ ሰብአዊ ቃል ምሳሌ ለማይሆነው ለቃል ፀዓት/መውጣት/ ምስጋና ልናቀርብ ይገባናል።
ሠለስቱ ምእት/318ቱ ሊቃውንት/ በጸሎተ ሃይማኖት፣ በታላቁ የኒቂያ የሃይማኖት አንቀጽና አዋጅ፡- “ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋህድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠረ ዓለም ብርሃን ዘእም ብርሃን አምላክ ዘእም አምላክ ዘበአማን፡- ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ አንድ የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በአየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ።” በማለት የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
እርሱ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው። ከብርሃን ብርሃን ቢቀዳ ከብርሃን ሳይለይ ያው ብርሃን ተብሎ ነው። ቃልም ከአብ ሲወልድ ከአብ ሳይለይ የአብን ስምና ክብር ወርሶ ነው። ከውሃ ውሃ ቢቀዳ ያው ውሃ ነው። እርሱም ከብርሃን አብ የተገኘ ብርሃን ነው። ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ ብለዋል። ሐሰተኛ አማልክት አሉና እውነተኛ አሉ። ከሰው፣ ሰው እንዲገኝ ከአምላክም አምላክ ተገኝቷል። 318ቱ ሊቃውንት ይህን ቃል የወሰዱት “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ” ከሚለው ሐዋርያዊ ቃል ነው/ዕብ. 1፡3/።። ልጅ መልክን ይወርሳል፣ ባሕርይን ይካፈላል። አንዳንድ ልጅ መልኩ ላይመስል ይችላል፣ ባሕርዩ ግን ግድ የአባቱ ነው። ወልድ ግን አባቱን በመልክ የሚመስል፣ በባሕርይ የሚተካከል ነው። ልጅ በመወለዱ የዘመንና የክብር ማነስ አለው። ሰው በመሆኑ ግን እኩል ነው። አባትና ልጅ በሰውነት አይበላለጡም። የባሕርይ እኩያነት ማለት ይህ ነው። ወልድ ግን በመወለዱ ከአብ አልተከተለም። እርሱ ቀዳማዊ ነው። ከአምላክ ተገኝቷልና አምላክ ነው። ሁሉን ወራሽ ተብሏል /ዕብ. 1፡2/። ልጅ አባቱ ያፈራውን ሁሉ ሊወርስ ይችላል። ከመወለዱ በፊትና በኋላ ያለውን ይወርሳል። ወልድ ግን የፈጠረው እርሱ ነውና ወራሽነቱ ከምድራዊ ወራሽ ልዩ ነው።
ለፍጥረታት መጀመሪያቸው ዕለተ እሁድ ናት። የመጀመሪያ ቀን የተባለችው ለዚህ ነው። እሑድ አሐደ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን አንድ ማለት ነው። የፍጥረታት ጥንት እሑድ ስትሆን ለቃል ግን ጥንት ወይም መነሻ የለውም። ለቃል የተገለጠው መጀመሪያነት ዘላለማዊነት ነው። ቃል በተለየ አካሉ ከአብ ጋር ነበረ፣ በቃልነቱ ከዊን/ኋኝነት/ ደግሞ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ህልው ሆኖ ይኖራል። ዮሐንስ ቃል በአብ ህልው መሆኑን ደግሞ ለምን ሊነግረን ፈለገ? የቃልን አካላዊነትና ድርሻ መግለጥ ዘላለማዊነቱንና አምላክነቱን ለመግለጥ ስለሚረዳ ነው። አካላዊነቱን ማመን ህልውናውን መቀበል ነው። አካል የሌለው ከአካላዊ አብ ጋር እኩል ሊሆን አይችልና አካላዊነቱን ጠቅሶ እግዚአብሔር ነው ይላል።
እጅ በክንድ ላይ፣ ክንድ በአካል ላይ አለ። እጅ በሠራው ክንድ፣ ክንድ በሠራው አካል አለበት። በወልድ ቃልነት በተፈጠረው ዓለምም አብ ፈጣሪ የተባለው እጁ፣ ክንዱ ስለሆነ ነው። ክንድ ከአካል ሳይለይ ሥራ እንደሚሠራ ቃልም ከአብ ሳይለይ ይህን ዓለም ፈጥሯል። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አንድ ፈጣሪ የሚያሰኝ ይህ ነው። ቃል የአብ ባሕርያዊ ቃሉ ባይሆን ኖሮ በወልድ ቃልነት በተከናወነው ዓለም አብ ፈጣሪ ለመባል ባልበቃ ነበር። ይህን አብ ፈጠረ ይህኛውን ወልድ ፈጠረ የማይባለው እግዚአብሔር አንድ ፈጣሪ፣ ቃልም የአብ ኃይሉና ክንዱ ስለሆነ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም፡- “ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው” በማለት ስለ ክርስቶስ ይናገራል/ኢሳ. 59፡16/።
ኃይሉ በሆነው ቃሉ ያነሣን፣ እጁ በሆነው ልጁ የቸረን፣ ክንዱ በሆነው ወዳጁ የታደገን ለዘላለም ይመስገን።