“እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ” /ዮሐ. 1፡23/፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ መሢሁ እንዳልሆነ አበክሮ ተናገረ፡፡ ኤልያስም እንዳልሆነ በግልጥ መሰከረ፡፡ እርሱ ግን በነቢዩ በኢሳይያስ ትንቢት የተነገረለት መንገድ ጠራጊ መሆኑን መሰከረ፡፡ ዮሐንስ ከመወለዱ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ትንቢት ተነግሮለታል፡፡ ዮሐንስም ስለ እርሱ በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፈውን ያውቅ ነበር፡፡ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ሳይሆን አስቀድሞ የታወቀ ኑሮን እንደሚኖር መሰከረ፡፡ ይህን የሚመስል አሳብ ነቢዩ ዳዊትም ይናገራል፡- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” /መዝ. 138፡14-16/፡፡
ሰው ግሩም ብቻ ሳይሆን ድንቅም ነው፡፡ ግሩም ማለት ግርማዊ ተፈሪ ማለት ነው፡፡ ሰው በፍጥረት ፊት ገዥ ነውና ተፈሪ ነው፡፡ ወደ ቤቱ ሲገባ ፀሐይ የምትጠልቀው ይህ ገዥ በመኝታው እንዳይረበሽ ነው፡፡ እርሱ ወደ ቤት ሲገባ አራዊት የሚወጡት ስለሚያፍሩት ነው፡፡ ከእንቅልፉ ሲነቃ ወፎች የሚዘምሩት ገዥው ከቤተ መንግሥቱ ሊወጣ ስለሆነ የሙዚቃው ቡድን ማወጅ ስላለበት ነው፡፡ ገዥው ዕረፍቱን ሲጨርስ ጨለማ እንደ መጋረጃ ይገለጣል፡፡ ሰው በፍጥረት ፊት ግርማዊ ነው፡፡ በራሱ ፊት ድንቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ተፈጥሮው የጠቢባን ጥበብ ሊደርስበት ያልቻለ ድንቅ ስብስብና መዋቅር ነው፡፡ ነቢዩ ያልተሠራ አካሉና ያልተፈጠሩ ቀኖቹ በእግዚአብሔር እንደ ታዩ ይናገራል፡፡ እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር መጽሐፍ እንደ ተጻፉ በመናገር ያመሰግናል፡፡ እግዚአብሔር የሕይወታችንን ታሪክ አስቀድሞ ጽፎታል፡፡ ታሪኩም የሚደመደመው መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ሰው ራሱን ገሀነም ሲያገኘው ከተጻፈው ወጥቶ ነው፡፡ ስንወለድ የታየን ሳይሆን ዓለም ሳይፈጠር ታይተናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” ይላል /ኤፌ. 1፡4/፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ እርሱ የተጻፈውን የሥራ ድርሻ እየገለጠ ነው፡፡ ድርሻን ማወቅ ትልቅ ደስታ ነው፡፡ የማመንታት ኑሮ የምንኖረው፣ ከሩጫችን በኋላ የማናርፈው ድርሻችንን በትክክል ባለማወቅ ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ፍጻሜ ላይ እንዲህ የሚል የእርካታ ጸሎት አቀረበ፡- “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” /ዮሐ. 17፡4/፡፡ ሁላችንም በዕድሜአችን መጨረሻ ይህን መናገር ስንችል ሞትን በደስታ እንጋፈጣለን፡፡ በጌታችን ጸሎት ውስጥ የምንማረው፡-
1- ልናደርገው የተሰጠን ሥራ አለ፡፡ ሥራ ፈት አይደለንም፡፡
2- ያንን ሥራ የምንሠራው በምድር ላይ ነው፡፡ በሰማይ የሥራ ዋጋ እንጂ ሥራ የለም፡፡
3- እግዚአብሔር የሚከብረው የእርሱን ሥራ ስንፈጽም ነው፡፡ ሥራውን መጀመር ብቻ ሳይሆን መፈጸም ይገባናል፡፡ በጌታችን ጸሎት ውስጥ የብዙዎቻችን ችግር ይታያል፡-
የተሰጠንን ሥራ መለየት አልቻልንም፡፡ ይህ በጣም ጊዜን የሚጋፋ ነገር ነው፡፡ ድርሻችንን ካላወቅን ያለ ድርሻችን እያበላሸን ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ሥራ ፈት ሆነን ተቀምጠን ሊሆን ይችላል፡፡ ባልተሰጠን ቦታ ስንገኝ የተሰጠን ቦታ ክፍት ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚያ ላንሞላ እዚህ እያጎደልን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህች ዓለም የሥራ ቦታችን እንደ ሆነች ዘንግተናል፡፡ በሰማይ ያለው የምድር ዋጋ መሆኑን ረስተናል፡፡ እግዚአብሔርን የምናከብረው በምስጋና በጸሎት ብቻ ሳይሆን የሰጠንን ሥራ በመፈጸም መሆኑንም ማሰብ ያስፈልገናል፡፡
“እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ” /ዮሐ. 1፡23/፡፡ ንጉሥ የሚያልፍበት መንገድ፣ ጠራጊ አለው፡፡ በጥንቱ ከመንፈቅ በፊት መንገድ ጠራጊው ሕዝቡን አስተባብሮ ተራራውን እየናደ፣ ሸለቆውን እየሞላ ያስተካክላል፡፡ በዘመናዊው ዓለምም መንገዱ ከሚፈነዳ ነገር ንጹሕ መሆኑን እያረጋገጠ መንገድ ጠራጊው ያልፋል፡፡ ዮሐንስ ግን የሚያቀናው የጌታን መንገድ ነው፡፡ የጌታ መንገድ የሰው ልብ ነው፡፡ ይህን መንገድ ማስተካከል በዓለም ላይ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከተስተካከለ ግን የዘላለም መንገድ ነው፡፡ ጎዳናን ከመሥራት የሰውን ልብ መጠገን ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ጎዳናዎች የሚሠሩት ሰው እንዲያልፍባቸው ነው፡፡ የሰው ልብ ግን የሚሠራው እግዚአብሔር እንዲያልፍበት ነው፡፡ ያ መንገድ የሚቀናውም በንስሐ ነው፡፡
ዮሐንስ የምድረ በዳው ድምፅ ነው፡፡ ምድረ በዳ የተባለው ዘመኑና የሰው ልብ ነው፡፡ ከነቢዩ ከሚልክያስ በኋላ ነቢይ አልተነሣምና የዝምታ ዘመን ነበር፡፡ ይህ ለአራት መቶ ዓመታት የነበረው ዝምታ የተሰበረው በዮሐንስ ነውና የምድረ በዳው ድምፅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዝም ያለበት ዘመን አስጨናቂ ዘመን ነው፡፡ “በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር” ይላል /1ሳሙ. 3፡1/፡፡ ትልቅ ቅጣትም እግዚአብሔር የቃሉን ረሀብ በምድር ሲያመጣ እንደሆነ በነቢዩ በአሞጽ ተነግሯል /አሞ. 8፡11/፡፡ ቃሉ የሚሰጠንን ደስታ የጎልማሳነት ኃይል፣ የቁንጅና ድምቀት አይሰጠንም፡፡ ያለ ቃሉ ጎልማሶች ይዝላሉ፣ ቆንጆዎች ይረበሻሉ፡፡ ዮሐንስ የምድረ በዳው ድምፅ ስለነበረ ትልቅ በረከት ነው፡፡ ዛሬም ያሉ ቃሉን የሚያገለግሉን በረከቶቻችን ናቸው፡፡ ሌላው ምድረ በዳ የተባለው የሰው ኑሮ ነው፡፡ ምድረ በዳ የሚታይ ለምለም፣ የሚሰማ መልካም የሌለበት ነው፡፡ እንዲሁም ከሰው ክፋት የተነሣ መርዶ በበዛበት ዓለም ላይ ዮሐንስ መጽናናትን የሚሰብክ የምድረ በዳ ድምፅ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ስለ ቃል ተናግሯል፡፡ ዮሐንስ ደግሞ ድምፅ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቃል ክርስቶስ ነው፣ ዮሐንስ ድምፅ ነው፡፡ ድምፅ ቃልን የሚያስተጋባ ነው፡፡ ዮሐንስም ክርስቶስን የሚያጎላ ነው፡፡