የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፍቅር ትንታኔ

እንኳን ምድራዊ ሀብትና እውቀት ይቅርና ሰማያዊ ጸጋዎችም ያለ ፍቅር ባዶ ናቸው ፡፡ ፍቅርን ስትይዝ ሁሉንም ጸጋ ያዝህ ማለት ነው ፡፡ የሃይማኖት መሠረትና ጉልላት ፍቅር ነው ፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ስፍራ አጥተህ ይሆናል ፣ ፍቅር ግን ምድባ የማያስፈልገው ተፈላጊ አገልግሎት ነው፡፡ ፍቅር ካለህ እግዚአብሔር ባንተ ልብ አለ ፣ አንተም በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ አለህ ፡፡ ፍቅር ድል አለው ፡፡ ስለ ጸጋ ስጦታዎች ብዙ ጭቅጭቅ አለ ፣ ስለሚበልጠው ጸጋ ስለ ፍቅር ግን ስብከት እንኳ ጠፍቷል ፡፡ ስለ ፈውስ ብዙዎች ይለምናሉ ፣ ነፍስን ስለሚፈውሰው ፍቅር ግን አይጸልዩም ፡፡ የፈውስ ጸጋ ባይኖረን ችግር የለውም ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ነገር በእውቀት ፣ በእምነትና በፍቅር ካልተደረገ ኃጢአት ነው፡፡ ጳውሎስ በጥላውና በልብሱ ቅዳጅ በሽተኞችን ይፈውስ ነበር ፣ እርሱ ግን በብርቱ ራስ ምታት ይቸገር ነበር ፡፡ ዓይኑም በዚህ ምክንያት ደክሞ ፣ ሰውነቱም ደቅቆ ነበር ፡፡ የፈውስ ጸጋ ያላቸው ሊታመሙ ይችላሉ ፡፡ ፍቅር ግን ያለው ነፍሱ ተፈውሳ ሌሎችን ይፈውሳል ፡፡
ትንፋሽህ ድንገት የሚቋረጥ ሲመስልህ ፣ የልብህ ምቶች የቀዘቀዙ መስሎ ሲሰማህ ፣ ተስፋህ ጭልጥ ሲልብህ የምትድነው በፍቅር ብቻ ነው ፡፡ እንጨት በምስጥ ፣ እህል በነቀዝ ፣ ልብስ በብል ይበላል ፤ ሰውን ጥላቻ ይገዘግዘዋል፡፡ ሌሎች ጸጋዎች በኃይል እንዲሠሩ ሞተሩ ፍቅር ነው ፡፡ ፍቅር ከሌለ ሰማዕትነት ሊኖር አይችልም ፡፡ በየዕለቱ ሰማዕትነት ላይኖር ይችላል ፣ በየዕለቱ መሥዋዕትነት አለ ፡፡ እርሱም ጥላቻን እንቢ ማለት ነው ፡፡ በሁሉ ቦታ ፣ በሁሉም ደረጃ ፣ በሁሉም ጸጋ ውስጥ ፣ በሁሉም ዘመን ደግሞም ለዘላለም የሚፈለግ ፍቅር ብቻ ነው ፡፡ በፍቅር የማይቃጠሉ ልቦች ወንድማቸውን ለመስቀል ይጨክናሉ ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቆመችበት ምሰሶ ፍቅር ነው ፣ ያለ ፍቅር ትወድቃለች ፡፡
ፍቅር ራሳችንን በሰው ውስጥ ሰዎችን በራሳችን ውስጥ የምናይበት መስተዋት ነው ፡፡ ፍቅር ያላቸው ሌሎችን የማስከተል አቅም አላቸው ፡፡ ፍቅር በቀላሎች ሰፈር ያላት ስያሜ ምስኪንነትና ፍርሃት ነው ፡፡ መንገዶችን ከመሥራት ፍቅርን መገንባት ይቀድማል ፡፡ የተሠሩ መንገዶች በጥላቻ ይዘጋሉ ፡፡ ትልቁ ርእዮተ ዓለም ፣ የማይከሽፍ መሳሪያ ፍቅር ብቻ ነው ፡፡ ፍቅር ትልቁ ስጦታ ፣ ትልቁ መንገድ ፣ ትልቁ መሪ ነው ፡፡ በመጨረሻው ቀን የሃይማኖት መግለጫ ሳይሆን የሃይማኖት ልጅ የሆነው የፍቅር መግለጫ ይነበባል ፡፡
ዓይን ያለ ፍቅር ካላየ ምን አገባኝ ይላል ፡፡ ጆሮ ያለ ፍቅር ከሰማ ይፈርዳል፡፡ ምላስ ያለ ፍቅር ከወጣ ይሰብራል ፡፡ እጅ ያለ ፍቅር ከተዘረጋ ይጥላል ፡፡ እግር ያለ ፍቅር ከሄደ ድልድይ ያፈርሳል ፡፡ ፍቅር የሌለው ነቢይ ዓይኑ የታመመ ነውና ባሻገር አያይም ፡፡ ፍቅር የሌለው ሐዋርያ ልሳኑ ተይዟልና የሚናገረው አይሰማም ፡፡ ፍቅር የሌለው ሰማዕት ክርስቶስን አላወቀምና በከንቱ ይሞታል ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደ ጎደሉን ብንናገርም በዋናነት የጎደለን ፍቅር ነው ፡፡ ፍቅር በመጨረሻው ዘመን ይቀዘቅዛል እንጂ አይጠፋም ፡፡ የክርስቲያን ፍቅር ከመንበረ ሥላሴ የሚቀዳ ነውና አይነጥፍም፡፡ ያለ ፍቅር የተሰበኩ ነፍሰ ገዳይ ይሆናሉ ፡፡ ለማፍቀር የልብ ፈቃድና የእግዚአብሔርን ፍቅር ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡ ጠጥቻለሁ ግን አልረካሁም ካልህ ፍቅር ጎድሎሃል ማለት ነው ፡፡ ፍቅር በግልጽነት የምትከብር ናት ፡፡ ፍጹም የምትሆነውም ፍርሃትን ስታሸንፍ ነው ፡፡ ፍቅር ራሷ ጌጥ ናትና ጌጥ አትፈልግም ፡፡
ፍቅር ጽንፍ የለሽ ናትና ዘረኝነት አይስማማትም ፡፡ ተብራርቶ ያላለቀ ትንታኔ ፍቅር ብቻ ነው ፡፡ በፍቅር ያጌጡ በወርቅ ከተንቆጠቆጡ ይበልጣሉ፡፡ ምኞት ዳርቻ ፣ ጥማትም እርካታ የሚያገኘው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ ያለ ፍቅር የተዘረጉ ምጽዋቶች ከዱላ አይተናነሡም ፡፡ ኅሊናውን አጉድለን ሆዱን የሞላንለት ከሰጠነው የሰረቅነው ይበዛል ፡፡ ፍቅር ሁሉም ሰው የሚሰጠው ምጽዋት ነው ፡፡ ፍቅርን የማይሰጥ ድሀ ፣ የማይቀበል ባለጠጋ የለም ፡፡ ጎዶሎዎች ሙሉ የሚሆኑት በፍቅር ብቻ ነው ፡፡ ሩጫህን የጀመርከው ያለ ጭብጨባ ብቻህን መሮጥ የጀመርህ ቀን ነው ፡፡ የታየህን እይ እንጂ የሚያዩህን አትይ ፣ ትወድቃለህና ፡፡
ሁለት ጽንፎችን የሚያጋጥም የመዐዘን ራስ ድንጋይ ፍቅር ነው ፡፡ በየዕለቱ የምንጎድለው ከፍቅር ነው ፡፡ ፍቅር በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ይመራናል፡፡ ፍቅር ሰዎችን ካላገኘ ተግባራዊ አይሆንም ፡፡ ፍቅር እግዚአብሔር የፈጠረውን መውደድ ነውና ለእንስሳትና ለእጽዋትም ይተርፋል ፡፡ እግዚአብሔር ያልፈጠረውን ኃጢአት ፍቅር ይጠላል ፡፡ የሰላም መገኛ ፍቅር ናት ፡፡ እግዚአብሔር የቆሰለውን ዓለም ለማዳን የተጠቀመው ብቸኛ መሳሪያ ፍቅር ነው ፡፡ የተለያየ ጸጋን አንድ የሚያደርግ ፍቅር ነው ፡፡ ፍቅር ከሙያ ይበልጣል ፡፡ 
የደስታ ቋጠሮ/15
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 13/2010 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ