የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ ልጅ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ሚያዝያ 1/2008 ዓ.ም.
 
     “አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን”
/ዮሐ. 1፡14/፡፡
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድ ልጅ ነው፡፡ በባሕርይ ልደቱ ቀዳሚም ተከታይም የለበትም፡፡ ወልድ ዋሕድ ማለት አንድ ልጅ ነው፡፡ ዮሐንስ አንድ ልጅ የሚለው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም የመጣውን ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ልጅና በማርያም ልጅ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ ነው፡፡ የማርያም ልጅም የአብ ልጅ ነው፡፡ ንስጥሮስ ለክርስቶስ ሁለት አካላትና ሁለት ባሕርያትን ሰጠ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ደግሞ ለክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ሰጡ፡፡ እርሱ ግን አንድ ልጅ ነው፡፡ ለአንዱ ልጅም ሁለትነት አይተረክለትም፡፡ ተዋህዶው መለወጥን፣ ኅድረትን፣ መቀላቀልን፣ መጠፋፋትን፣ መዳበልን፣ ምንታዌን/መንታነትን/፣ ፈረቃን፣ ሁለት ግብራትን፣ ሁለት ፈቃዳትን ያስቀረ ነው፡፡ ለአንዱ ክርስቶስ ሁለትነት መስጠት አብን ሁለት ልጆች አሉት ማለት ነው፡፡ በአንዱ ክርስቶስ አንዱ የሚሰገድለት አንዱ ስግደት አቅራቢ ሁለት ማንነቶች አሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሠርግ ቤት የሄደውና የቃናን ውሃ የለወጠው ማን ነው? መለኮት ከሆነ ሳይታጣ መሄድ አያስፈልገውም፡፡ ሥጋ ከሆነም ውኃን ወይን ማድረግ አይቻለውም፡፡ አንዱ ክርስቶስ ወደ ሠርግ ቤት ተጠራ፤ አንዱ ክርስቶስ ውኃውን ወይን አደረገ፡፡ መዳን የተፈጸመው በአንዱ ክርስቶስ ነው፡፡ መለኮት በሥጋ ካልሞተ፣ ሥጋም በመለኮት ካላዳነ መዳን እውን ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ መለኮት በባሕርይው መሞት፣ ሥጋም በባሕርይው ማዳን አይቻላቸውምና፡፡

ዮሐንስን በፍጥሞ ደሴት፡- “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” ያለው አንዱ ክርስቶስ ነው /ራእ. 1፡17-18/፡፡ መለኮት ብቻ ነው ካልን “ሞቼ ነበርሁ” እንዴት ይላል? ሥጋ ብቻ ነው ካልን “ፊተኛውና ኋለኛው መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ” እንዴት ይላል? በተዋህዶው አንድ አካልና አንድ ባሕርይ የሆነው ክርስቶስ እርሱ የሞተው እርሱ ሕያውም ነው፡፡
 ወልድ ዋሕድ ብለን ነው የምናምነው ማለት በሰማይና በምድር አብ አንድ ልጅ አለው ብለን እናምናለን ማለት ነው፡፡ ንስጥሮስ፡- “ማርያም የወለደችው ሰው ነው፤ ስለዚህ ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ መባል አይገባትም፡፡ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ግን የአምላክ ልጅ አደረበት፤ አብ ልጄ ነው ሲል በጸጋ ልጅነትን አገኘ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ” በማለት ስላስተማረ በኤፌሶን ጉባኤ በ431 ዓ.ም. ተወግዟል፡፡ ይህ አንዱን ክርስቶስ በአካልም በባሕርይም መክፈል ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ ግን “የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት በዮርዳኖስ መሰከረ እንጂ ስለሁለት ልጆች አልመሰከረም፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ልጅና የባሕርይ ልጅ ይባላል፡፡ አንድ ልጅ በመባሉ ቀዳሚና ተከታይ የሌለበትን መሆኑን የባሕርይ ልጅ መባሉ ከጸጋ ልጅነት ልዩ መሆኑን ያሳያል፡፡ የባሕርይ ልጅ መባሉ አብን በመልክ መስሎ፣ በክብር ተካክሎ መወለዱን ያመለክታል፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ሳለ እርሱ እንዴት አንድ ልጅ ተባለ? ስንል እርሱ የባሕርይ ልጅ እኛ የጸጋ ልጆች ስለሆንን ነው፡፡ ለእርሱ የጸጋ ልጅ መባል እንደማይስማማው ለእኛም የባሕርይ ልጅ መባል አይስማማንም፡፡ እርሱ ከአብ በመወለዱ የባሕርይና አንድ ልጅ ነው፡፡ ይህ ልደቱም የባሕርይ ልደት ነው፡፡ ከአብ የተወለደውና ከድንግል የተወለደው አንድ ነው፡፡ አንድ ልጅ ወይም ወልድ ዋሕድ ነው፡፡ በሰማይና በምድር አብ አንድ ልጅ አለው፡፡ ወንጌላዊው፡- “አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” ያለው ለዚህ ነው /ዮሐ. 1፡14/፡፡
ስለዚህ ክብር የዕብራውያን ፀሐፊ የገለጠውንና አባቶች የተረጎሙትን እናያለን፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ፡- “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ይላል /ዕብ. 1፡2/፡፡ “ሁሉን ወራሽ” ነው፡፡ አንድ ልጅ ከሆነ ሁሉን ይወርሳል፡፡ አንድ ልጅ ያላቸው ንብረታቸው ሳይከፈል ለዚያው ለአንዱ ልጅ ይሆናል፡፡ ልጅ የሚወርሰው ከእርሱ በፊትና እርሱ እያለ ወላጆች ያፈሩትን ነው፡፡ ክርስቶስ ግን የሚወርሰው ራሱ የፈጠረውን በመሆኑ ከምድራውያን ወራሾች የተለየ ነው፡፡ ዳግመኛም ፀሐፊው፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይላል /ዕብ. 1፡3/፡፡
“እርሱም የክብሩ መንጸባረቅ”  አለው፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከፀሐይ አካል ሳይለይ በዚህ ዓለም እንደሚያበራ እንዲሁም ከአብ የተገኘው ቃለ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስም ከአባቱ ሳይለይ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ ከብርሃን ብርሃን እንዲገኝ አብን አህሎና መስሎ ተወልዷል፡፡ ልጅ ከወላጁ ሲወለድ በተከፍሎ /በመለየት/ ነው፡፡ ስለዚህ በራሱ መኖር ይችላል፡፡ ቃል ግን ከአብ ሲወለድ ያለ ተከፍሎ ወይም ያለ መለየት ነው፡፡ እርሱ የባሕርዩ ምሳሌ ነው ይለዋል፡፡ ልጅ ወላጆቹን ባይመስል የአባቱን አባት ወይም የእናቱን እናት ይመስላል እየተባለ ወደኋላ ይፈለጋል፡፡ አባቱን ግን ቢመስል ይበልጥ ያስደስታል፡፡ ወልድ ግን አባቱን የሚመስልና የሚያህል ነው፡፡ ልጅ አባቱን ቢመስል በዘመን ያንሳል፣ በክብር ከአባቱ ይቀንሳል፡፡ በሰውነቱ ግን እኩል ነው፡፡ ከሰው የተገኘ ሰው ነው፡፡ ወልድም ከአምላክ የተገኘ አምላክ ነው፡፡ የባሕርዩ ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህ ነው አብን በሙሉነት የገለጠው፣ የተረከው /ዮሐ. 1፡18/፡፡ ዳግመኛም፡- “ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ” ይለዋል፡፡ ሰማይ ያለ ካስማ የቆመው፣ ምድር ያለመሠረት የጸናው በእርሱ ደጋፊነት ነው፡፡ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የፍጥረትን ቀጣይነት ያረጋገጠ ነው፡፡
በመቀጠል፡- ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይለዋል፡፡ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይለዋል፡፡ ካህን መሥዋዕት ያቀርባል እንጂ መሥዋዕት አይሆንም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ካህንም መሥዋዕትም ሆኖ ከኃጢአታችን ያነጻን ነው፡፡ ልጅ ምንም ልጅ ቢሆን ከአባቱ አጠገብ ይቀመጣል እንጂ ዙፋንን አይጋራም፡፡ አንድ ንጉሥ ዙፋኑን ለልጁ አያጋራም፡፡ በዙፋን እንዲቀመጥ አይጋብዘውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዙፋን ቀኝ የተቀመጠ በመሆኑ አልጋ ወራሽ ልጅ ሳይሆን ንጉሥ ነው፡፡ አዎ ወንጌላዊው ያየው እውነት ነው፡-
     “አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” የብርሃን ልጅ ብርሃን፣ የአምላክ ልጅ አምላክ፣ የንጉሥ ልጅ ንጉሥ እንደሆነ አየን ማለቱ ነው፡፡ እኛም እንድናይህ አግዘን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ