የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፍለጋ ማብቂያ

“በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን ።” ኤፌ. 2 ፡ 6-7 ።

የሚመጡ ዘመናት አሉ ። የሚመጡ ዘመናት ሲል ሁለት ጉልህ ነገሮችን ይገልጣል፡- የመጀመሪያው ትንሣኤ ልቡና አግኝተን በእምነት በምግባር የምንኖርበት እስከ ዕለተ ሞታችን ያለው ጊዜ ነው ። ትንሣኤ ልቡና ማለት አማኝ በድኅነት ጸጋ የሚከብርበት ፣ ክርስቶስን የማግኘት ጥልቅ ትርጉም ነው ። እምነትም ለማይታየው እግዚአብሔር የምንሰጠው ምላሽ ሲሆን ምግባር ደግሞ ለሚታየው ዓለም ተማጽኖ የሚታይ ሥራ የምንሠራበት ነው ። ይህ ዓለም በማይነገር መቃተት ከክርስቲያኖች የሚታይ ምግባር እየፈለገ ነው ። ፍቅርን ተርበው ያሉ በነጻ የሚወዳቸው ፣ በጎነታቸውን አጉልቶ ክፋታቸውን አሳንሶ የሚቀርባቸው እየፈለጉ ነው ። የቸርነት እጆችን ብናገኝ ወራሪ ሁኖ የመጣብንን ረሀብ ድል እንነሣው ነበር እያሉ የሚከጅሉ አያሌ ወገኖች አሉ ። የቅን ፍርድን ብናገኝ ሞት ሕይወት ይሆንልን ነበር በማለት ፍትሕን የተጠሙ ወገኖች በዝተዋል ። ክርስቲያኖች ከማይታየው እግዚአብሔር ጋር ስላላቸው የእምነት ግንኙነት መተንተን አንችልም ። ጸሎታቸውን ፣ ንስሐቸውን እነርሱ ያውቁታል ። ለተጨነቀው ዓለም ግን እየሰጡ ያለውን ምላሽ ሁሉም ሊናገረው የሚችለው ነው ። እንኳን ለጠፋው ዓለም ይቅርና እርስ በርስ የሚዋደዱ ክርስቲያኖችን እያጣን ነው ። አረማውያን ሌላውን ለማጥቃት የቡድን ፍቅር ፣ ዘረኞች እነርሱ ብቻ ለመኖር የጎሠኝነት ጽዋ በሚጠጡበት ዘመን ክርስቲያኖች ወይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ንጹሕ ፍቅር ፣ ወይ ከመደምሰስ የሚያድን የቡድን ፍቅር አጥተው ይኖራሉ ።

ቅዳሴ ላይ ጉቦ የሚቀባበሉ ፣ በፖሊስ ላለመታየት አምልኮውን የተዳፈሩ ፣ መላእክትን የዘነጉ ብዙ አማንያን አሉ ። ሁለት ትዳር ይዘው በክሬ አትምጡብኝ እያሉ የሚተዉኑ አያሌ ናቸው ። ከቤተ ክርስቲያን መልስ መንደሩን በነገር የሚያቃጥሉ ቍጥር የላቸውም ። በኢየሱስ ስም እያሉ ሰውን ሲያስለቅሱ የሚውሉ በየቢሮው የተሰገሰጉት ባለጭምብሎች ፣ ደጉን ክርስቶስ ዓለም እንዲጠላው እያደረጉ ነው ። ክርስቲያን ነኝ ማለት ኢትዮጵያዊ ነኝ እንደ ማለት የዜግነት ስም ያደረጉት ብዙ ናቸው ። ጨካኝ ሁኖ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል ፣ ሰው እያረዱና እያስቀሉ ክርስቲያን መሆን ግን አይቻልም ። ትንሣኤን ተነሥተን ብናከብር እግዚአብሔር ደስ ይለው ነበር ። የዓመት ፈቃድ የወጡ ጠጪዎችና አመንዝራዎች በበዓሉ ቀን ወደ ቀደመ ሥራቸው ይገባሉ ።

በጥንቱ ዘመን ምዕራብና ምሥራቅ ተብሎ ክርስትናው በአቅጣጫ በተከፈለበት ጊዜ ክርስቲያን ወንድሙን ከአላውያንና ከአረማውያን ጋር ወግኖ ወግቶታል ። ወንድሙን ገድሎ ሲመለስ ግን አንተም ካድ ተብሎ በሰይፍ ሃይማኖቱን ጥሏል ። ባመንን ቀን በክርስቶስ ፍቅር አምነናል ፣ በመጨረሻው ቀንም ለሰዎች ያለን ፍቅር በስድስቱ ቃላተ ወንጌል ይዳኛል ። ትንሣኤ ልቡና የነፍስን መነጽር የሚወለውል ፣ ለበጎ ሥራ የሚያነቃቃ ፣ ሕይወት ባለው ግንኙነት የሞተውን ዓለም የሚታደግ ፣ የአድራሻ ለውጥ በማድረግ የቀደመ ኑሮን በጽድቅ ግብር የሚበቀል ነው ። ዘመኑና ተግባሩም እስከ ዕለተ ሞት ነው ። ከዕለተ ሞት በኋላ የበጎ ሥራ ሽልማት እንጂ የበጎ ሥራ ዕድል የለም ።

የሚመጣው ዘመን ሁለተኛው ትንሣኤ ሥጋ አግኝተን ከክርስቶስ ጋር የምንኖርበት ነው ። የሚበዛው ዘመን ያለው ወደፊት ነው ። በዚህ ዓለም ያለው የትኛውም ዘመን ፣ እንደ ማቱሳላ የሺህ ዓመት ድንበር ብንነካም የሚመጡት ዘመናት ብዙ ናቸው ። በዚህ ዓለም ብንጎዳ በማያልፈው ዓለም እንጠቀማለን ። በዚህ ዓለም ተጠቅሞ በማያልፈው ዓለም መጎዳት ግን ከባድ ነው ። ዓለም ከንቱ ነው ስንል ደስታውም ኀዘኑም ኃላፊ ነው ማለታችን ነው ። ስለዚህ በደስታውም በጣም አለመደሰት ፣ በኀዘኑም በጣም አለማዘን ይገባል ፣ ከንቱ ነው የሚለው ቃልም ሚዛንና ልክ መስጫ ነው ።

በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ያለው ቸርነት ብዙ ነው ። እግዚአብሔር አብ የእጁን ብቻ ሳይሆን ልጁን ሰጥቶ ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ረቂቅ ነው ። ልጁ ራሱም ስጦታ ነው ። ልጁ ራሱም ሰጪ ነው ። ቸርነት በዝቶልናል ። በዓለም ላይ ያሉ በቢሊየን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ቤተሰባችን ናቸው ። ይህ ቸርነቱን የሚገልጥ ነው ። በቤተ ክርስቲያንም የህልውና መጀመሪያ ይሆን ዘንድ ልጅነትን በጥምቀት ሕይወትን በሥጋ ወደሙ ሰጥቶናል ። በየዕለቱ የምናገኘው የቃሉ ገበታም ትልቅ በረከታችን ነው ። እግዚአብሔር የስጦታውን ብዛት አትረፍርፏል ። በእርሱ እውቀት ውስጥ ብቻ የተሰወረች ርስተ መንግሥተ ሰማያትንም ስናስብ የሆነልን ብዙ ነው ። አሁን በቤተ ክርስቲያን ያለው ጸጋ በረከት ቅምሻ ሲሆን በመንግሥተ ሰማያት የሚገለጠው ግን ከቃላት በላይ ነው ። በሰማይ ላይ የሚታየውን ውብ ቀስተ ደመና ወደ ታች ስበን በወጠርነው የሥዕል ሸራ ላይ ማተም እንደማይቻለን የመንግሥተ ሰማያትን ደስታ በዚህ ዓለም ማምጣትም መናገርም አይቻልም ።

ይህን የመንግሥተ ሰማያት ደስታ ለመካፈል ሁለት ነገሮች ይቀድማሉ ። የመጀመሪያው ከክርስቶስ ጋር መነሣትና ከክርስቶስ ጋር መቀመጥ ነው ። ለመነሣት መሞት ያስፈልጋል ፤ ያልሞተ አይነሣምና ። ለመቀመጥም ከፍ ማለት ይጠይቃል ፣ ያላረገ በሰማያዊ ስፍራ አይቀመጥምና ። ከክርስቶስ ጋር መሞት በጥምቀት የምንገልጠው ትእምርት/ምልክት ሲሆን ዓለምን ክጃለሁ የምንልበት ምስክርነት ነው ። ለዓለም ሞቻለሁ በማለት ቀድሞ የምንኖርለትን ነገር መለወጥ ነው ። የቀድሞ የመጠጥ ወጪአችንን ፣ የዝሙት በጀታችንን ለስብከተ ወንጌል ማድረግ እርሱ መሞት ነው ። ከክርስቶስ ጋር መቀመጥም እርሱ ራስ ነውና ራስ ባለበት አካል ይኖራል ። ከክርስቶስ ጋር መዋሐድ በቀኙ መቀመጥ ነው ። መቀመጥ የሚለው ቃልም መደላደልና ማረፍን የሚያመለክት ነው ። ክርስቶስ የፍለጋ ሁሉ ማብቂያ ነውና ።

በጥላህ አኑረን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ