የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 6

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ጥር 28/2008 ዓ.ም
የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ትምህርቶች
የዮሐንስ ወንጌል ከሦስቱ ወንጌላት ልዩ የሚያደርገው የክርስቶስን መለኮታዊነት ለማስረዳት የሚተጋ ወንጌል በመሆኑ ነው። የጌታችንን ትምህርቶች በስፋት አስፍሮልናል። እንደ ሌሎቹ ወንጌላት በክርስቶስ ምሳሌዎችና ተአምራት ላይ ብዙ ዘገባ አላደረገም። የጌታችንን መለኮታዊነት ለመግለጽ አንዳንድ ተአምራትን ቢጽፍም ዋነኛ ዓላማው የጌታችን ህልውና ከዘላለም መሆኑን መግለጥ ነው። ወንጌሉ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች የሚከፈል ነው። ከምዕራፍ 1-12 ስለ ጌታችንን መለኮታዊነት የገለጠበት ሲሆን ከ13-21 ከሐሙስ ማታ ጀምሮ ያለውን የጌታችንን ትምህርትና ነገረ መስቀሉን እንዲሁም ትንሣኤውን ይናገራል። ከምሴተ ሐሙስ ጀምሮ ያለውን ክስተት ሁሉም ወንጌላውያን ሲጽፉ ትምህርቱን ግን በስፋት የጻፈልን ዮሐንስ ነው።
የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ትምህርቶች
1- ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት ይናገራል

ዮሐንስ በወንጌሉ የክርስቶስን መለኮታዊነት የሚገልጸው በአራት መንገዶች ነው። 1ኛ- ዘላለማዊ ነው። 2ኛ- ከአብ ጋር የተካከለ ነው። 3ኛ- አምላካዊ ተአምራት ያደረገ ነው። 4ኛ- የሕይወት ምንጭ ነው።

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት ወይም ዘላለማዊነት ለመግለጥ ይተጋል። ሥጋ መልበስ አንድ ታላቅ ክስተት እንጂ የህልውና መነሻ እንዳልሆነ በመግለጥ ይጀምራል። ከአርያም ወደ ቤተ ልሔም ይወርዳል እንጂ ከቤተ ልሔም ተነሥቶ ወደ አርያም ለመድረስ አይታገልም። ብዙዎች የክርስቶስን አምላክነት መቀበል የሚቸገሩት አሰሳቸውን የሚጀምሩት ከቤተ ልሔም ስለሆነ ነው። ቤተ ልሔም ግን የአንድ ታላቅ ፍቅር መግለጫ እንጂ የክርስቶስ መነሻ አይደለችም። ከቤተ ልሔም በፊት በመለኮትነት የኖረው ከቤተልሔም በኋላ ግን አምላክም ሰውም ነው። ዮሐንስ የክርስቶስን ዘላለማዊነት ለመግለጥ፡- ከአብ ጋር ከዘላለም እንደ ነበረ ይናገራል /ዮሐ. 1፡1/። ፍጥረትን ያበጀ፣ የሁሉም ነገር የመገኘቱ የበላይ ምክንያት እንደ ሆነ ያስረዳል /ዮሐ. 1፡3/። ዮሐንስ መጥምቅ ጌታችንን በሥጋ ልደት ስድስት ወር ቢቀድመውም ከዮሐንስ በፊት እንደ ነበረ ይመሰክራል /ዮሐ. 1፡30/። “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” በማለት ጌታችን ለአይሁድ የተናገረውን ይጠቅሳል /ዮሐ. 8፡58/። ከአብርሃም እስከ ጌታችን የሥጋ ልደት 2000 ዓመታት የዘመን ርኅቀት አለው። ጌታችን ከአብርሃም በፊት እንደ ነበር ሲናገር ገና የሠላሳ ዓመት ጎበዝ ነበር። እርሱ ግን በመለኮትነቱ ከአብርሃም በፊት የነበረ ነው።
ዮሐንስ ከአብ ጋር በእኩያነት መኖሩን በመግለጥ የክርስቶስን መለኮታዊነት ይገልጣል። “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ይላል /ዮሐ. 1፡1/። ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም ከአብ ጋር ነበረ። ከእግዚአብሔር አብም ጋር ልዩ ኅብረት አለው። ከአብ ጋር የኖረውም በጥገኝነት ሳይሆን በእግዚአብሔርነት ነው። ራሱ ጌታችንም፡- “እኔና አብ አንድ ነን” /ዮሐ. 10፡30/ ብሏል። በአብ ክብር ያለ በመሆኑ ክርስቶስን ማየት አብን እንደ ማየት ነው /ዮሐ. 14፡9/።  አብ ያለውን ሕይወት ክርስቶስ አለው። ፍጹም ፈራጅም ነው /ዮሐ. 5፡19-29/።

ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊነት ያስረዳው ያደረገውን ተአምራት በመግለጥ ነው። ወደ አገልግሎቱ ከገባ በኋላ ጌታችን ያደረገውን የመጀመሪያውን ተአምር ዘግቦአል /ዮሐ. 2፡1-11/። በዚህ ተአምርም ክብሩን ገልጦ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አምነዋል። ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊነት የገለጠው የሕይወት፣ የእውነትና የብርሃን ምንጭ መሆኑን በመግለጥ ነው /ዮሐ. 1፡4/። እነዚህ ነገሮች የመለኮት ገንዘብ ናቸው። በክርስቶስ አምነን የምንባረከው ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ ነው። አሊያ “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው”  የሚለው ርግማን ይደርስብን ነበር /ኤር. 17፡5/። በሃይማኖተ አበው እንደ ተገለጠው፡- “ማንም ማን ከመለኮት የተለየ ፍጡር ነው ብሎ በክርስቶስ አይመን፤ ከሕይወት እንዳይለይ፤ ፍጡር ዓለምን ያድን ዘንድ አይችልምና። የፍጡር ሞትም በሰው አምኖ የሚጠመቀውን አያከብረውምና ሁላችን በክርስቶስ ሞት እንከብራለን እንጂ” ይላል /ዘአቡሊዲስ ም. 42፣5/።

ጸጋውን ያብዛልን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ