የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ የካቲት 16/2008 ዓ.ም.
ወንጌላዊው ቃል እግዚአብሔር መሆኑን ገልጧል። አሁንም በአጽንኦት ቃል የሁሉም ፈጣሪ መሆኑን ይናገራል። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” /ዮሐ. 1፡3/። ዮሐንስ ስም ሳይጠቅስ በየዘመናት የሚነሡ መናፍቃንንና ትምህርታቸውን ይገስጻል። መናፍቅ፣ መንፈቅ ከሚለው ቃል የወጣ ሲሆን ግማሽ ማለት ነው። ከፊል እውቀትና ከፊል እምነት ያለው፣ ጨርሶ ያላወቀ፣ ጨርሶ ያልካደ፣ በሙሉ የማያምን፣ በሙሉ የማይክድ፣ ለብ እንዳለ ውሃ የሚንቀዋለል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለአመሉ የሚጠቅስ፣ ለመማር የማይሻ፣ በቃላት ድርደራ አሳምናለሁ ብሎ የሚሰማራ፣ ሥልጣንና የገንዘብ ጥማት በል የሚለው፣ የሰውን ሥጋዊ ቀልብ በሚስብ ነገር መግለጥ የሚችል ማለት ነው። ዮሐንስ በአጭር ቃላት የዘመናትን ስህተት ንዷል። የጥንቱ አርዮስና የዛሬ የጂሖቫ ምስክሮች የሚረቱበት አንቀጽ ይህ ነው። አርዮስ የሚታወቅበት ኑፋቄው ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው የሚል ነው። አርዮስን እንቅፋት የሆነበት ቃል ሰው ሆኖ የሠራው የትሕትና ሥራ አይደለም። አርዮስ ወልድን ፈጥሮ ፈጠረበት ብሏል። የአብ በኩር ፍጡር ይለዋል። ለዚህም ምሳሌ የሚያደርገው አንጥረኛ መዶሻውን፣ ሸክላ ሠሪ መደቧን አስቀድማ እንድትሠራ እንዲሁም አብ ወልድን መሣሪያ አድርጎ ፈጥሮ ፈጠረበት ብሏል። ወልድንም እንደ ጸጋ አምላክ ያየዋል። በመቀጠል ስግደት ይገባዋል የሚል የተሳከረ አሳብ ያቀርባል። ወልድ ፍጡር ነው ብሎ ስግደት ይገባዋል የሚል ክርስቲያን አይደለም በማለት አትናቴዎስ ይረታዋል። ክርስቲያን ለፍጡር የአምልኮ ስግደት አያቀርብምና። ስለዚህ አርዮስ በገዛ ቃሉ ጣኦታዊ መሆኑን መስክሯል። ወልድን እንደ ጸጋ ልጅና አምላክ በማየቱ ከእኛ ልጅነት ጋር በማመሳሰሉ አትናቴዎስ እንዲህ ሲል መልሷል፡-
“ክርስቶስ በሥጋ ዘመኑ በሥጋ ርስት በሥጋዌ ሥርዓት ሐዋርያትንና የአዳም ልጆችን ወንድሞቼ ማለትን አያፍርም። የእግዚአብሔር ልጅ የአዳም ልጅ ሆኗልና። የአብ የባሕርይ ልጅነቱን በተናገረበት አንቀጽ ግን ራሱን ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር ቆጥሮ አልተናገረም። አባቴ ፣ አባታችሁ አለ እንጂ አባታችን አላለም። አብም ተቀዳሚ ተከታይ ለሌለው ለአንድ ልጁ አባትነቱን በመሰከረበት አንቀጽ በዮርዳኖስ ከዮሐንስ ጋር አዳብሎ አቀናጅቶ ወይም በደብረ ታቦር ከዮሐንስ ከያዕቆብና ከጴጥሮስ ጋር አዳብሎ ልጆቼ አላለም አጥርቶ ልጄ አለው እንጂ”/የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ112/። ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም ስለ ዳግም ልደት በተናገረበት አንቀጽና የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 3ን በተረጎመበት ድርሳኑ፡- “የክርስቶስ ልደት እንዲህ ከሆነ ከመንፈስ ከተወለዱት የእርሱ ብልጫ ምንድነው? እርሱስ እንዴት አንድያ ልጅ ሊባል ይችላል? እኔም ከእግዚአብሔር ተወልጃለሁ፤ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ግን አይደለም። ወልድ ግን ከአብ ባሕርይ ካልተወለደ ከእኛ በምን ይለያል? ከመንፈስ ቅዱስ ያንሳል ልንለው ነዋ! የእኛ ልደት በመንፈስ በጸጋ ነው” ብሏል።
አርዮስ መውለድና መፍጠር ሁለቱም ሞክሼ ቃላት ናቸው ብሏል። ፍጡር ነው ያለውን ወልድ መልሶ ልጅ ነው ይለዋል። ይህም የአብን አባትነቱ ከዘመን በኋላ የተገኘ ነው እንዲል አድርጎታል። 318ቱ ሊቃውንትና ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮስን በገዛ ቃሉ ረትተውታል። “እኛ የምንወልደውን አንፈጥረውም፣ የምንፈጥረውንም አንወልደውም”። በማለት ረትተውታል። ለምሳሌ ጠረጴዛ ብንሠራ ፈጠርነው እንጂ አልወለድነውም ማለት ነው። መውለድ ባሕርያዊ ተካፍሎ ነው። መፍጠር ግን ከባሕርያችን ውጭ ሙያ ነው። ቅዱስ አትናቴዎስ ዕብ 1፡3ን በመጥቀስ “የባሕርዩ ነፀብራቅ” የሚለውን ተርጉሟል፡- “የፀሐይ መኖር በፀዳል፣ የእሳት መኖር በነበልባል እንዲታወቅ አብን ያወቅነው በወልድ ነው። ፀዳል ከብርሃን እንደማይለይ ወልድ ከአብ፣ አብም ከወልድ አይለይም። ፀሐይና ፀዳል ሁለት ፀሐዮች እንደማይባሉ አብና ወልድም ሁለት አማልክት አይባሉም” በማለት መልሷል። ሌላው ወልድን ፍጡር ማለት መዳንን ይነካል። በፍጡር ዓለም አይድንምና በማለት አባቶች መልሰዋል። አባቶች ከመናፍቃን ጋር ባደረጉት ክርክር ድንበራቸው መዳን ነው። ለመዳን በማይጠቅምና መዳንን በሚነካ ነገር ጊዜ አላጠፉም። ይህ ነገር ለመዳን ምን ይጠቅማል? ይህ ነገር መዳንን ይነካልን? ይሉ ነበር።
ዮሐንስም የቃልን ፈጣሪነት በግልጽ አስቀምጧል፡- “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” /ዮሐ. 1፡3/። የፍጥረት መገኛ እርሱ ነው። አምላክነትን የተቀበለው ቢሆን ለእኛ ሕይወትን መስጠት እንዴት ይችላል? የተቀበለው ከሆነ እንዴት ይተርፈዋል? በማለት አባቶች መልሰዋል።
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” /ዮሐ. 1፡3/ የሚለው አሁንም የግኖስቲኮችን አስተሳሰብ የሚረታ ነው። ግኖስቲክስ ግኖሲስ /እውቀት/ ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ነው። ፍችውም አዋቂዎች ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች እምነትና እውቀትን በማወዳደር ለእውቀት ትልቅ ቦታ የሰጡ ሰዎች ናቸው። መዳንም በእውቀት ነው ብለው ያስባሉ። አስተሳሰባቸውም ቤተ ክርስቲያንን ሲያውክ ኖሯል። የግኖስቲኮች አንዱና የመጀመሪያው ኑፋቄ፡- “ሁለት አማልክት አሉ፣ አንዱ ልዑልና መልካም ሲሆን ሌላው ዝቅተኛና ክፉ ነው። ይህን የሚታየውን የክፋት ምንጭ የሆነውን ግዙፍ ዓለም የፈጠረ ዝቅተኛው አምላክ ነው። ደጉና ልዑሉ አምላክ የፈጠረው ረቂቁን ዓለም ነው” ይላሉ። እንደ እነርሱ አስተሳሰብ ብርሃንን የፈጠረ ደጉ አምላክ ሲሆን ጨለማን የፈጠረ ክፉውና ትንሹ አምላክ ነው። ሁሉ የሆነው ግን በወልድ ብቻ ከሆነ ሁለት አማልክት ሊኖሩ አይችሉም። ዓለም አንድ ፈጣሪ እንዳላት ራሷ ምስክር ናት። አንድ ዓለም ናትና። ሁለት አማልክት ቢኖሩ ሁለት ዓለም ይኖር ነበር። የአማልክትም ፉክክር ይታይ ነበር።እንዲሁም አማልክት የፈጠሯት ዓለም ብትሆን አማልክት በተጋጩ ቁጥር ዓለም ሰላም ታጣ ነበር። የተለያዩ አባላት ያሉባት ዓለም በሰላም የምትኖረው ፈጣሪ አንድ ስለሆነ ነው። ሰውም በአንድ አካል ላይ የተለያዩ ክፍሎች ሳሉት በሰላም በስምምነት የሚኖረው አንዱ እጅ ስላበጀው መሆኑን የእስክንድሪያው ትልቅ አባት አትናቴዎስ አስተምሯል።
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” /ዮሐ. 1፡3/።
ሁሉን ለፈጠረ እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።