የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 7

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ጥር 30/2008 ዓ.ም.
የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና አስተምህሮ
2- ሰባቱ እኔ ነኝ
በወንጌሉ ውስጥ ከምናገኛቸው ዋና ዋና ትምህርቶች አንዱ ሰባቱ እኔ ነኝ የሚሉ መገለጫዎች ናቸው። ጌታችን ራሱን “እኔ ነኝ” በማለት በሰባት መንገዶች ገልጧል። እኔ ነኝ ብሎ የሚናገር እግዚአብሔር ብቻ ነው። ከፍጡር ወገን እኔ ነኝ ብሎ መናገር የሚችል ማንም የለም። ምክንያቱም በየደቂቃው ከአድራሻው እልፍ ይላልና። በየደቂቃውም ራሱን ያጣዋልና። እርሱ ግን በባሕርዩ የጸና ስለሆነ እኔ ነኝ ብሎ መናገር ይችላል። እኔ ነኝ የሚለው መግለጫ ያህዌ ነኝ ማለት ነው። በዘጸ. 3፡14 ላይ “እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው”እኔ ነኝ ያለው ያህዌ አሁን ሥጋ ለብሶ መጥቷል። እኔ ነኝ ማለት ያህዌ ነኝ ማለት ነው። ጌታን ሊይዙት በመጡ ጊዜ እኔ ነኝ ሲላቸው ወደ ምድር የወደቁት እኔ ያህዌ ነኝ ስላላቸውና አይሁዳውያን ይህን ስም መስማትና መቋቋም ስለማይችሉ ነው /ዮሐ. 18፡6-7/። ይህን ስም መጥራት አንችልም ብለው አዶናይ፣ ኤልሻዳይ እያሉ በልዋጭ ስም ይጠሩታል። ስለዚህ ጌታችን እኔ ነኝ ማለቱ ያህዌ ነኝ ማለቱ ነው።
 እኔ ነኝ እያለ ራሱን የገለጠው በሰባት መግለጫዎች ነው። ሰባት በዕብራውያን ዘንድ ፍጹምነትን አመልካች ቁጥር ነው። ስለዚህ ጌታችን ራሱን የገለጠባቸው ሰባቱ እኔ ነኝ የሕይወት ጥግና ሙላት፣ ለጥያቄአችንም ሙሉ መልስ ናቸው።

1-   “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” /ዮሐ. 6፡35/።

ጌታችን የሕይወት ጥጋብ ነው። እርሱ የበቃኝ ኑሮ መሠረት ነው። በዓለም ላይ ምንም ነገር ብናገኝ በቃኝ አንልም። ክርስቶስን ስናገኝ ብቻ በቃኝ እንላለን። ለምን? ስንል የጥጋብ ልኩ ስለሆነ ነው። የዚህ ዓለም ነገር ሁሉ የጨው ውሃ እንደ ጠጡ መልሶ ያስጠማል።  አንድ ያለው ዐሥር ያምረዋል። ዐሥር ያለው አርባ ያምረዋል። ክርስቶስ ግን የእርካታችን ሙሉ መልስ ነው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ በማለት የተናገረው ኅብስት አበርክቶ ስለመገባቸው እናነግሥህ ላሉትና መና የሚወርድበትን ዘመን ለናፈቁ አይሁዳውያን ነው። የበረከተ እንጀራም፣ የወረደ መናም ውስጥን አይሞላም። ውስጥን የሚሞላው እርሱን በእምነት መመገብ ብቻ ነው።

2-   “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” /ዮሐ. 8፡12/።

ጌታችን ይህን ቃል የተናገረው ስታመነዝር አገኘናት ብለው አንዲት ሴትን እያዳፉ ላመጡ ከሳሾች ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት የማጋለጥ አገልግሎት የለውም። የማጋለጥ ሥራ የፖሊስና እርምጃው ነው። ጌታ ሰው በጨለማ ሲሆን ራሱን እየረሳ የሌላውን ማንነት እንደሚያይ እየገለጠ ነው። ይህን ቃል ሲናገር እነዚያ ከሳሾች ወጥተዋል። ከሳሾች ግን በዘመናት አሉና ወደ ብርሃን ጋበዛቸው። እርሱ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”ሲል ፀሐይና ጨረቃን እተካለሁ እያለ አይደለም። እርሱ የውስጥና የሕይወት ብርሃን ነው። በእርሱ ብርሃን ፊት ስንቆም ራሳችንን ብቻ እናያለን። ሌሎች ያጎደሉትን እያዩ ከመሳለቅ እኔ ልሞላው የምችለው ምንድነው? የሚያሰኝ ብርሃን ክርስቶስ ነው። ዓለሙ በመካሰስ ይኖራልና ይህ ብርሃን ያስፈልገዋል። እነዚያ ፈሪሳውያን እየተመጻደቁ የመጡት በንጽሕና አይደለም፣ በኃጢአት ዓይነት ነው። ዓለም በኃጢአት ዓይነት ሲናናቅ ይኖራል። የጌታ የቅድስና ብርሃን ግን ራስን ያሳያል። የፀሐይ ብርሃን ሰዎችን እናይበታለን፣ የክርስቶስ ብርሃን ግን ራስን ያሳያል። የፀሐይ ብርሃን ፈራጅ ያደርጋል፣ ክርስቶስ ግን ሸፋኝ ያደርጋል። ወደ ክርስቶስ ስንደርስ እንደ እኛ ያለ ደካማ እንደሌለ ይገባናል።
3-   “እኔ የበጎች በር ነኝ” /ዮሐ. 10፡7/።

በር ሁለት ዓይነት አገልግሎት አለው። ለእንግዳ የሚከፈት፣ ለሌባ የሚዘጋ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም በርነቱ ለበጎች ብቻ ነው። በግ የዋህ ነው፣ ምእመናንም የዋህ ናቸው። ዛሬ ያለው ክርስትና የዋህነትን እያጣ ብልጣብልጥነት እየሆነ ነው። ምናልባት አይጠጡ ይሆናል፣ ግን ጤናን ለመጠበቅ ሊሆን ይችላል። የማያጨሱ ሰው ግን የሚያጨሱ በቤተ ክርስቲያን አሉ። ሜዳዊ ወይም የታይታ ቅድስናን የተሞሉ፣ ነጭ ልብስ እንጂ ነጭ ልብ ያጡ አያሌ ናቸው። ጌታችን በርነቱ ለበጎች ነው። በር ጠባብ ነው፣ ሲገቡ ግን ሰፊ ማረፊያ አለው። ወደ ጌታም ለመድረስ ትግሉ ብዙ ነው። አንዴ ከገቡ ግን መሰማሪያው ሰፊ ነው። በግ ከሌሎች እንስሳት ልዩ የሚያደርገው ያለ እረኛው ይጠፋል። ሌሎቹ እንስሳት በማሽተት ወደ መጡበት ይመለሳሉ። በግ ግን ከእረኛው ከተለየ ይጠፋል እንጂ አስታውሶ መመለስ አይሆንለትም። እንዲሁም ምእመናን በጎች ናቸው ሲባል ክርስቶስን የሚከተሉና አገልጋዮቻቸውን የሚያከብሩ ናቸው ማለት ነው። ራሳቸውን የሚያሰማሩ፣ ተጠሪነት የሌለው ሕይወት የሚኖሩ በጎች አይደሉም።

4-   “መልካም እረኛ እኔ ነኝ” /ዮሐ. 10፡ 11/።

እረኛ የሚያሲዘው ሀብት ስለሌለው የሚያሲዘው ራሱን ነው። ክርስቶስም ራሱን ያስያዘልን እረኛ ነው። እርሱ የነፍሳችን እረኛ ለመሆን በደሙ የፈረመልን ነው። መልካም ያልሆኑ እረኞች አሉ። ለበጉ ስለሚሰጡት ሳይሆን ስለሚቀበሉት የሚያስቡ፣ አውሬ ሲመጣ ጥለው የሚሸሹ እረኞች አሉ። ጌታችን ግን የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ የታደገን መልካም እረኛ ነው።

ምስጋና ለጌትነቱ ይሁን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ