የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የደስታ ማዕድ

ጌታችን በመቃብር ሦስት ሌሊትና ሦስት መዓልት አደረ ስንል የምንቆጥረው ከሐሙስ ማታ ጀምሮ ነው ፡፡ ቅዱስ ቁርባን የተሠራው የሞቱና የትንሣኤው ጥላ ባለበት በምሴተ ሐሙስ ነው ፡፡ በመስቀል ላይ የሚቆረሰውን ሥጋ ፣ በመስቀል ላይ የሚፈሰውን ደም የሚወክል ሥጋና ደሙን በምሴተ ሐሙስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፡፡ ይህን ምሥጢር ለግለሰብ ሳይሆን ለሐዋርያት ማከናወኑ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ሥልጣን ስለሆነ ነው ፡፡ ከክርስቶስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከምእመናን ጋር አንድ የምንሆንበት ስለሆነ በግል ማከናወን ፣ ከቤተ ክርስቲያን ሥልጣንና ከካህናት ተዋናይነት ውጭ መፈጸም ተገቢ አይደለም ፡፡ የምሴተ ሐሙስ እራቱን ሌሎች ሲያዘጋጁት ሥጋና ደሙን ግን ራሱ ጌታችን አንሥቶ ሰጠ ፡፡ ከመጨረሻው እራት ቀጥሎ መሰጠቱ የመጨረሻው መጨረሻ ስለሆነ ነው ፡፡ ጥልቅ ትርጉምና ምሥጢር ያለው ሲሆን ከክርስቶስ ጋር የምንዋሐድበት ነው ፡፡ የምንወስደውም በሚታይና በማይታይ መልኩ ነው ፡፡ ኅብስቱ በሚታይ መልኩ ሲሆን ሥጋን አድራሻ እንዲያደርግ ነው ፡፡ ክርስቶስ ለሥጋችንም ሞቷልና ፡፡ በእምነት ግን የምንቀበለው አማናዊ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋና ደም ነው ፡፡ ጥምቀት ምሳሌ እንዳልሆነ ከእርሱ በፊት ግዝረት ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ ቅዱስ ቁርባንም ምሳሌ አይደለም ፡፡ ምሳሌው የፋሲካው በግ ነበረ ፡፡ ግዝረት አንድ ጊዜ እንደሆነ ጥምቀት አንድ ጊዜ ነው ፡፡ የፋሲካው በግ በየዓመቱ እንደሆነ ቅዱስ ቁርባን የሚደጋገም ነው ፡፡
በመስቀል ላይም ጌታችን ጎኑን በጦር ሲወጋ ውኃና ደም መውጣቱ ፣ ውኃው ጥምቀቱን ፣ ደሙ ቁርባንን የሚያሳይ ነው ፡፡ ጌታችን ከቁርባን በፊት የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ለቅዱስ ቁርባን ፍጹም ትሕትና ፣ ፍቅርና ንስሐ እንደሚያስፈልግ ሲያስተምር ነው ፡፡ ጌታችን ኅብስቱን ሲያነሣ ነገ የሚቆርሰውን ሥጋውን እያሰበ ነው ፡፡ እኛም ኅብስቱን ስንበላ መስቀል ላይ የተቆረሰውን የክርስቶስን ሥጋ እናስባለን ፡፡ በሚታይ ኅብስትም የማይታየውን የክርስቶስን ሥጋ እንቀበላለን ፡፡ ጌታችን ወይኑን ሲያነሣ ነገ የሚያፈሰውን ደሙን በማሰብ ነው ፣ እኛም ወይኑን ስንወስድ ይህ ወይን ፍጹም በዕለተ ዓርብ ከፈሰሰው የክርስቶስ ደም ጋር አንድነት እንዳለው እናምናለን ፡፡ እንዴት ኅብስቱ ሥጋ መለኮት ይሆናል ካልን አንድ ፈላስፋም የሚለው እንዲሁ ነውና አማኝ አይደለንም ፡፡ ጌታችን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ድረስ ወደዳቸው ፣ ቀጥሎ የዘላለማዊ ፍቅሩ መግለጫ የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን ሰጣቸው ፡፡ እስራኤል ከግብጽ ምድር የወጡበት የፋሲካ በግ አንድ ጊዜ ታርዶ ድነዋል ፡፡ እኛም አንድ ጊዜ በተፈጸመው በክርስቶስ መሥዋዕትነት ድኅነት አግኝተናል ፡፡ እስራኤል በየዓመቱ የፋሲካውን በግ በማረድ እንደሚካፈሉና ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት እንደሚያድሱ እኛም የክርስቶስን ሥጋና ደም በወሰድን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ይበልጥ እንጠጋለን ፡፡ ጥልቅ ፍቅር ካልሆነ ሥጋዬን ብሉ የሚል የት ይገኛል ፡፡ ይሁዳ ቁርባንን በተከፈለ ልብ ከተቀበለ በኋላ የጥፋት መሳሪያ እንደሆነ ቅዱስ ቁርባን በፍጹም ትሕትናና ንስሐ ካልወሰዱት ዕዳ ይሆናል ፡፡ ተራ ማዕድ ወይም መታሰቢያ ብቻ ቢሆን እንዴት ዕዳ ያመጣል ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ፡፡ ጥምቀት አንድ ጊዜ መሆኑ የምንወለደው አንድ ጊዜ ስለሆነ ነው ፡፡ ለማደግ ግን በየዕለቱ መመገብ አለብን ፡፡ ቅዱስ ቁርባንም መደጋገሙ ልጅነታችን የሚያድግበት ስለሆነ ነው ፡፡
  
የደስታ ቋጠሮ/8
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሰኔ 30/2010 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ