የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጌታችን ጥምቀት

እንኳን ለ2016 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን ከሰማይ በትሕትና ወረደ ። የበላዮች ወርደው የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ እንዲያዩ የነገሥታት ንጉሥ አርአያ ሆነ ። የሕዝብ ሁሉ ጥያቄ “ወርዳችሁ እዩን” የሚል ነው ። በስማ በለው ሕዝባቸውን የሚያነጋግሩ ለሕመሙ እውነተኛ መድኃኒት መስጠት አይችሉም ። የነገሥታት ፀሐፊዎች ወደ ቤታቸው በጊዜ ለመግባት ደግ ፣ ደጉን ብቻ ያወራሉ ። የጸጥታ ኃላፊዎች የት ነበራችሁ? እንዳይባሉ ሰላም ሳይሆን ሰላም ነው ይላሉ ። ጌታችን ወርደህ እየን ሳይሉት ወርዶ እንደሚያየን ተስፋ ሰጠ ። ተስፋውንም ፈጸመ ። እርሱ ለኑሮችን ሩቅና እንግዳ አለመሆኑን ገለጠ ። ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠመቀ ። ጥምቀት ለእኛ እንጂ ለእርሱ ልጅነትን አያስገኝለትም ። በጥምቀቱ ልጅነቱ ተመሰከረ ። የወለደው አብ መሰከረ ።

ጌታችን የመሰወር ወራትን አደረገ ። ሠላሳ ዓመት ተሰወረ ። ብዙ መገለጥ የሚወድዱ ያለ ጊዜአቸው ይጨልማሉ ። በዝተንም እንዳንረክስ ፣ አንሰንም እንዳንረሳ ከሰዎች ጋር በወጉ መገናኘት ይገባል ። ሰው በር ቢዘጉ ጠንቋይ ነው ይላል ፣ በር ቢከፍቱ ዟሪ ነው ይላል ። ቢያቀርብ ክብሩን አይጠብቅም ይባላል ። ቢያርቅ አውሬ ነው ይሉታል ። የመሰወር ወራትን ማክበር ግን ያለ ጊዜው ከመሞት ይጋርዳል ። ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ ተገልጦ በ33 ዓመቱ ሞተ ። በዚህ መሠረት በ15 ዓመቱ ቢገለጥ በ18 ዓመቱ ሊገድሉት ይነሣሡ ነበር ።

ጌታችን ሠላሳ ዓመት ቅድስት እናቱን አገለገለ ። ሠላሳ ዓመት ከሕዝብ ማንነቱን ሰወረ ። ይልቁንም ላለፉት 18 ዓመታት በናዝሬት እንደ ተራ ሰው ኖረ ። የናዝሬት ነዋሪዎችም አልጠረጠሩትም ። በእውነት ወርዷልና ፣ በእውነት ታዝዟልና ። መጥረጊያ ይዘው የሚታዩ ባለሥልጣናት ፣ አቧራ የሚያጸዱ የበላዮች በእውነት ወርደው እንደሆነ አይታወቅም ። ቀጥለው በወርቅ ዙፋን እንደሚቀመጡ ይታወቃል ። ለቆፈረ እጃቸው የሐር መከዳ ይደረግላቸዋል ። ጭቃ ላልነካ እጃቸው ወንዝ ጠልፈን እናስታጥብ የሚል ይበዛላቸዋል ። ክርስቶስ ግን በእውነት ወርዶ ፣ በእውነት ታዝዞ ነበርና የናዝሬት ሰዎች አላወቁትም ። የምድር ገዥዎች ሌላውን ለማነሣሣት ለሠላሳ ደቂቃ መጥረጊያ ይይዛሉ ፣ ጌታችን ግን ሠላሳ ዓመት ሁሉን ታዘዘ ። በእውነት እንድንወርድ ፣ በእውነት ዝቅ እንድንል ይህ በዓል ያስተምረናል ። የጠላትነት ሁሉ መንስኤው አለመውረድ ነው ። አለመታዘዝ ነው ።

በዓሉን በባሕል ሳይሆን በአምልኮ ልብ ማክበር ይገባል። ቀኑ የተነሣሕያን ቀን እንጂ ኃጢአት የሚጨምሩበት ቀን አይደለምና ተራ ነገሮችን እናርቅ !

ይቀጥላል

በዓለ ጥምቀቱን የሰላም ያድርግልን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ