መግቢያ » ትረካ » ጴጥሮስን አገኘሁት » የጴጥሮስ አማት

የትምህርቱ ርዕስ | የጴጥሮስ አማት

/ማር. 1፡29-31/
የመጋቢት ወር እየተፈጸመ የፋሲካ በዓል እየተቃረበ ነው ። የገሊላው ጴጥሮስም የክርስቶስን ጥሪ ሰምቶ ታንኳን ጥሎ ፣ ቤቱን ትቶ ከወጣ ሳምንታት እያለፉ ነው ። ሁለት ሰዎች አብረው ተኝተው አንደኛው ሕልም ቢያይ አብሮት የተኛው አብሮ ስላለ ብቻ ሕልምን እንደማይጋራ ፤ መንፈሳዊ ጥሪ ሲደርስም አብረውን ያሉት የታየን ላይታያቸው ይችላል ። ሰው እግዚአብሔር ሲጠራው እንኳን ከሰው ከልቡ ጋርም መማከር አያስፈልገውም ። አብርሃም ልጅህን ሠዋልኝ በተባለ ጊዜ በልጁ ላይ የእርሱን ያህል መብት ቢኖራትም ሣራን አላማከረም ። እግዚአብሔር ከአብርሃምም ከሣራም በላይ በይስሐቅ ላይ መብት አለውና ። ሐዋርያው ጳውሎስም ጥሪ በደረሰው ጊዜ ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከረም ። እኛን የጣመን ነገር አብረውን የሚኖሩትን ላይጥማቸው ይችላል ። መንፈሳዊው ነገር “የታየኝ ይታያችሁ” ከማለት በቀር በግብግብ የምናስረዳው አይደለም ። የገሊላው ጴጥሮስ የሚመጣውን ዓለም አይቶ ንብረቱን ጥሎ ወጣ ። መንግሥተ ሰማያት ተከፍቶ ይጠብቀው ዘንድ በሩን ክፍት አድርጎ መነነ ። እግዚአብሔር ሲጠራ እኔ ምን እሆናለሁ ? እነ እገሌስ ምን ይሆናሉ ? አይባልም ። እግዚአብሔር ሥራውን  ለሚሠሩለት ሥራቸውን ይሠራላቸዋል ። መንፈሳዊ ጥሪ ማለት ልባችን በደስታ ሲደልቅ ዙሪያችን ደግሞ የኀዘን ከበሮ የሚመታበት ነው ። ገንዘብ ስናገኝ ደስ ያላቸው ቤተሰቦቻችን ፣ የክርስቶስን ሕይወት ስናገኝ ሊከፉ ይችላሉ ። የሰውን ፊት እያዩ የመንግሥቱን ሥራ መሥራት በፍጹም አይቻልም ። ክርስቶስ ከወዳጅ አስጥሎ ወዳጅ ፣ ከዘመድ ለይቶ ዘመድ የሚሆን ነው ። ስለ እርሱ የሚጎዳንን ነገር ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመንንም መተዉ ይገባል ። እርሱ ዓለም ከምትሰጠን ረብ በላይ ነውና ።

የክረምቱ ወራት እያለፈ የጽጌው ወራት እየመጣ ነው ። ፋሲካ በአደይ አበባ ተከቦ የሚውል ነው ። በጴጥሮስ ቤት ግን ትልቅ ግራ መጋባት ተከስቷል ። የጴጥሮስ ሚስት ትግ ፣ ትግ ትላለች ። መለስ ብላ “በስተርጅና ዲቁና” በማለት በመገረም ብቻዋን ትስቃለች ። ክርስቶስ የባሏን እሺታውን እንጂ ጉልበቱን እንዳልፈለገ አልገባትም ። አሁን በአሳብ ትወስዳለች ። “ቤቴን ያፈረሰው ያ እንድርያስ ነው ። ጎበዙን አባወራ ጎበዝ ሐዋርያ ልናደርገው ነው እያለ ሲናገር ሰምቻለሁ ። እንድርያስ ተናግሮ የሚያስቀይም ባይሆንም አሁን ልቀየመው ነው ። መጥምቁ ዮሐንስ ጋር ከጥብርያዶስ እስከ ዮርዳኖስ ሲመላለስ ዓመታት አለፉ ። መጥምቁ ዮሐንስም ከዚህ በኋላ እኔን ሳይሆን ክርስቶስን ተከተሉ በማለት ወደ ክርስቶስ እንደ መራቸው ሰማሁ ። እንድርያስም እኔን ሳያስፈቅድ ወስዶ ከክርስቶስ ጋር ጴጥሮስን አስተዋወቀው፣  ያን ቀንስ ጴጥሮስም በጀ አላለም ። ነገር ግን ኬፋ ብሎ ስም እንዳወጣለት ነግሮኛል ። እኔም ቦጅቧጃ ነውና እንደው ያድርግልህ ብዬ መርቄዋለሁ ። ወላጆቹ ስምዖን ብለውት እንደ ሸንበቆ ሲወዛወዝ የኖረ ነው ። ባለማወቅ ቢያስቀይምም ቶሎ ብሎ ይቅርታ ሲል ሆድን ያራራል ። በጴጥሮስ ቤት ቂም ዕድሜዋ አጭር ነው ። ቀኑ ሳይመሽ የጠቆረውን ፊት በይቅርታ ያበራል ። ሰውን እንቅልፍ ነሥቶ እንቅልፍ የሚተኛ አልነበረም ። እንባውን እንደ ነሡት ልጅ ሲያወርደው ወንድ ሴቱ ይለመነዋል ። ታዲያ ኬፋ አለኝ ብሎ ሲነግረኝ በምን አወቀህ ብዬው ነበር ። ያን ቀንስ አላሳዘነኝም ። አሁን ግን እንደ ወጣ ቀረ ። የመጨረሻው ቀን ምን ነበረ ብዬ ታንኳ ላይ የሚያግዙትን ጨቅላዎች ጠይቄ ነበር ። እነርሱም ያሉኝ ክርስቶስ ትላንትና በዮርዳኖስ አግኝቶት ነበረ ፣ ዛሬ ደግሞ በጥብርያዶስ ሊፈልገው መጣ አሉኝ ። ክርስቶስ ጉዳይ ከጀመረ ማብቂያ የለውም በማለት ነግረውኛል ። በጥብርያዶስም በተአምራት ብዙ ዓሣ ካጠመደ በኋላ ሁሉን ትቶ እንደ ተከተለው ሰማሁ ።”
የጴጥሮስ ሚስት በጓዳዋ በትካዜ ሁና ይህን ስታስብ የእናቷ ማቃሰትና እሪታ ከእንቅልፍ ዓለም ፣ ከቁም ሰመመን ፣ ከአሳብ ሰፈር መለሳት ። “ምነው አመመሽ ?” ብላ ወደ እናቷ ስትጠጋ ንዳዱ አያስቀርብም ነበር ። በተቆራረጠ ድምፅ ፣ እልህ በተናነቀው ቅላፄ፡- “እስከ ዛሬ የምወደው አንቺን ሳይሆን ጴጥሮስን በረ ፣ አሁን ሆዴ ተቀየመው ። ሰው ከነፍሬው አይሞትም ይሉ ነበር ፣ ለእኔ ግን ሰው ከነፍቅሩ አይሞትም ቢባል ይሻለኛል ። ጨጓራዬ ነደደ ። በስተርጅና ቤት ለቆ ከወጣቶች ጋር ክርስቶስ የተባለውን እከተላለሁ ሲል አዘንሁ ። ይኸው በንዳድ አለሁ ። እስቲ ውኃ አፍስሽልኝ” አለቻት ። ንዳዱ ግን መብረድ አልቻለም ። “ምነው የእስራኤል አምላክ ጀምበሩን አስቀያሚ አደረግህብኝ ። ጀምበር ሲዋብ እንጂ ሲያስጠላ ልክም አይደለም” አለች ። እንደ ምንም ብላ የደጁን ነፋስ ፣ ከጥብርያዶስ የሚምዘገዘገውን አየር ብትስብም ንዳዱ ግን መለስ ማለት አልቻለም ። ትኩሳቱ እየጸና መቃዠት ስትጀምር የጴጥሮስ ሚስት በትዳር እጦት ላይ የእናት ሞት ሊገጥማት መሆኑን አስባ በጩኸት አቀለጠችው ። ማንም ግን ሊደርስላት አልቻለም ። “ትዳሬ የከዳኝን ማን ይደርስልኛል” ብላ ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች ።
ያ ሩኅሩኅ ጴጥሮስ፡- “ሚስቴን ሳልሰናበታት መምጣቴ እንጂ ሌላ ምን የሚቀጨኝ ነገር አለ” በማለት በልቡ ያሰላስል ነበር ። የተባረከው አምላክ ክርስቶስ ግን የጴጥሮስን የልብ ማዕበል ይሰማል ። ሁሉን አዋቂ ነውና ። በአማቱ የተለኮሰውን እሳት ፣ ሚስቱ የገባችበትን የአሳብ አዘቅት አሻግሮ ያደምጣል ። ሁሉ በሁሉ ነውና እዚያ ለመድረስ መሄድ አያስፈልገውም ። እዚህ ሁኖ እዚያም አለና ። ሁሉንም የሚወዘውዛቸው አለማወቅ ነውና አዘነላቸው ። አላዘነባቸውም ። “ዮሐንስ” በማለት ጠራው ፣ ያዕቆብም የተጠራ ያህል መጣ ። “ተነሡ ወደ እንድርያስና ወደ ጴጥሮስ ቤት እንሄዳለን” አላቸው ። ጴጥሮስም የልቡን ያወቀበት መስሎት በሐፍረትም በደስታም ተነነ ።
የጴጥሮስ ሚስት መስኮቱን ከፍታ የጽጌውን ወራት ነፋሻ አየር ትስባለች ፣ የገብሱ ዛላ ከምበል ደፋ ሲል ታያለች ። የሚያስደስተው እንዳያስደስታት በልቧ ቂም ሞልታል ። የተቀየመችው የምትችለውን ባሏን ብቻ ሳይሆን የማትችለውን ክርስቶስንም ነበር ። ማዶ እያየች በትካዜ ስትወጠር በሩ ተንኳኳ ። ቀድሞ የገባው እርሱ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን በብርሃናዊ ፊቱ ፣ በፍቅር ድምፁ ለየች ። ቢመጣ ይህን እለው ነበር የምትለው ሁሉ ሲመጣ ጠፋት ። ለጴጥሮስ ቀዳሚ ሁኖ ገባለት ። ከእርሱ በኋላም ዮሐንስ ፣ ያዕቆብና የተቀየመችው እንድርያስ ገቡ ። ጌታም ሳይቀመጥ የጴጥሮስን አማት ሊያገኝ ሰተት ብሎ ገባ ። ጓዳን ሳያስፈቅድ ያያል ፣ ያየውን ግን ይሸፍናል ። መታመሟን የነገሩት ያህል አውቋል ። በላብ ተጠምቃ ማንም የማይቀርባትን አሮጊት ጌታ ቀርቦ ዳሰሳት ። እርሱ ለምጻሙን ሲዳስስ እረክሳለሁ አይል ። ምስኪንን ሲጠጋ እቆሽሻለሁ ብሎ አይሰጋም ። እጆቿን በእጆቹ ያዘና በሥልጣን ቃል አሥነሣት ። ንዳዱ ለቋት ሲሄድ ታወቃት ። ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው ። እርስዋም እየሳቀች እመጣለሁ ብዬ አስቤ ነበር በማለት አንድ ግጥም ስትናገር ሁሉም ሳቁ፡-
ዓርብ ተጠንስሶ ለቅዳሜ አይደርስም ፣
የሰው መላክተኛ የልብ አያደርስም።   
ጌታ ግን ለአማቱና ለሚስቱ አንዴ ስሙኝ ብሎ ተናገረ፡- “ጴጥሮስ እኔ ጋ ቢሆን የእናንተም ይሆናል ፣ የእናንተ ቢሆን ግን የማንም ሳይሆን ይቀራል   ። ገሊላ ሳይሆን ሮም ቆሞ ገና ስለ እኔ ይመሰክራል ። በእርሱ መጠራት ቅር እንዳይላችሁ” አለ ። የጴጥሮስ አማትም “ንስሐዬን እናገራለሁ” ብላ ዘረዘረችው ። ጌታም ወደ ዮሐንስ ዞር አለና፡- “እንዳትረሳ አሁን የምነግርህን በልብህ መዝገብ ጻፈው” አለው ። “ጴጥሮስ ለአገልግሎት ሲወጣ ሚስቱን ይዞ እንዲዞር ይሁን ። ቤተ ክርስቲያን ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሚስቱም በጀት ይኑራት ። ሀገረ ስብከት ስታደላድሉ ለጴጥሮስ ኢየሩሳሌም መንበሩ ይሁን አለው ።
ታላቅ ግብዣ በዚያ ቤት ሆነ ። ቅድም የኀዘን ክረምት ነበረ ። አሁን ግን የደስታ ፀደይ ሆነ ። ሲሠራ አይገደው ! ! !
ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም