የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የልጅነት ሥልጣን

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ መጋቢት 21/2008 ዓ.ም.
“ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” /ዮሐ. 1፡12-13/፡፡
አንድ ሰው፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሕዝብ ታላቅ ጥያቄ ወይም ታላቅ መልስ ነው” ብሏል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄአችን ከሆነ ዕረፍት የለንም፣ መልሳችን ከሆነም መቅበዝበዝ የለብንም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መልሳችን ካልሆነ ጥያቄአችን እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ እርሱ ታላቅ የመዳን አንቀጽ ብቻ ሳይሆን የኵነኔም አንቀጽ ነው፡፡ ያመኑበት ሲድኑ ያላመኑበት ይኰነናሉ፡፡ በስሙ ወይም በማንነቱ በመሥዋዕትነቱ ያመኑ የልጅነት ሥልጣንን ያገኛሉ፡፡ የዘላለም ሕይወትን፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን፣ የእግዚአብሔርን ከለላ… ያገኛሉ አላለም፡፡ ልጅነትን ያገኛሉ ይላል፡፡ ልጅነት ሁሉን የሚጠቀልል ስለሆነ ነው፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ነንና፡፡ ይህ ልጅነት ሦስት ዓይነት ጠባይ እንዳለው ገጸ ንባቡ ያሳየናል፡-
1-  ሥልጣን አለው
2-  ስጦታ ነው
3-  ከሥጋ ልደት ልዩ ነው፡፡
1-ሥልጣንአለው
 “የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” ይላል፡፡ ይህ ልጅነት ተራ ልጅነት አይደለም፡፡ ሥልጣን ያለው ልጅነት ነው፡፡ በአገራችን “ልጅ እገሌ” የሚባል መጠሪያ እንሰማለን፡፡ ለምሳሌ ልጅ ኢያሱ እንላለን፡፡ ኢያሱ የአፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ ነው፡፡ ልጅ የሚለው መጠሪያ ከፊት ሲውል ያ ሰው ከንጉሣዊ ቤተሰብ እንደ ተወለደ ማሳያ ነው፡፡ አዝማደ መንግሥት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔርም የሰማይና የምድር ንጉሥ ነውና ከእርሱ የምንወለደው ልደት ልዑልና ልዕልት የሚያሰኝ ልደት ነው፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ስንወለድ ልዑላንና ልዕልቶች ሆነናል ማለት ነው፡፡
 በክርስቶስ ለሚያምኑ ኃይል ሳይሆን ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከኃይል ሥልጣን ይበልጣልና፡፡ በጎዳናው ላይ ትራፊኩ እጁን ወደ ላይ ሲያነሣ መኪናውም ሾፌሩም ይቆማሉ፡፡ በኃይል መኪናውና ሾፌሩ ይበልጣሉ፡፡ ከትራፊኩ እጅ ጀርባ ግን መኪናውንም ሾፌሩንም የሚገዛ ሥልጣን አለ፡፡ ብዙ ነገሮች ኃይለኛ ቢሆኑብን እንኳ እኛ ግን ሥልጣን አለን፡፡ በዚህ ሥልጣን ደዌያትና አጋንንት ይገዛሉ፡፡
2- ስጦታ ነው
 “የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸውይላል፡፡ ይህን ልጅነት በማመን እንጂ በጥረትና በብቃት ያገኘነው አይደለም፡፡ ስጦታ ነው፡፡ እኛ ሰዎችን በተወዳጀን ቁጥር ስጦታችን እየጨመረ ይመጣል፡፡ ፖስት ካርድ፣ ቀጥሎ ወርቅ… እያለ ያድጋል፡፡ እግዚአብሔር ግን በመጀመሪያዋ ቅጽበት የልጅነትን ስጦታ ይሰጠናል፡፡ እርሱ የመጨረሻውን ከመስጠት ይጀምራል፡፡ የመጨረሻውን ተቀብለናልና ደስ ይበለን፡፡ ከዚህ በኋላ ሚሊየን ዓመት ብንኖርና ሚሊየን ጊዜ ቢሰጠን ከተሰጠን አይበልጥም፡፡ የተሰጠን ልጅነት ነው፡፡ የመጨረሻውን ስለተቀበልን ዓለም ብታከብረን ብታዋርደን ሁለቱም አይገርመንም፡፡ የመጨረሻው የተከፈለውን ማንም ሊያነሣውና ሊጥለው አይችልም፡፡ ዋንጫውን ተቀብሎ የሚጫወት የለም፡፡ እኛ ግን ዋንጫውን ተቀብለን ሰዓቱ እስኪሞላ እንሮጣለን፡፡
 ልጅነት ዓለም ማያ ነው፡፡ ይህን ዓለም ያየነው ስለተወለድን ነው፡፡ ያኛውንም ዓለም የምናየው በመወለድ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልተወለደ ዓለም አያይምና፡፡ ይህ ዓለም ግዙፍ ነውና ግዙፍ ልደት አስፈለገ፤ ያኛው ዓለም ረቂቅ ነውና መንፈሳዊ ልደት አስፈለገ፡፡ የክርስቶስ ሁለተኛ ልደቱ የመጀመሪያውን ልደቱን ያሳያል እንዳልን የእኛም ዳግማዊ ልደት አስቀድሞ ስንፈጠር የተሰጠንን ያንን ልጅነት ያሳየናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ እቅድ ይዞ ወደ ዓለም አልመጣም፡፡ ከበደል በፊት ወደ ነበረው ማንነት ሊመልሰን መጥቷል፡፡ አዎ ይህ ልጅነት ስጦታ ነው፡፡ የመባል ልጅነት ነው እንጂ የባሕርይ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ልጅነት ግን የባሕርይ ነው፡፡ የእኛ ልጅነት የመባል፣ የሹመት መሆኑን፡- “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን” በማለት ተገልጧል /1ዮሐ. 3፡1/፡፡
3-  ከሥጋ ልደት ልዩ ነው
“እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” ይላል /ዮሐ. 1፡13/፡፡ ወንጌላዊው ይህን አሳብ መጥቀስ ለምን አስፈለገው? ስንል እስራኤል ከአብርሃም በመወለዳቸው ብቻ ቢያምኑም ባያምኑም የአብርሃም ልጆች ነን የሚል ትምክሕት ነበራቸው፡፡ እኛም ራሳችንን በሥጋ ከምናገኝበት ቤተሰብ ብናምንም ባናምንም በግድ ልጅ ነን፡፡ መንፈሳዊው ልደት ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በግድ የምንቀበለው ሳይሆን በእምነት የምንቀበለው ነው፡፡
በሥጋ ስንወለድ በዚያው ቅጽበት የተወለድንበት ቤተሰብ አባል እንሆናለን፡፡ በዚያው ቅጽበትም የዓለም አቀፉ የሰው ዘር አባል እንሆናለን፡፡ ስንወለድም በተወለድንበት አጥቢያና  በዓለም አቀፉ የክርስቶስ አካል ውስጥ አባል እንሆናለን፡፡ ይህ በቅጽበት የሚከናወን ተግባር ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ