የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጌርጌሴኖን ታማሚ

ማር. 5፡1-20
በጥብርያዶስ ባሕር በስተደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው በጌርጌሴኖን ከተማ ወደብ ላይ ታንኳዋ ረጋች ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱን አዋጅ የተራራውን ስብከት ካሰማ በኋላ ለምጻም በማንጻት ፣ በሽተኞችን በመፈወስ ፣ማዕበልን በመገሠጽ ታላላቅ ተአምራትን ፈጽሟል ። ከጤነኞች ሠፈር ፣ ከባለጠጎች ገበታ ፣ ከሹማምንት ቢሮ እስካሁን አልተገኘም ። ድሆችንና ምስኪኖችን እየረዳ ይጓዝ ነበር ። በዱር የተጣለውን ወደ እርሱ አቅጣጫ እየሄደ ያገኘው ነበር ። ያ የዱር ነዋሪ በአጋጣሚ ክርስቶስን ያገኘ ይመስለው ነበር ፣ እርሱ ግን ሥራውን የሚሠራው ለአጋጣሚ የሚሆን ምንም ክፍተት ሳይሰጥ ነው ። ሰው እንዳይቀርባቸውና እንዳይረክስ ይሸሹ የነበሩ ለምጻሞችና ድሪቷሞች እርሱ ግን እንዲዳስሳቸው ቀርበውታል ። ቅድስናው የሚገፈትር ሳይሆን የሚያቅፍ ነበር ። የገዛ መልካቸው የጠፋቸው ራሳቸውን በእርሱ መልሰው አግኝተዋል ። በጓዳ ያለውን ጉድለት ያውቅ ነበር ። ሰዎች በአልጋቸው ሁነው ሲያቃስቱ እርሱ ያንን ድምፅ ይሰማ ነበር ። ላልፈለጉት እየተገኘ ፣ ላልጠሩት እየተገለጠ ብዙ ማዳን አደረገ ። እስኪፈልጉትና እስኪጠሩት ቢጠብቅ እስከ ዛሬ አንድ ሰውም አይድንም ነበር ። ደቀ መዛሙርቱም ለእነ እገሌ ብዙ ተደረገ እያሉ እንዳያስቡ በማዕበል ሲጨነቁ ከሞት አዳናቸው ። የነበራቸውን ዘመን ሳይሆን ያለቀውን ዘመናቸውን ክርስቶስ እንደፈለገውና እንደ ከበረበት አስተውለዋል ። “ዘመኔን ሰጥቼው” እያሉ እንዳይፎክሩ ሞት ካደባበት ዘመናቸው ጀመረ ።

ጌርጌሴኖን ልባቸው ጠንካራ የሆነ ፣ የሰው ዋጋ ያልገባቸው ፣ ክርስቶስን ናልን ሳይሆን ከከተማችን ውጣልን ብለው የሚለምኑ ሰዎች ያሉባት ከተማ ናት ። ጌርጌሴኖን ብዙ የአእምሮ በሽተኞችን የምታስተናግድ የጣር ከተማ ናት ። የሰው ዋጋ በወደቀባቸው ፣ ገንዘብ በዙፋን ተቀምጦ በሚገዛቸው ፣ ራስ ወዳድነት በነገሠባቸው ከተሞች ብዙ የአእምሮ ጭንቀት ይከሰታል ። እነዚህ ፍጹም አቅላቸውን የሳቱና አብደው በከተማ የሚዞሩ ፣ በመቃብር የሚኖሩ በሽተኞች በከተማው የታወቁ ናቸው ። የታወቁት ግን በበሽታቸው ብቻ ነበር ። እያሉ እንደሌሉ የተረሱ ቢሆኑም እነርሱም በኃይለኝነታቸው “አለን” ብለው በፍርሃት ሰዎችን ያስገዙ ነበሩ ። መፈራት ሥልጣን ቢሆን ኑሮ እነዚህ ሰዎች ባለሥልጣን ይባሉ ነበር ። ረጅም ምላሳቸው ተፈርቶ ዝም የሚባሉ ፣ ሌላውን እንዳይበጠብጡ እሺ እሺ የሚባሉ ፣ “ስለ ምጣዱ አይጧ ትለፍ” ተብለው የሚከበሩ በሽተኞች አሉ ። መፈራት ሥልጣን አይደለም ። ተወዶ መከበር ፣ ተከብሮ መፈቀር ለቀናዎች የተሰጠ ነው ።
አያልቅበት ጌታ አንዱን ተአምር አድንቀው ሳይፈጽሙ ሌላ ተአምር ያደርግላቸው ነበር ። በረሃ አቋርጦ ፣ ባሕር ተጋፍቶ የሚደርሰው ለእነዚህ ምስኪኖች ነው ። በቀትር የጨለመባቸው ፣ ከቆሙት ጋር ሳይሆን ከሞቱት ጋር ደባል የገቡ ብዙ አሉ ። ከሕያዋን ሰፈር ቦታ ያጡ ፣ የመቃብር ድንጋይ ላይ መሬት የተመሩ አያሌ አልቃሾችን ምድር ይዛለች ። በትዳር ቢኖሩ የመነኑ ፣ አጠገባቸው ያለው የማይረዳቸው ፣ ችግራቸው የስንፍናቸው ውጤት የመሰለባቸው ፣ የሚወዱትን አጥተው መራራን ለማጣጣም ራሳቸውን የሚያለማምዱ ፣ ጭንቀት የማይደክመው ጓደኛ ሁኖ ሌት ተቀን የሚያዋራቸው ፣ ችግር ጎረቤት ሁኖ የተጣበቃቸው ብዙ ተንከራታቾች አሉ ።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ፍለጋ ወደ ጌርጌሴኖን ሄደ ። ሰዎች ባሕር አቋርጠው የሚሄዱት ለመዝናናት ነው ፣ እርሱ ግን ፍቅርን ለመዝራት ባሕር አቋርጦ ሄደ ። ፍቅር በሰው ላይ እንጂ በመሬት ላይ የሚዘራ አይደለም ። ሰው መጥፎ ቢሆን እንኳ ፍቅርን የምንዘራበት የእግዚአብሔር ማሳ ነው ።
የሰው ልጅ በተለያየ ነገር አእምሮውን ይስታል ። ጨርቁን ጥሎ በከተማ ይዞራል ። አንዳንድ የአእምሮ በሽተኞች “አንተን እሾምሃለሁ ፣ ላንተ ሚሊዮን ብር እሰጣለሁ” ይላሉ ። እነዚህ ሰዎች ቢኖረኝ ለእገሌ ይህን አደርጋለሁ እያሉ ያስቡ የነበሩና ያ ችሮታ ምኞት ብቻ ሲሆንባቸው ያበዱ ናቸው ። የአቅማችንን ያህል ፣ አንዳንዴም ከአቅማችን በላይ ልናደርግ እንችላለን ። የራቀን ነገር በምኞት እያወረድን ለምንወዳቸው መነስነስ መጨረሻው አእምሮን ማጣት ነው ። “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዲሉ ። አለመቀጠሉ እንጂ በቀን ሦስት ጊዜ የማያብድ ሰው ጥቂት ነው ። ሠራተኞች ሲለግሙብን ፣ ትዳራችን አላውቅልህ ሲለን ፣ ልጆቻችን በራሳቸው መንገድ ሲሄዱ ፣ ጎረቤት እንደ ጦስ ዶሮ ሲዞረን ፣ እኛ ለተሸከምነው ሰዎች የእኛ ችግር ሲከብዳቸው ፣ በሐሜት ጥሬ ሥጋችንን ሲበሉት ፣ በመውደቃችን የደስታ ድቤ ሲደልቁ ፣ የምናምነውን ነገር እንምረጥላችሁ ሲሉ ፣ አለመለመናችንና ኑሮዬ ይበቃኛል በማለታችን መቃብር ሲቆፍሩብን … በእነዚህ ነገሮች በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ እናብዳለን ። መለስ ብለን ደግሞ የተፈለገው እንዲህ እንድሆን አይደል ብለን ብልህ እንሆናለን ። መንፈሳዊነቱ እስቲመጣ ብልህ መሆንም ዕድሜን ያረዝማል ።
ከዚያ ባሻገር ሰዎች በርኩስ መንፈስ ተይዘው ሊያብዱና አቅላቸውን ሊስቱ ይችላሉ ። ሰይጣን በዋናነት የሚፈልገው የሰውን ማስተዋሉን መስረቅ ነው ።ሁሉ የአእምሮ ሕመም ግን ከአጋንንት አይደለም ። ከትንሹ ራስ ምታት ጀምሮ እያደገ የሚመጣ የአእምሮ ሕመም አለና ሰው ሁሉ ነጻ ላይሆን ይችላል ። ጨጓራ እየሠራ ስለሆነ ይታመማል ፣ ከጨጓራ ይልቅ ሥራ ያለበት አእምሮ ቢታመም የሚደንቅ አይደለም ። ልዩነቱ ግን ከጨጓራ ይልቅ ፈጥኖ የሚፈወስ አእምሮ መሆኑ ነው ። ስለ አእምሮ ታማሚዎች ለማወቅ ግን መጀመሪያ አእምሮ ያስፈልጋል ። በአንዳንድ ባሕል በሽታ ሰንጠረዥ አለው ። ይኼማ ይሻላል የሚል አስተሳሰብ አለ ። የባለጠጋ የድሀ ተብሎም በሽታ ክፍል ያገኘባቸው ባሕሎች የትየለሌ ናቸው ። ብቻ አጋንንት የለም የሚሉና ሁሉም ነገር ከአጋንንት ነው በሚሉ ይህች ዓለም ግራ ተጋብታለች ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባውና ገና ከታንኳው ሲወርድ ርኩስ መንፈስ የያዘው አንድ ሰው ከመቃብር ወጥቶ ተገናኘው ። ይህ ሰው ከቆሙት በታች ከሞቱት በላይ ነው ። የመቃብር ስፍራ ሊያልፉበት የሚያስፈራ ፣ ነገ የሚጠብቀን ቢሆንም ማሰብ የማንፈልገው ዘላቂው ቤት ነው ። እግዚአብሔር ካልፈቀደ እንኳን መኖሪያ መቀበሪያም አይገኝም ። በባሕር የሰጠሙትን ፣ በአየር ላይ ተበትነው የቀሩትን ማሰብ ትምህርታችን ነው ። አንማርም እንጂ ። ሰው የወንድሙን መሞት ሲያምን የራሱን መሞት ግን አያምንም ። ባጭር ቋንቋ እኛ ተንቀሳቃሽ ሬሳ ነን ። ለሕይወታችን ክብረት የሚሰጠው የሞተውና የተነሣው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው ። መሬቴን ነካህብኝ እያልን እንጣላለን ። መሬት የሰው አይደለም ፣ ሰው ግን የመሬት ነው ። የምንረግጣት አፈር አንድ ቀን ትረግጠናለች ። የክርስቶስ ደም ዋጋ ባይሆነን ኑሮ እኛ ሰባና ሰማንያ ኪሎ አፈር ነን ።
ይህ ሰው የጌርጌሴኖኑ እብድ ነው ። ብዙ በሽተኞች ቢኖሩም የእርሱ ግን ለየት ያለ ነበረ ። ቢያንስ አራት ታላላቅ ችግሮች ነበሩበት ።
ይቀጥላል
ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ