የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይሸነፍ ብርሃን

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ የካቲት 26/2008 ዓ.ም.
“ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም” /ዮሐ.1፡5/፡፡
የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሔር መኖር የማይችል ፍጡር ነው፡፡ የእስትንፋሱ ምንጭ ራሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እግዚአብሔር የሕይወት መገኛ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግ ሲጀምር ሕይወትን ያገኛል፡፡ ያ ሕይወት እንደ እንስሳት የሚያንቀሳቅስና የሚያመርት ደመ ነፍሳዊ ሕይወት ሳይሆን ክብርን ለእግዚአብሔር የሚሰጥ፣ ሰዎችን የሚወድ፣ ሰማይን የሚናፍቅ ሕይወት ነው፡፡ ብርሃን ባለበት ጨለማ እንደሌለ እግዚአብሔር ባለበትም ሞት የለም፡፡ ማርታ፡- ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” ብላለች /ዮሐ. 11፡21/፡፡ አንተ ባለህበት ሞት የለም ማለቷ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሕይወት ብቻ ሳይሆን የብርሃንም ምንጭ ነው፡፡ ብርሃን የሚያነቃ ነው፣ ብርሃን ከመጣ በኋላ መተኛት ያቅተናልና፡፡ ብርሃን የሚያሰማራ ነው፣ ብርሃን ከመጣ በኋላ ወደ ተግባራችን እንሮጣለንና፡፡ ብርሃን የሚያገናኝ ነው፣ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም በሩን ይከፍታልና፡፡
የዛሬዋን ሕይወት ጣዕም የሚሰጣት የነገ ግቧ መታወቁ ነው፡፡ የነገ ግቡን ያላወቀ ተረጋግቶ መቀመጥ አይችልም፡፡ መድረሻውን የማያውቅ መንገደኛ ሳይሆን ተንከራታች ነው፡፡ በክርስቶስ ስናምን የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠን መድረሻችንን እንድናውቅ ነው /ዮሐ. 3፡16/፡፡ መድረሻን ማወቅ ይህንንና ያንን ለምን እንደምናደርግ ምክንያታዊ ያደርገናል፡፡ ያለ ሕይወት መራመድ፣ ያለ ብርሃን ግብን ማየት አይቻልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የሕይወት ብርሃን ነው፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ እንድንገኝ ብቻ ሳይሆን ሰማይ የምንደርስበትን ካርታም ሰጥቶናል፡፡ ሕይወት መገኘት ወይም ህልውና ብቻ ሳይሆን ጉዞም ናት፡፡ እግዚአብሔር የሚሰጠን ሕይወት ብርሃን ያለው ነው፡፡ በብርሃን የምናገኛቸውን ነገሮች እንደ ቀላል ነው የምንቆጥራቸው፡፡ ብርሃን ባይኖር ብለን ብናስብ ይጨልምብናል፡፡ ብርሃን ባይኖር የሆነው ሁሉ አይሆንም ነበር፡፡ ዓይናችን ያለ ብርሃን ለጌጥነትም አይሆንም፡፡ በዓለም ላይ በጸጥታ የሚጮህ ነገር ማንበብና መጻፍ ነው፡፡ ብርሃን ባይኖር ይህ የጸጥታ ጩኸት አይኖርም ነበር፡፡
የዓይን ዋጋዋ ብርሃን ነው፡፡ ዓይን ያለ ብርሃን ዋጋ የሌላት ፍጥረት ናት፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮች እንዲጠቅሙ ብርሃን ያስፈልጋል፡፡ ልብሳችንን መታጠቅ የምንፈልገውና ራቁትነትን መቀበል የሚያቅተን ብርሃን ሲመጣ ነው፡፡ ያለ ብርሃን ነውርንና ክብርን መለየት አንችልም፡፡ ብርሃን ሲመጣ ስሜታችንን የት መግለጥ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ብርሃን ሲመጣ ከማን ጋር ነበርኩ? የምንለው ለዚህ ነው፡፡ “እናንተ የምታዩኝ እኔ የማላያችሁ” የሚለው ግጥም ብርሃን ሲመጣ ያበቃል፡፡ የገጠመን ነገር አደጋ ሳይሆን ዓለምን ያወቅንበት ነው፡፡ የሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ያወቅንበት ቀን ዕለተ ብርሃን ነው፡፡  የመኪና መንቀሳቀሱ ሕይወት፣ መሪው ግን ብርሃን ነው፡፡ መኪና ያለ ብርሃን ልንቀሳቀስ ቢል አደጋ ነው የሚገጥመው፡፡
ብርሃን ምሪት ነው፡፡ ሰው ጠንቋይ ቤት የሚሄደው ምሪት ፍለጋ ነው፡፡ በድፍረት ለመነገድ፣ ለመማር… ይታየኛል የሚሉ ነቢያትን የሚፈልገው ለዚህ ነው፡፡ ብርሃን ስፍራችንን እንድንመዝን ያደርገናል፡፡
“ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም” ይላል /ዮሐ.1፡5/፡፡ ብርሃን ሲመጣ ጨለማ በየት በኩል ወጣ? የብርሃን መምጣት ጨለማን መድረሻ ያሳጣዋል፡፡ በእኛ ያለው ብርሃን መሆኑን የምናውቀው የጨለማው ጓዶች ሲቃወሙን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ብርሃን ግን የሚያሸንፍ እንጂ የሚሸነፍ አይደለም፡፡ ዛሬ ብዙ ጨለማዎችን እናያለን፡፡ የራስ ወዳድነት፣ የቡድንተኝነት፣ የቅንዓት… ጨለማን እናያለን፡፡ ቀጣዩ እያሳሰብንም እንዴት ይሆን? እያልን እንጨነቃለን፡፡ ደስ ይበለን የሚያሸንፈው ብርሃን ነው፡፡ መንፈሳዊ ጉዞአችንን የሰዎች ተቃውሞ፣ አገልግሎታችንን የሌሎች ነቀፋ እንዲያሰናክለው መፍቀድ የለብንም፡፡ የተቀበልነው ብርሃን የሚያሸንፍ እንጂ የሚሸነፍ አይደለም፡፡ ደግሞም ካልተመታ በቀር የሚጮህ የለምና ጨለማው ሲጮህ መበርታት እንጂ መበርገግ የለብንም፡፡
ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና  ይሁን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ