የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የደካሞች ብርታት

 

“የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።” 

ማቴ. 12 : 20 ።

በሸምበቆ ላይ ቅጥቃጤ ፣ በጥዋፍ ላይ እፍታ ሲጨመር ከባድ ነው ። ሸምበቆ ለወትሮ ደካማ ነው ። ጥዋፍም የማብራት አቅሙ ትንሽ ነው ። ሸምበቆ ምንም ነገር መሸከም አይችልም ፣ ጥዋፍም መላውን ቤት ማብራት አይችልም ። በሸምበቆ ምሰሶነት የሚሠራ ቤት ፣ በጥዋፍም መብራትነት የሚበላ እራት የለም ። በተፈጥሮአዊ ድካሙ ላይ ሸምበቆ ሲቀጠቀጥ ፣ በጥዋፍ አቅም ላይም ነፋስ ሲጨመርበት ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው ። ሁሉም ሰው የሸምበቆ አቅም አለው ። አንዳንዶች ግን ቅጥቅጥ ሸምበቆ ናቸው ። ሁሉም ሰው በተፈጥሮ ደካማ ነው ፣ አንዳንዶች ግን ድካማቸው የተገለጠ ነው ። ሁሉም ሰው የጥዋፍ መብራት ነው ፣ አንዳንዶች የሚጤስ የጥዋፍ ክር ናቸው ። ቅጥቅጥ ሸምበቆን ማንም ተስፋ አያደርገውም ፣ ምክንያቱም ተሰንጥሮ ይወጋል ፣ አንዳንድ ሰዎችም የሕይወት ድካማቸው ሲወራ “እኔንም ልጄንም እንዳያበላሹ ፣ አገርንም እንዳይጎዱ መጥፋት አለባቸው” ይባላል ። ከእግዚአብሔር ቀድመን እንፈርድባቸዋለን ። ስህተታቸውን ጆሮ አልለመደውም ፣ ድካማቸውን ስልታዊ ቋንቋ አይሸፍነውም ። መራቆታቸው በአደባባይ ስለሆነ ልብስ መጣል አይቻልም ። ሞተው ማረፋቸውን ባናውቀውም “ምነው ሞተው ባረፉት” እንላለን ። ቅጥቅጥ ሸምበቆን የበለጠ የምንሰብረው እኛን እንዳይወጋን ብለን ነው ። አንዳንድ ሰዎች መወገድ አለባቸው የምንለው ለራሳችን ደኅንነት በማሰብ ነው ። ሸምበቆ ስብራቱ ይጠገናል ተብሎ ተስፋ አይደረግም ። አንዳንድ ሰዎችም ንስሐ ቢገቡም የሚነጹ አይመስለንም ። ንስሐ ገብተናል ፣ ይቅርታ ጠይቀናል ቢሉ እንኳ የልብ እየሠሩ ንስሐ አይገባንም ፣ ይቅርታም አይመጥነንም እንላለን ። 

የሚጤስ ጥዋፍን በእፍታ ወደ መብራትነት መመለስ ከባድ ነው ። እርገጡትና በደንብ አጥፉት ይባላል ። ሽታው ያውካል ፣ ዓይን ይመዘምዛል ። እንደ ገና ያበራል ተብሎ ተስፋ አይደረግም ። በእፍታ ከማብራት ፣ በእግር ማጥፋት ይቀላል ። አንዳንድ ሰዎች ስህተታቸው እምነትን የሚያሸንፍ ይመስላል ፣ ውድቀታቸው ንስሐ ያለው አይመስልም ። ጥፋታቸው ያውካል ። ችግራቸው እየተከተለ ያስለቅሰናል ። ከአጠገባችን እንዲርቁ ወይም ከአጠገባቸው ለመራቅ እንመኛለን ። እነዚህ ሰዎች ቢበረቱ የሚሆኑት የጥዋፍ መብራት ነው ። ጎበዝ የሚባሉትም ጉብዝናቸው የሸምበቆ ጉልበት ነው ። ንስሐ ቅጥቅጡን ሙሉ ሸምበቆ ፣ የሚጤሰውንም ክር የጥዋፍ ብርሃን ያደርገዋል ። ባንሰበርም ሸምበቆ ነን ፣ ባንጠፋም የጥዋፍ ክር ነን ። የሚሸከመን አምላክ እንፈልጋለን እንጂ ሌላውን ለመሸከም አቅም ያንሰናል ። ፀሐዩን ጌታ እንናፍቃለን እንጂ የጥዋፍ ብርሃናችን ዙሪያችንን አያሳየንም ።

እግዚአብሔር የሚያውቀን በሸምበቆነታችን ነው ። ሰይጣን ደግሞ በስህተትና በክስ ይቀጠቅጠናል ። እግዚአብሔር የሚያውቀን በጥዋፍ መብራትነታችን ነው ። ሰይጣን ደግሞ የሰውን አፍ ተጠቅሞ ያጠፋናል ። ብቻ ዓለም ሰባራ በሰንጣራ የሚስቅባት መድረክ ናት ። 

የአንዳንድ ሰዎች አቅም ቅጥቅጥ ሸምበቆ ነውና ተግሣጽን መቀበል እንኳ አይችልም ። የድሮ ልጅ በርበሬ ቢያጥኑትም ጠንካራ ነው ፣ ብረት አግለው ቢጠብሱትም የማይበገር ነው ። የአሁን ልጅ ግን በጥፊ የሚሞት ነው ። የገዛ ካልሲውን አጥቦ እጁ የሚወልቅ ነው ። ብዙ ቅጥቅጥ ሸምበቆዎች አሉ ። በተለመደውና በቆየው የማግባባት መንገዳችን ልናድናቸው አንችልም ። ብዙ ፍቅር ይፈልጋሉ ። ራርቶ የሚያክማቸው ይሻሉ ። የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ የሚጤስ ጥዋፍ ነው ። ከመጨረሻው የሚጀምር አምላክ ካልሆነ የሚችላቸው የለም ። ከእነርሱ ጋር ስንሆን ልቅሶአቸው ይረብሻል ። ብሶታቸው የራሳችንን ብሶት ይቀሰቅስብናል ። እነርሱን ከማድመጥ መሸሽ ይቀናናል ። ተናግረው የማይረኩ ይመስላሉ ፣ ቀኑን እንዳያጨልሙብን እንርቃቸዋለን ። እኛ ለስሜታችን ስንጨነቅ እነርሱ ግን በሞትና በሕይወት መካከል ይዋትታሉ ።

ለደካማ የሚሆን ልብ ያለው በሥጋ የተገለጠው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እርሱ ደካማን እንደሚወድና ታሪክን እንደሚለውጥ በቤተ ልሔም መወለዱ ፣ እስራኤልን ወዳሰቃየችው ግብጽ መሰደዱ ፣ በኃጢአተኞች ከተማ በናዝሬት ማደጉ ፣ ከቀራጮች ጋር አብሮ መብላቱ ፣ ከወንበዴዎች ጋር መሰቀሉ ምስክር ነው ። ምሥጢረ ሥጋዌ ለደካሞች ስለተከፈለው ዋጋ የሚናገር የምስኪኖች መጽናኛ ነው ።

ጌታ ቅጥቅጦችን አይሰብርም ። ተስፋ ላጡት ተስፋ ይሆናል ። የሚያስለቅሱ ወገኖችን አጠገቡ አድርጎ ያባብላቸዋል ። ለአልዓዛር በመቃብሩ ስፍራ ፣ ለኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ እንዳለቀሰ ለእነዚህም ብቸኞች ይራራል ። እንዴት ተበላሹ ? ብሎ ታሪክ አያጠናም ፣ ለምን ተበላሹ ? ብሎ ፍርድ ውስጥ አይገባም ። “እንዴት ልጠግናቸው ?” ይላል ። የደጎች ልብ ከሚችለው በላይ የደከሙ ፣ ጆሮ መስጠት የሚችሉ ሰዎች የማይችሏቸው ጉዳተኞች አሉ ። መድኃኔዓለም ግን የእነዚህ ሁሉ ተስፋ ነው ። 

ለሰው ያታከታችሁ ለክርስቶስ አትከብዱትምና ፈጥናችሁ ወደ እቅፉ ግቡ ።

አቤቱ ከአንተ ርቀን እኛነታችንን የጎዳነውን ወደ አንተ አቅርበን ።

የብርሃን መስኮት /1

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ