“ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤” ማቴ. 2፡3።
ሰብአ ሰገል “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው(” ብለው በታላቅ ናፍቆት በፈለጉት ጊዜ ሄሮድስና መላው የኢየሩሳሌም ነዋሪ ደነገጡ ። ሄሮድስ ለሥልጣኑ ሰግቶ ይደንግጥ ፣ ኢየሩሳሌም ለምን ደነገጠች ( ብለን መጠየቅ አለብን ። ሄሮድስ ለሥልጣኑ በጣም ስሱ ነበር ። ይህን ዜና ሲሰማ እንደ ቆሰለ አውሬ ሕዝቡን እንዳይፈጅ ፈርተው ነው ። መሢሕን የምትጠብቅ ኢየሩሳሌም መሢሕ ተወለደ ሲባል ለማየትም አልጓጓችም ። እንደውም ካለው ንጉሥ ጋር እንዳልጣላ ብላ ደነገጠች ። ታላቁ የምሥራች ለማያምኑት ታላቅ መርዶ ሆነ ። የሩቁ ያከበረውን ክርስቶስ የቅርቡ ሊያከብረው አቃተው ። ምን ጊዜም ክርስቶስን በሚመለከት ሦስት ዓይነት ወገኖች ይታያሉ ። ሄሮድስ ፣ ካህናትና ሰብአ ሰገል ናቸው ። ሄሮድስ ለክርስቶስ ጥላቻ የነበረው ሊገድለው የሚሻ ነው ። ካህናቱ ንቀት የነበራቸው ለአዳኙ ቸል ባዮች ነበሩ ። ሰብአ ሰገል ክርስቶስ የሚናፍቁት ፣ የሚወዱትና የሚሰግዱለት ናቸው ። ዛሬም እነዚህ ሦስት ወገኖች ይታያሉ ። ለክርስቶስ ፍቅርና ስግደት ከሌለን እንደ ካህናቱ ንቀትና ቸልተኝነት ፣ እንደ ሄሮድስ ጥላቻና ገዳይነት ይኖረናል ። የክርስቶስ የሆኑትን መጥላት ፣ መናቅ ዛሬም ካለ የማቴዎስ ምዕራፍ ሁለት ንባብ ሕያው ነው ።
ሰብአ ሰገል ከሩቅ አገር የሁለት ዓመት ጉዞ ተጉዘው የመጡ ናቸው ። ክርስቶስ በተወለደ ዕለት በቤተ ልሔም ሰማይ ላይ የነበረው የመላእክት ትእይንት በአገራቸው ሆነው ሳያዩት አልቀሩም ። ደግሞም በተፈጥሮና በከዋክብት እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ ታይቷል ። ሰብአ ሰገል የተፈጥሮ ሳይንስ ፣ የሥነ ፈለክ ፣ የመድኃኒት ቅመማ ፣ የባሕረ ሐሳብ ፣ የሒሳብ ሊቃውንት ሲሆኑ የዓለምን ሁኔታ ለነገሥታትና ለዓለም ሕዝብ የማሳወቅ ኃላፊነት ነበረባቸው ። ከነቢዩ ከዳንኤል በባቢሎን በፋርስ ምድር የክርስቶስን የመምጣቱን የሱባዔ ቍጥር ፣ የትንቢት ድርድር የሰማው የዞሮአስተር ተከታዮች ናቸው ። ሰብአ ሰገል የክርስቶስን መምጣት በሱባዔ ፣ በትንቢት ፣ በተፈጥሮ ለውጥ ተረድተው እንደ ተወለደ አወቁ ። አውቀው ዝም አላሉም ፣ ሊሰግዱለት መጡ ። ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ለየት ያለ የከዋክብት እንቅስቃሴ እንደ ነበር አጥኚዎች ደርሰውበታል ። የሚገርመው ሰብአ ሰገል ሥልጣን የነበራቸው ጠቢባን ነበሩ ። ለምርምር ሥራም የሚሆንና የዝና ትርፍ የሆነው ሀብትም ነበራቸው ። ንጉሥ ቤተ መንግሥት ይወለዳል ፣ እነርሱ ግን በበረት ያገኙትን ሕፃኑን አከበሩት ። የቦታና የጌጥ አምላኪዎች አልነበሩም ማለት ነው ፣ ሊቅ የላይ መለኪያ ሳይሆን የውስጥ ውበትን የሚፈልግ ነው ። ንጉሥ በዙፋን ላይ ያዩታል ፣ ጌታችን ግን በከብቶች ሣር ላይ ተኝቶ ነበር ። ንጉሥ ሠራዊት አሉት ፣ ጌታ ግን አረጋዊው ዮሴፍና እናቱ ማርያም ብቻ አጠገቡ ነበሩ ። ሰብአ ሰገል ክርስቶስን የፈለጉት ተሞኝተው አይደለም ፣ ሁሉ ከንቱ መሆኑን ጨብጠው አይተውት ነው ።
በጌታችን ልደት ላይ አሕዛብ ተጋበዙ ። የቤተ ክርስቲያን የወደፊት መልክ ተገለጠ ። ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብና ከአሕዛብ የተውጣጣች ናትና ። አዳም ምቾትን ፈልጎ ሞትን አመጣብን ፣ ክርስቶስ መስቀልን ተሸክሞ አዳነን ። ከመስቀሉ ምዕራፎች አንዱ በበረት መወለድ ነው ። ክርስቶስና መስቀል ተለያይው አያውቁም ።
በላቲን አሜሪካ ድሀ ስለ ሆኑት ፕሬዝዳንት ብዙ ተነግሯል ። እኒህ የዘመናችን መሪ የነበሩት አንዲት ቮልስ ዋገን መኪና የነበረቻቸው ያችንም የሚጠቀሙ ፣ በአነስተኛ የገጠር ቤታቸው የሚያድሩ ነበሩ ። ከመሪነትም ሲነሡም የዕለት ሥራ እየሠሩ መኖር ቀጥለዋል ። በዚህም ተከብረዋል ። ዓለም ራስዋ የምትፈልገው ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱ ፣ ውድ ቤተ መንግሥት የሚገነቡትን ሳይሆን የድሀ መልክ ያላቸውን ነገሥታት ነው ። “የዓለማችን ድሀው ፕሬዝዳንት ብለው ይጠሩኛል እኔ ግን ድሀ እንደ ሆንሁ አይሰማኝም ፣ ድሀ የሚባሉት የተቀናጣ ኑሮ ለመኖር የሚስገበገቡ ናቸው” በማለት የኡራጓዩ ፕሬዝዳንተ ሆሴ ሙጂካ ተናግረዋል ። እኒህ ሰው ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ይኖሩበት በነበረው የገጠር ቤታቸው ኑሮአቸውን ቀጥለዋል። ጥይት በማይበሳው መኪና ሳይሆን የ1987 ዓ.ም ስሪት በሆነችው ቮልስ ዋገን መኪና የሚሄዱ ነበሩ ። በፕሬዝዳንትነት ከሚያገኙት ደመወዝ 90 ከመቶውን ለድሆች ይሰጡ ነበር ። እኒህ ፕሬዝዳንት በ89 ዓመታቸው አርፈዋል ። በወቅቱ የነበሩት የኡራጓዩ መሪ የእኒህን ድሀ ፕሬዝዳንት ሞት አስመልክተው የሰጡት የኀዘን መገለጫ፡- “ስለ ሰጠኸን ነገር ሁሉ ለሕዝብ ስለነበረህ ጥልቅ ፍቅር እናመሰግናለን” የሚል ነበር ። እኒህ ድሀ ፕሬዝዳንት በሙስና ያልተከሰሱ የዓለማችን ፕሬዝዳንት ሊባሉ ይችላሉ ፤ እርሳቸውም ከሞታቸው ከዓመት በፊት፡- “ሞት የማይቀር ነው ፣ ምናልባት የሕይወት ጨው ሊሆን ይችላል” ብለዋል ። ስግብግቡ ዓለም መናኝ ነገሥታትን ፣ ድህነትን የመረጡ መሪዎችን ይናፍቃል ። ክርስቶስ ቅንጡ ሳይሆን የሕማም ሰው ሆኖ መጣ ። ነገሥታት መጠነኛ ኑሮን ካልመረጡ የሕዝብ ስቃይ እየጨመረ ይመጣል ። ይህንን ሊያስተምር የአይሁድ ንጉሥ በበረት ተወለደ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም.