የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፈካ አበባ

 

ወዳጄ ሆይ !

ሞት በተጋረጠበት ዘመን በሕይወት የሚያሻግር እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ከሞት ውጭ ያሉ ፈተናዎች ሕይወትን እንድትወዳት አሊያም እንድትጠላት ያደርጉሃል ። ሕይወትን የምትወዳት ታመህ ለመዳን ፣ ተሰደህ ጥግ ለማግኘት ፣ አጥተህ ለመባረክ ስትሻ ነው ። ሕይወትን የምትጠላት ደግሞ በመሰልቸትህና ዛሬ የዓለም ፍጻሜ ሆኖ ሲሰማህ ነው ። ከፊት ለፊት ያለው ጅረት አጭር ቢሆንም ሩቅ ነው ። ከፊትህ ያለው ደራሽ ውኃ ከኋላህ ሲሆን ትዝታም አይኖረውም ። 

ወዳጄ ሆይ !

የደቦ ሹመት በደቦ ጩኸት ያበቃል ። የሹመት ሠረገላህን መውረድህን እያሰብህ ተሳፈራት ። ስትወርድም ያንተ የሆነችውን ሀብት አትተዋት ። መክበር እንዳለ መዋረድ ፣ ማግኘት እንዳለ ማጣት አለና ከመሬት አትራቅ ። ወደ ሰማይ ማየት እንጂ ወደ መሬት እያዩ መኖር ስጋት ነው ። እርሱም የዚህ ዓለም ከፍታ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ናፍቆት በውስጥህ ከሌለ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ዕቃ እየኖርህ ነው ። ከሩቅ የመጣው የሚመዝንህ አብሮህ ላለው በምትሰጠው ክብር ነው ። እደርሳለሁ ሳትል ዛሬን ካየህ ነገም በእግዚአብሔር እጅ ነው ። ለሞቱ ቀርቶ ላሟሟቱ የሚለቀስበት ዘመን ነውና ተግተህ ጸልይ ። የሰጠ እጅህ ሲነከስ የተቸነከረውን መድኃኔ ዓለምን አስታውስ ። ደግ አልቆ የተሻለ ክፉ ሲመረጥ ያ ዘመን የዘመን ልቅላቂ ነው ። ወዳጅ በዕንቈም አይገዛም ። 

ወዳጄ ሆይ !

ስለ ፀሐይ አመስግነህ ፣ ስለ ዝናብ እግዚአብሔርን አወድሰህ የማታውቅ ከሆነ ስለሌላ ለማመስገን አትጠበቅም ። ጠበሉ ሲቀዘቅዝ እሰይ እሰይ ፣ ሲያቃጥልም እሰይ እሰይ ይባላል ። የተሰጠህን ነገርም በምስጋና ተቀበል ። የተሞላ ሰው እስኪያወጣው ፣ ጥይት ያቃመ ሰውም እስኪጨርሰው ጠብቀው ። ባዶ ሆኖ ታገኘዋለህ ። 

ወዳጄ ሆይ !

መልእክት መልአክ ይፈልጋል ። መልአክ የሌለው መልእክት እግር አልባ ፣ መልእክት የሌለው መልአክ ዱዳ ናቸው ። ዛሬ ትላንት ፣ አንተም ሬሳ ሳትባል እወቅበት ። ንዴት የትዕግሥት ድህነት ነው ። ንዴት ካጣኸው በላይ ያሳጣሃል ። ንዴት ለቅጽበት በውስጥህ የተደበቀውን አውሬ ያወጣዋል ። የሚገርመው ያ አውሬ ወጥቶ አለመቅረቱ መልሶ መደበቁ ነው ። ለመውጣት የፈለከው መሰላል ለመውረድም ያስፈልግሃልና ከበርሁ ብለህ ሕዝብ አትናቅ ። 

ወዳጄ ሆይ ! 

በረከሰች ከተማ መቀደስ እንደ ሎጥ ፣ በተቀደሰች ገነት መርከስ እንደ አዳም አለና ልብህን መርምር ። አባቶቻችን ሰው ቦታን ፣ ቦታም ሰውን ይቀድሳል ያሉትም እውነት ነው ። እርሱ ነው ከማለት እኔ ነኝ ማለት ማዕበልን ያበርዳል ። የጀመረ ካልጨረሰ አይከብርም ፣ የጨረሰም ካላመሰገነ አይደሰትም ። የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ ነውና ደስ ይበልህ ። ይታዩ ዘንድ ከተማውን የዞሩ ፣ ይደበቁ ዘንድ ዋሻውን ያጣሉ ። በመካከላችን እግዚአብሔር አለና እውነት እንነጋገር ። 

በቸር ዋሉ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ