ረቡዕ፣ ጥር 30 2004 ዓ.ም.
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ወደር በማይገኝለት የጨከነ ልብ ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ሳለ ደግሞም ዙፋኑን ከበው የሚያመሰግኑት ሳለ ይህን ክብሩንና ምሥጋናውን ትቶ በበረት መወለዱ በኋላም ለመስቀል ሞት መሰጠቱ የጨከነ ልብን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ብዙ ነገሥታት በዘመናቸው እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብዙ ሺህ ህዝብ አስፈጅተዋል፡፡ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች መበደላቸውን አምነው ሥልጣንን ከማስረከብ በሌላ ብልሃት ሥልጣናቸውን ለማርዘም ይታገላሉ፡፡ ስለሌሎች ጥቅም ክብርን መተው ጭካኔን ይጠይቃል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ በድህነት ያጠራቅሟትን ጥሪትና የቀየሷትን ጎጆ፣ በብዙ ጥረት የገዙትን ጀልባ ትተው ጌታን ለመከተል የጭካኔን ፈተና ማለፍ ነበረባቸው፡፡ ጳውሎስ ከተከበረበት ምኩራብ ለመውጣት፣ ከታወቀው መምህሩ ከገማልያል ለመለየት፣ ከሚወደው ህዝብ በአቋም ለመለያየት መወሰኑ ጭካኔን ያመለክታል፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ እግዚአብሔር ሲጠራኝ ከእግዚአብሔር ተሽሎ ማንን አማክራለሁ? ያለ ይመስላል (ገላ.1÷16)፡፡
አሁንም ጳውሎስ ተዳልሎ መኖርን በመጥላት ጴጥሮስን በግልጥ መቃወሙ (ገላ.2÷11)፣ ሰይፍ ይዞ የሚጠብቀውን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለረሃባቸው ምግብ ይዞ መሄዱ የጨከነ ፍቅር እንደሆነ ይገልጣል (ሮሜ. 15÷30-32) ነቢዩ ‹‹ልቤ ጨካኝ ነው፣ አቤቱ፣ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፣ እዘምራለሁ›› (መዝ.56(57)÷7) ብሏል፡፡ ጳውሎስና ሲላስ በእሥር ቤት፣ በእግር ብረት መካከል በእኩለ ሌሊት ይቀኙ ይዘምሩ የነበሩት ልባቸው ጨካኝ ስለነበረ ነው (የሐዋ.16÷25)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጭካኔን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ለዓላማው ጨካኝ ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጀግና ስለነበረ እንደሚሞት እያወቀ ወደ ኢየሩሳሌም በገሀድ በሆሳዕና ዝማሬ ገባ፡፡ ጀግና ማለት በራሱ ላይ ስለ ዓላማው የሚጨክን እንጂ በሰው ላይ የሚጨክን አይደለም፡፡ የጀግና መለያው ፍቅር ነው፡፡ ዓለም ግን አንድ የገደለውን ነፍሰ ገዳይ ስትለው ሺህ የገደለውን ጀግና ትለዋለች፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ጭካኔና ሰይጣን የሚያለማምደን ጭካኔ በጣም ይለያያል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጭካኔ በራሳችን፣ በመሻታችንና የእኔ በምንላቸው ላይ ስለክርስቶስ የምንወስደውን እርምጃ የሚገልጽ ነው፡፡ የዛሬው ዘመን ክርስትና ልል የሆነው በትርፍ ገቢያቸው እንኳ ጨክነው ጌታን የሚያገለግሉ ሰዎች የጠፉበት በመሆኑ ነው፡፡ ከሞት ይልቅ በጨከነ ልብ ካልተከተልነው እግዚአብሔር ሊሠራብን አይችልም፡፡ ራሳችንን ቀጥሎ በተጠቀሱት የጭካኔ ፈተናዎች እንገምግመው፡፡
- ክርስትናን የምንኖረው አይዞአችሁ በሚሉት ወገኖች መካከል ብቻ ነው?
- የእግዚአብሔርን ፍቅርና ማድረግ የሚገባንን የምናስታውሰው ስንሰበክ ብቻ ነው?
- ሰውን ሁሉ ያለ ልዩነት እንወዳለን? የሰውን ነጻ አመለካከት እናከብራለን?
- ስለሌሎች ሸክም ይሰማናል?
- የንስሃ ሕይወት አለን?
- ስለ ክርስቶስ ሁሉን ለመተው ድፍረት አለን?
- የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት ነው የምንታዘዘው? ወይስ የሚመቸንን እየመረጥን ነው ቡፌ የምናነሳው?
- ክርስቲያኖች በሌሉበትም ከክርስቶስ ጋር ለመኖር ውሳኔ አለን?
እግዚአብሔር የጨከነ ልብ ይስጠን!