የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያለውን ያደርጋል /ሐዋ. 27፡25/

                                 ቤተ ጳውሎስ ሰኞ ነሐሴ 28/2004 ዓ.ም
በዓለማችን ላይ ያሉትን ያደረጉ ሰዎች ብናገኝም እንኳን ከተናገሩት ባነሰ መጠን የተጓዙ ናቸው፡፡ ሕይወትን ልዩ የሚያደረጋት ስጦታ መሆኗ ብቻ ሳይሆን በጀቷም ሰማያዊ መሆኑ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቀን የራሱ በጀት አለው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ለፍጥረት ሁሉ የዕለት በጀት ይመደባል፡፡ ነቢዩ፡- “የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፣ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፡፡ አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን  ታጠግባለህ” ይላል /መዝ. 144፡15-16/፡፡
        ወደ ዓለም የመጣነው በእግዚአብሔር መንግሥት ፈቃድ እንደሆነ ሁሉ የመኖር ዓላማችን ሙሉ የሚሆነውም በፈቃዱ ስንኖር ብቻ ነው፡፡ ሰው ሆኖ መፈጠርና ሰው ሆኖ  መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እንደ ሰው ተፈጥረው እንደ ሰው ሳይኖሩ ያለፉና ዛሬም የማይኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ላልተፈጠሩበት ዓላማ ስለሚኖሩ ለራሳቸው ሳይመቻቸው ለሌላውም ሳይመቹ ያልፋሉ፡፡ ዓለማችን እነዚህን ሁለት ወገኖች ታስተናግዳለች፡፡ ለብዙዎች የእግዚአብሔር ፈቃድ ጉድለት ስለሚመስላቸው በራሳቸው ጎዶሎ ፈቃድና እርካታ በሌለው ሕይወት ይባክናሉ፡፡ ከሕይወት በረከቶች አንዱ መርካትና ዕረፍት ነው፡፡
        ከላይ በርእሱ በተጠቀሰው ምዕራፍ ላይ የምናገኘው ታሪክ መንገደኞችን የያዘ መርከብ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህቺ መርከብ የሕይወት መርከብ ተጓዦችን በምሳሌነት ትገልጣለች፡፡ በውስጧም የተለያዩ ወገኖች አሉ፡፡ መርከቢቱ በባሕር ላይ የምትጓዝ እንደ መሆኗ ለጉዞዋ እርግጠኛ የሚያደርጓት የተለያዩ ነገሮች ያስፈልጓታል፡፡
 የመጀመሪያው፣ ስለ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ እርግጠኛ መሆን፣
ሁለተኛ፣ በጉዞው ላይ ለሚከሰት ችግርና አደጋ ዋስትና፣
ሦስተኛ፣ ለጉዞ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቁሳቁሶች ናቸው፡፡
        ይህች መርከብ ከላይ ከተጠቀሱት መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱን አሟልታለች፡፡ ሁለቱ ዋነኛ ነገሮች ግን የላትም፡፡ ይኸውም ስለ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ እርግጠኛ አልነበረችም፡፡ በዚህ ፈታኝ ጉዞዋ ውስጥ ዋስትና የላትም፡፡ ቁሳቁስ ግን ይዛለች፡፡ ወገኖቼ እስቲ ለአንድ አፍታ ይህቺን መርከብ በዓይነ ኅሊናችሁ ተመልከቷት፡፡ የብዙዎችን ሕይወት የምትወክል ይህች መርከብ ቁሳቁስ ብቻ የተሞላውን የሰዎች ማንነት ትገልጣለች፡፡ ዓለማችን ሕይወትን በቁሳዊ ነገሮች ብቻ በሚመዝኑ፣ በሕይወታቸው አምላካዊ ፈቃድና ዋስትና በሌላቸው፣ እንዲሁም ዘመኑን በማያስተውሉ ሰዎች ተሞልታለች፡፡ ቁሳዊው ዓለም የማያረካ ውሃ፣ የማያሳርፍ ሰላም፣ የማያደርስ ምሪት አለው፡፡ መርከቧ የያዘቻቸው ሰዎች የተለያዩ እንደመሆናቸው ከነዚህም መካከል የሕይወት ዓላማና ግብ እንዲሁም ምሪት ያላቸውን ሰዎች አካታለች፡፡ በመሆኑም ከመነሻው ጉዞውን የተቃወሙ ነበሩ፡፡
“ጳውሎስ÷ እናንተ ሰዎች ሆይ÷ ይህ ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጉዳት እንዲሆን አያለው ጥፋቱ በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም ብሎ መከራቸው” /የሐዋ. 27፡10/፡፡
        እግዚአብሔር በየዘመናቱና በየስፍራው ራሱን ያለ ምስክር አይተውም፡፡ በመሆኑም በእያንዳንዱ የሕይወት መንገድ ላይ ፈቃዱንና ምሪቱን እንዲሁም የሕይወት ዋስትና እርሱ መሆኑን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ምስክሮች ባይኖሩ ሕይወት እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ትሆን ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ያረጉና የሕይወትን ዓላማ የተረዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ነቢዩ፡- “ጌታ  ሆይ፣ ምስክርነታችንን ማን አመነ?”/ሮሜ 10፡16/ እንዳለ ምስክርነታቸውን የሚቀበለው ምን ያህሉ ነው?
        ጳውሎስ ስለ ጉዞው አደገኛነት ቢነግራቸውም የሚቀበለው ግን አላገኘም፡፡ ጉዞው እጅግ ታላቅ ጉዳትና አደጋ ያለው ከመሆኑም ሌላ ይህ ጉዳት በመርከቡና በጭነቱ ሳይሆን በሕይወታቸው ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ዋጋ ከፍለን ካልተማርን በስተቀር አናምንም፡፡ እግዚአብሔር የምንጓዝበት መንገድ ክፉ መሆኑን እየነገረን እኛ ግን ይህን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት የፈቃዳችንን መንገድ እንቀጥላለን፡፡ የምንጓዝበት መንገድ በእጃችን ያለውን ቢያስጥለን ነው በማለት እንዘናጋለን፡፡ ይሁን እንጂ የጠላት ዓላማ የእጃችንን ማስጣል ሳይሆን እኛን መጣል ነው፡፡ ፍጥረታዊው ሰው ዋስትና የሚያ ደርገው ቁሳዊውን ነገር በመሆኑ ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከቡ መሪና ባለቤት ተቀባይነት አግኝተው ጉዞው ተጀመረ፡፡
        አምላካዊውን ማስጠንቀቂያ ቸል ያለችው መርከብ መሪዋንና ባለቤቷን ዋስትና አድርጋ ለጉዞ ስትነሣ የተመቻቸ የአየር ሁኔታ  በመታየቱ የተቃና ጉዞ መሰለ፡፡ “ልከኛም የደቡብ ንፋስ በነፈሰ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ፡፡ በቀርጤስም ጥግ ጥጉን አለፉ”/ሐዋ.17፡13/፡፡ እግዚአብሔር እየተናገረንን አሻፈረኝ ብለን የምንጀምረው መንገድ ከጅምሩ የተሳካ ቢመስልም ፍርሃት ግን ስለሚከበን የምንጓዘው ጥግ ጥጉን ነው፡፡ “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” /ምሳ. 16፡25/፡፡ መርከቢቱ የተሳካ በሚመስለው ሁኔታ ጉዞዋን ብትጀምርም ብዙ ሳይዘገይ አውራቂስ የተባለው አውሎ ነፋስ ተመታች፡፡ በሁሉም  ላቅ ድንጋጤ ወደቀባቸው፡፡ የታመኑበት መሪና የመርከቡ ባለቤት ዋስትና መሆን አልቻሉም፡፡ ስለዚህም መርከቡን መቆጣጠር ባለመቻላቸው እነርሱ ሳይሆኑ እርሱ ይነዳቸው ጀመር፡፡   ፈቃድ ስንጓዝ ባሕሩን በእግር እንራመደዋለን፣ ያለ ፈቃዱ ግን በመርከብም አንሻገረውም፡፡
የተቆረጠ ተስፋ
            መርከቢቱ በከፍተኛ አደጋ ላይ በመውደቋ በውስጧ ያሉት ሁሉ ተጨነቁ ለመዳንም የተለያየ ጥረት አደረጉ፡፡ ጭነቱን ሁሉ ከመርከቧ ላይ ወደ ባሕሩ ይወረውሩ ጀመር፡፡ ጳውሎስ እንደተናገራቸው ጉዳቱ ለሕይወት የመጣ በመሆኑም በጭነቱ መቃለል ሊተርፉ አልቻሉም፡፡ ምስኪኑ የሰው ልጅ ከሁሉ በላይ የሚጎዳው ለገዛ ፈቃዱ በመገዛት ነው፡፡ ዓለማችን የምትናወጠውና በልዩ ልዩ አደጋ የምትመታው ሰው ፈቃዱን ለእግዚአብሔር መሠዋት ባለመቻሉ ነው፡፡ ለደረሰበት ውድቀትም የእጁን በመተው ከአደጋው ለማምለጥ ይፍጨረጨራል፡፡ አደጋው ግን ሕይወት ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ እኛንም የእጃችንንም ያሳጣናል፡፡ በዚህ ታላቅ አደጋ ላይ የወደቀችው መርከብ ለብዙ ቀን በጨለማና በአውሎ ነፋስ በመንገላታቷ የመዳን ተስፋዋ ጨለመ። “ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ ወደፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ተቆረጠ” /ሐዋ. 27፡20/፡፡
መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት
        ከምድር የተቆረጠ ተስፋ ከሰማይ ይቀጠላል፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ከጅምር ወደ ፍጻሜ የሚጓዘው በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላካችን የደረቀውን እያለመለመ የተቆረጠውን እየቀጠለ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ስንት የፈቃድ መንገዳችን ባስቀረን ነበር፡፡ እርሱ ግን መንገዱን ሳንጀምረው በፊት ያስጠነቅቀናል፣ ይመክረናል፡፡ አሻፈረን ብለን ስንጓዝ ፈቃዳችንን ስለማይጋፋ ዝም ይለናል፡፡ በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩ ሁሉ ሞታቸውን ሲጠባበቁ የመዳን ተስፋ  ታወጀላቸው፡፡ ነቢዩ ዳዊት፡- “ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል” /መዝ. 22፡6/ ይላል፡፡
        የእግዚአብሔር ፍቅር በተፈቃሪው ማንነት ላይ ያልተመሠረተ ኃጢአተኛውን የሚያድንና ለማዳንም ተስፋ የማይቆርጥ በትዕግሥት የሚሸከም በንስሓ የሚመለሱትንም የሚቀበል ነው፡፡ ይህ ፍቅር ማረፊያ ወደባችን ነው፡፡ እንደገና የተሠራንበት በመሆኑም ይህን ታላቅ ፍቅር እናመሰግናለን፡፡ አስቀድመው የናቁት ጳውሎስ አሁን ደገሞ የመዳን ተስፋን ሰበከላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች አንዱ አገልግሎታቸው ለወደቀው ሰው የንስሓ ጥሪና የመዳን ተስፋን ማወጅ ነው፡፡ የሰው ልጅ የራሱ መንገድ ወደ ሞት ቢነዳውም እግዚአብሔር ግን በንስሓ ወደ ሕይወት መንገድ ይመራዋል፡፡ “አሁንም አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፡፡ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ አይጠፋምና” /ሐዋ.27፡22/፡፡  በደረሰብን መከራ አይዞአችሁ የሚለን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ግን ይገባዋል ዋጋው ነው ይሉን ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር መከራውን በራሳችን ፈቃድ ጎትተን ያመጣነው እንደሆነ ቢያውቅም የእርሱ ዓላማ ከመከራው ተምረን ወደ እርሱ ፈቃድና አሳብ እንድንደርስ ነው፡፡
ያለውን ያደርጋል
        መቼም በመከራ ውስጥ የሚነገር ተስፋ የሚፈፀም ስለማይመስለን እንጠራጠራለን፡፡ እርሱ ግን በዘመናት ቃሉን የሚያከብር  ታማኝ ጌታ  ነው፡፡ ኪዳኑን ይጠብቃል፣ የተናገረውን ይፈጽማል፡፡ ጳውሎስ የመዳን ተስፋን ሲነግራቸው በመርከቢቱ ውስጥ ያሉት ወገኖች እንደ ዋዛ ሰምተውት ነበር፡፡ እርሱ ግን በአምላኩ የታመነ ስለነበር እንዲህ አላቸው፡- “እናንተ ሰዎች ሆይ አይዟችሁ እንደተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና” /ሐዋ. 27፡25/፡፡
        ለፍጥረታዊው ሰው የእግዚአብሔር ነገር ሞኝነት ስለሚመስለው በመንፈስ ካልሆነ አይረዳውም፡፡ ለእምነት ሰዎች ግን ከነገሮች ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ጌታ የሚሳነው እንደሌለ ስለሚያምኑ ክብሩን  ያያሉ፡፡ እርሱ አይቸኩልም አይዘገይም በጊዜው ይደርሳል ያለውንም ያደርጋል፡፡  አሜን!!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ