የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለሰው ሁሉ የሚያበራው

“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም” /ዮሐ. 1፡9-10/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በሥጋ በመጣበት ወቅት ብዙ አላሳይ ያሉ የሕይወት፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ጨለማዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙዎች በድህነት የሚማቅቁበት፣ በቅኝ ገዢዎች ክንድ የደቀቁበት፣ ሁሉ በሽተኛ ሆኖ የሚያቃስትበት፣ ኅሊና በጭንቀት የሚናጥበት፣ ነገ አልታይ ብሎት ትውልድ በቀቢፀ ተስፋ የሚንቀዋለልበት፣ ካህናት የወቅቱን ፖለቲካ የሚያጥኑበት፣ በአገር ሽማግሌ ጠፍቶ ሁሉም በራሱ መንገድ የሚነጉድበት፣ ጥቂተ ቀናተኞች አገራቸውን ነጻ ለማውጣት ወደ አርበኝነት የተሰማሩበት፣ ለሮማ መንግሥት አድረው ይሠሩ የነበሩት እንደ አገር ሻጭ የሚታዩበት፣ ዘረኝነት ነግሦ የወደቀን ለማንሣት እንኳ አንተ ሳምራዊ ነህ ወይስ አይሁዳዊ? የሚባልበት፣ አንዱን አምላክ በአንድ መቅደስ ለማምለክ ተቸግረው በገሪዛንና በኢየሩሳሌም መቅደሶች የሚሰገድበት፣ በእግዚአብሔር ስም ሰዎች የመለያየትና የስድብ ጥማቸውን የሚወጡበት፣ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ ሽማግሌዎች ያለ ጧሪ የቀሩበት፣…ዘመን ነበር፡፡ ጌታችን ወደዚህ ጥልቅ ጨለማ ብርሃን ሆኖ መምጣቱ ትክክል ነበር፡፡ እርሱ ለወቅቱ ሁኔታ መልስ በሚሰጥ ስምና ጠባዩ ይገለጣል፡፡ ስለዚህ ብርሃን ሆኖ መጣ፡፡ ተስፋ የራቀው፣  ቀኑ ማለፉን የተጠራጠረው፣ ራእይ አጥቶ የሚንቀዋለለው፣ ሁሉን ነገር ከዕለት ጉርሱ አንጻር የሚለካው ያ ዋስትና ያጣ ትውልድ ጌታችንን ሲያገኘው ያለይሉኝታ ተጣበቀው፡፡ እርሱም አዝኖላቸው በትምህርቱ ነፍሳቸውን በበረከቱ ረሀባቸውን መገበ፡፡
ከእስራኤል ውጭም ያለው ዓለም ዘመናዊነትን እንደ አምላክ ቆጥሮ የሁሉም ነገር መልስ ከፈላስፎች የሚገኝ መስሎት ጠፍቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የለሽነት ነግሦ በተቃራኒው ደግሞ ቄሣር ጌታ ነው ተብሎ ይሰገድለት ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ማምለክ ተስኗቸው የገዛ እውቀታቸውን የሚያመልኩ ሆኑ /ሮሜ. 1፡22-23/፡፡ እርካታ ቢስነት ስለበዛም ከአንዱ ፍልስፍና ወደ አንዱ ሲገላበጡ ይውሉ ነበር፡፡ ራስን መግዛት እየጠፋ ትውልዳቸው የምኞቱ ሎሌ ሆኖ ነበር፡፡ ጌታችን በሃይማኖት ካባና በፍልስፍና ወረት ተይዘው ከደስታና ከእርካታ ለራቁት ሕዝብ ብርሃን ሆኖ መጣ፡፡ እርሱ ገበሬ በመከር ደስ ከሚለው፣ ወታደርም በምርኮ ከሚያገኘው የላቀ ደስታ ሆኖ መጣ /ኢሳ. 9፡3-6/፡፡
“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ይላል፡፡ በሥጋ አሁን ቢመጣም ይህ ብርሃን ግን ተመላላሽ ብርሃን ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት የወጣችው ፀሐይ ትላንት ወጥታ ነበር፡፡ ዛሬም ግን ካለንበት ድረስ መጥታለች፡፡ ፀሐዩ ክርስቶስም በፍጥረት፣ በረድኤት፣ በተአምራት ሲመጣ ኖሮ አሁን ግን በሥጋ መጣ፡፡ ድሮ ፀሐይን ለማየት ቀና ማለት ያስፈልግ ነበር፡፡ አሁን ግን ፀሐዩ ጌታ በረት ተወልዷልና ዝቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሰብአ ሰገል ጥበብ፣ ሥልጣን፣ ገንዘብ ቢኖርም ዝቅ ማለት የተወለደውን ሕጻን ለማግኘት መስፈርት ነው፡፡ እርሱ ሊያከብረን ዝቅ አለ፡፡ ሰማያዊ ሊያደርገን ምድራዊ ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ሊያደርገን የሰው ልጅ ሆነ፡፡ ትላንት እንዳልፈለገን አድርጎ ፈለገን፡፡ ሲያገኘንም አቅፎ ሳመን እንጂ አልወቀሰንም፡፡ ትላንት እንዳልመከረን አድርጎ ዛሬ መከረን እንጂ አልዘለፈንም፡፡ ትላንት እንዳልበደልነው አድርጎ ተቀበለን እንጂ “አንተ እኮ” “አንቺ እኮ” ብሎ ትላንትን አላነሣብንም፡፡ ለዛሬውም ጨለማ፣ አልታይ ላለን ጉዳይ መልሱ ብርሃን ክርስቶስ ነውና ወደ እርሱ በንስሐና በእምነት እንመለስ፡፡
ይህ ብርሃን ለሰው ሁሉ የሚያበራ ነው፡፡ ፍቅሩ በብርሃን ተመስሏል፡፡ ሁሉን የሚወድ ብርሃን፣ ፍቅር የሆነው አምላክ እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” /ማቴ. 5፡48/፡፡ ሰማዊ አባት ሁሉን አስተካክሎ በመውደድ ፍጹም ነው፡፡ ፀሐይ በድሃና በሀብታም፣ በጻድቃንና በኃጥአን ጣራ ላይ ትወጣለች፡፡ የፀሐይ ጌታ ክርስቶስም ወደ ሁሉ በፍቅር ብርሃኑ መጥቷል፡፡
አንተ እንዲሁ ወደድከን፡፡ እኛ ግን ብዙ ስለዋልክልን ወደድንህ፡፡ እስክንመጣ አልጠበቅህም፡፡ ካለንበት ውድቀት ሥር መጥተህ በፍቅር ድምፅ ተናገርከን፡፡ አብዝተህ ከተቀበልከው ይኸው ምስጋናችን፡፡ ሠርተህ ከተጠቀምክበት ይኸው ሰባራ ማንነታችን፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ