የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዳዊት ረድኤት

“አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝ. 45፡1።)

በዚህ ዓለም ላይ ስሜታችንን የሚረዳና የሚያግዘን ማግኘት ከባድ ነው ። እንባችንን እንደ ልፍስፍስነት የሚያዩ ፣ ያላየ ብዙ ይርገበገባል በማለት የሚፈርዱብን ፣ ወንድ ሆኖ ምን ይልመጠመጣል በማለት የሚኩራሩብን ፣ ሁሉም የራሱን ልቅሶ ያልቅስ ብለው ጀርባቸውን የሚሰጡን አያሌ ናቸው ። የሚታዘቡንና በቍስላችን ላይ እንጨት የሚሰድዱ ጥቂት አይደሉም ። መከራችንን የወሬ ርእስ አድርገው የሚያጣጥሙ ፣ እሑድ ላይ ቆመናል ብለው የእኛ ዓርብ ላይ የሚሳለቁ አይጠፉም ። በእንዲህ ዓይነት የጨለማ ጉዞ ያየናቸው ይሰወራሉ ። በምሽት የገዛ ጥላችን እንኳ እንደሚጠፋ ሰዎችም ከአጠገባችን ሳይሰናበቱት መሄድ ይጀምራሉ ። መከራ የምንጠብቃቸውን ሰዎች ሲያሳጣን የማንጠብቃቸውን ሰዎች ደግሞ አጠገባችን እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል ። ሰዎችን መዝኖ የሚያሳልፍልን መከራ ነውና በመምጣቱ ፣ የደረጃና የጥራት ባለሙያ ነውና በመድረሱ ደስ ሊለን ይገባል ። ፍሬ ያልነው ሰው ገለባ መሆኑን ፣ የፎከረው የሚክደን ጴጥሮስ መሆኑን የምናውቀው በጭንቅ ሰዓት ነው ።

በመከራ ሰዓት ለማን ላውራ እስክንል ድረስ የመተንፈስ ፍላጎት ያድርብናል ። ተናግረን ስለማንረካ ደጋግመን አንድ ነገርን እናወራለን ። ሰዎች የሰሙን ስለማይመስለን እንለፈልፋለን ። ጭንቀት እያሰከረን እንንገዳገዳለን ፣ እንዘላብዳለን ። እንረሳለን ፣ መኖርን እንጠላለን ። ዓለም ሁሉ በእኛ ላይ ያደመ ይመስለናል ። ያሳለፍነውን የደስታ ጊዜ እስክንረሳ ሁሉም ነገር ጨለማ ሆኖ ይታየናል ። በጨለማ የምናየው ራሱን ጨለማ ብቻ ነው ። በዙሪያችን ያለውን ውድና ውብ ነገር ጨለማ ይጋርድብናል ። መከራም እኔን ብቻ እዩኝ በማለት መፍትሔውን ይሸፍንብናል ልጆች አንድ ነገር ሲበላሽብን ቶሎ ብለው መፍትሔ ያሳዩናል ። ምክንያቱም እኛ ችግሩን ብቻ ስለምናይ መፍትሔው ይጠፋብናል ፣ እነርሱ ግን ችግሩን ትተው መፍትሔውን ብቻ ስለሚፈልጉ ያግዙናል ። በልጅነታችን መፍትሔውን ፣ ስናድግ ችግሩን ማየታችን ጉዞአችንን ቁልቁል አድርጎታል ።

በመከራ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎችን መርዳት ይገባናል ። ይህ ሰዋዊም መንፈሳዊም ግዴታ ነው ። እርዳታዎቹ ብዙ ዓይነት ናቸው ። የመጀመሪያው አብሮ ማዘን መቻል ነው ። ሁለተኛው ሳይሰለቹ ማዳመጥ ነው ። ሦስተኛ አብሮ መጸለይ ነው ። አራተኛ ምሥጢራቸውን መጠበቅና ችግሩን ቀለል አድርጎ ማሳየት ነው ። አምስተኛ አጠገባቸው መሆንና ማረሳሳት ነው ። ስድስተኛ መፈለግ ነው ። ሰባተኛ የእግዚአብሔርን መንገድ ማሳየት ነው ።

እግዚአብሔር በመከራችን ሁሉ ረዳታችን ነው ። እርሱ በዘመናት ሁሉ እነ እገሌን ጣለ ተብሎ ተጽፎለት አያውቅም ። መጣልንም በእኛ አይጀምርም ። እርሱ ይረዳናል/ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ/ እርሱ ይረዳናል /ላላ ተደርጎ ይነበብ/። ስሜታችንን የሚረዱልን ሰዎች ብናገኝ በቀላሉ እንደምንፈወስ እናስባለን ። ስሜታችንን የሚረዳልን አለ ። እርሱ እግዚአብሔር ይባላል ። አንድ ሊቀ ካህን ድርሻው መፍረድ አይደለም ፣ የቆመበት ስፍራ የዳኝነት ዐውድ አይደለምና ። ሰዎች በየትኛውም ችግር ውስጥ ቢያልፉ እነርሱን ማገዝ ግዳጁ ነው ። አንድ ሊቀ ካህን አለ ፣ መፍረድ እየቻለ የሚምር ፣ ለምን ወደቃችሁ ሳይሆን አሁን ላንሣችሁ የሚል ፣ እጆቹ ለምሕረት ፣ ለእርዳታ የተዘረጉ አንድ መምህር አለ ። ያንን መምህር አውቀዋለሁ ። እርሱ ግን ሳላውቀው ያውቀኝ ነበር ። እርሱ በሰው ዓይን አይቶ የማይበይን ነው ። እርሱ የሚሉንን ሰምቶ ገሸሽ የማይለን ነው ። ደህና አዋቂ ሲገኝ እንኳ ሰዎች ችግረኞችን ይጠቁማሉ ፣ እዚያ ሂዱ ይላሉ ። በእውነት እስከማውቀው እገሌ የሚባል ጠንቋይና አዋቂ አለ በማለት የሚያመላክቱ አሉ ። እኔ የማውቀው ያ አዋቂ ፣ ቋጠሮ ሁሉ በፊቱ የሚበተንለት ፣ ተራራ የሚደለደልለት ነው ። እርሱ አብሮ ያለቅሳል ፣ እንደሚረዳን እያወቀ አብሮን ያዝናል ። የዚህ አዋቂ አድራሻው ዕብራውያን 4፡14 ላይ ይገኛል፡- “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም ። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”

የቅዱስ ዳዊት ረዳት የእናንተም ረዳት ነው ። በመከራችን ሰዓት የሚረዳን ካለንበት ድረስ መጥቶ በመፈለግ ነው ። ከውድቀታችን ሥር መጥቶ በሹክሹክታ ድምፅ እወዳችኋለሁ ይለናል ። ክፉውን ወደ በጎ በመለወጥ ፣ ያስጨነቀንን በመርገጥ ይረዳናል ። ዛሬም እጁ ለመባረክ ፣ ክንዱ ለረድኤት አልደከመም ። የዳዊት አምላክ የእኛም አምላክ ነው ። አሜን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ