የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ሚያዝያ 5/2008 ዓ.ም.
“እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና” /ዮሐ. 1፡16/፡፡
ወንጌላዊው ስለ ቃል ቀዳማዊ ልደትና ስለ ደኃራዊ ልደቱ ተናገረ፡፡ ክብሩን አየን ብሎ በደብረ ታቦር ያየውን ገለጠ፡፡ ልክ እንደ ደብረ ታቦር ያለ ክብር የተገለጠው በዮርዳኖስ ነበርና ያንን ያየውን ዮሐንስ መጥምቅን አነሣ፡፡ ወንጌላዊውም ሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ያዩት ክብር በሥጋ ውስጥ የተሰወረውን መለኮታዊ ክብር ነው፡፡ ሰዎች እርሱን ሙሴ ነው፣ ኤልያስ ነው ይሉት ነበር፡፡ እርሱ ግን አምላከ ሙሴ አምላከ ኤልያስ እንጂ ሙሴና ኤልያስ አይደለም፡፡ ይህንንም ለመግለጥ በደብረ ታቦር ሙሴን ከመቃብር፣ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እንዲመሰክሩ አደረገ፡፡ ደብረ ታቦር ስለ ክርስቶስ ማንነት ጥልቅ ትምህርት የነበረበት የመገለጥ ተራራ ነው፡፡ ጴጥሮስ ይህን ክብር ሳያይ ነው፡- “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ የመሰከረው /ማቴ. 16፡16/፡፡ ሳያይ መሰከረ፣ አሁን ደግሞ ያመነውን አየ፡፡ አይቶ ማመን እምነት አይደለም፡፡ አምኖ ማየት ግን የሃይማኖት ዋጋው ነው፡፡ ጌታችን የጴጥሮስን እምነት ሊያጸናለት በደብረ ታቦር ክብረ መንግሥቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡ ጴጥሮስ ደብረ ታቦርን አልረሳትም፡፡ ከብዙ ዘመን በኋላ እምነቱ በፈጠራ ላይ ያልተመሠረተ መገለጥ መሆኑን ሲያብራራ፡- “ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን” ብሏል /2ጴጥ. 1፡17-18/፡፡
ቃል ሥጋ በመሆኑ ለራሱ ክብር ባይጨመርለትም፣ ሥጋ ግን ክብር ተጨምሮለታል፡፡ አንድ ንጉሥ አንዲት ድሃን ቢያገባ ከእርሱ የተነሣ ልዕልት እንድትባል እኛም ከእርሱ ሰው መሆን የተነሣ አዝማደ መንግሥት፣ ልዑላንና ልዕልቶች ሆነናል፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ አግኝተናል፡፡ “እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና” /ዮሐ. 1፡16/፡፡ ሰው በሰጠ ቁጥር ከራሱ እያጎደለ ነው፡፡ እርሱ ግን ሲሰጥ የሚጎድልበት አይደለም፡፡ ሰው በሰጠ ቁጥር ይሰስታል፣ እርሱ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምራል፡፡ ሰው በሰጠ ቁጥር ስጦታ ስጦታውን ያያል፣ እርሱ ግን ስጦታውን ሳይሆን እኛን ያያል፡፡ ሰው በሰጠ ቁጥር ይደምራል፣ እርሱ ግን በላይ በላዩ ይጨምራል፡፡
“እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀበልን” እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የማይነካ ጸጋ አለው፡፡ ባንቀበለው እንኳ ተከድኖ ይኖራል እንጂ ለሌላ አይሰጥም፡፡ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ዓላማ፣ ፍቅርና ጸጋ አለው፡፡ ጸጋው ፍጹም በመሆኑ በተነሣለት ቁጥር የሚቀንስ አይደለም፡፡ የማይጎድል ብልጽግና ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር የሚሰጥ፣ እንደ እርሱም ሙሉ የለም፡፡ ከሀብቱ ሙላትም አላዳላም፡፡ ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ከሰው ብንከጅል የሰው እጅ ትንሽ ነው፡፡ እርሱ ግን እጀ ሰፊ ነው፡፡ ከእርሱ ያልተቀበለ የለም፣ ያላመሰገነ ግን ይኖራል፡፡ በአማኝና በማያምን መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ሙላት መቀበል ድንቅ ነው፡፡ ሰው ከሰጠ በኋላ ይንቃል፣ ምክንያቱም ሰውዬውን ሳይሆን ስጦታውን ያያል፡፡ ሰውዬው ከስጦታው ያንስበታል፡፡እግዚአብሔር ግን እኛን ያያልና ሲሰጠን ይኖራል፡፡ ስጦታውም ንጉሣዊ ስጦታ ነውና መስጠት ክብሩ ነው፡፡ ያልተቀበለ የለም፡፡ እግዚአብሔር ተአምረኛ ነው ስንል ተአምር ያላደረገለት የለም ማለታችን ነው፡፡ ይህች ሰዓት እንኳ የእርሱ ተአምር ናት፡፡ ሰው ከክፉ ውስጥ መልካም አውጥቶ እያመሰገነ እኛ ክርስቲያን የተባልን ግን ከመልካም መልካም ማውጣት ተስኖን እናማርራለን፡፡ የሚገርመው እግዚአብሔር ምስጋና እየተቀበለ ያለው ከሞላላቸው ሳይሆን ከጎደለባቸው መሆኑ ነው፡፡
በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን ይላል፡፡ አነባብሮ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ በልጅነት ላይ መንግሥተ ሰማያትን፣ በብሉይ ላይ ሐዲስን፣ በትንሣኤ ልቡና ላይ ትንሣኤ ሙታንን፣ በነቢያት ላይ ሐዋርያትን፣ በወንድሞች ላይ ወንድሞችን፣ በቀን ላይ ቀንን፣ በዘመን ላይ ዘመንን፣ …የሰጠን አምላክ ነው፡፡ ቅኔ የተነባበረ ምስጋና ነው፡፡ ድርብ፣ ህብር፣ እጥፍ ምስጋና ነው፡፡ አነባብሮ ለሚሰጥ አምላክ የተነባበረ ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምስጋና ላይ ምስጋና ለእርሱ ይገባዋል፡፡ “ይገባዋል” የሚል ቃል በምስጋና ውስጥ ይገለጣል /ራእ. 5፡12/፡፡ የተነገረለት ሁሉ እውነት ነው፣ ይሰጠው፣ ይድመቅ፣ ይክበር፣ ይንገሥብን ማለት ነው፡፡ ንጉሥና ጳጳስ ሲቀባ ይደልዎ – ይገባዋል ይባላል፡፡ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ያቀረብነው ማንኛውም ምስጋና ያሳነስነው እንጂ ያበዛነው የለም፡፡ ሰውን ከልክ በላይ ልናመሰግን እንችላለን፡፡ ሰው በአፋችን ልክ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ግን የልኩን ያህል እንኳ ልናመሰግነው አንችልም፡፡ ልክ የለውም፡፡ ለፈሳሽ ለጠጣር፣ ለርቀት ለወሰን መለኪያ አለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ልክ የለውም፡፡ ለአሠራሩ ወሰን፣ ለምስጋናው ገደብ የለውም፡፡
“ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” /ዮሐ. 1፡16/፡፡ የሁለቱን ኪዳናት ስያሜና መካከለኞች አነሣ፡፡ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን አጭር ስያሜ ብንሰጣቸው ሕግና ጸጋ ይባላሉ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ብቻ ሳይሆን እውነትም ሆኗል፡፡ የሕግን ብይን በሙሉ ተቀብሏል፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕግ ቢሆንም በውስጡ ጸጋ ነበረው፣ ሐዲስ ኪዳንም ጸጋ ቢሆንም በውስጡ ሕግ አለው፡፡ የሕግን ብያኔ ግን ክርስቶስ ተቀብሏል፡፡ ሕግ ማለት ሰው ለእግዚአብሔር የሚያደርገው መልካምነት ነው፤ ጸጋ ግን እግዚአብሔር ለሰው ያደረገው መልካምነት ነው፡፡ የሰው መልካምነት በጅምር ስለተቋረጠ የማይቋረጠው መልካምነት በሐዲሱ ኪዳን ፈሰሰ፡፡
እስራኤልን በሙሴ አነጋገራቸው፣ እኛን ግን በልጁ ተናገረን፡፡ እስራኤልን በአስተርጓሚ አናገራቸው፣ እኛን ቃሉ በሆነው ልጁ በቀጥታ አነጋገረን፡፡ ሙሴ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል አላቸው፣ ጌታችን ግን እኔ ግን እላችኋለሁ አለን፡፡ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር 500 ጊዜያት ያህል ተነጋገረ፣ አንድ ጊዜ ግን ፊቱን አላየም፣ እኛ ግን አየነው፡፡ ከእርሱም ጋር በላን ጠጣን፡፡ ደስም አለን፡፡
ለተቀበልከን አምላክ ምስጋናና ክብር ይሁን፡፡