የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያለ ሰዓቱ አይነጋም

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ግንቦት 22/2007 ዓ.ም.        
 
ጨርሶ አይጨልምም። ፀሐይ ስትጠልቅ፣ ጨረቃና ከዋክብት ይወጣሉ። ዘጠኝ በሮች ሲዘጉ አንዱ ይከፈታል። ዘጠኝ ወዳጆች ሲሄዱ አንዱ ይተርፋል። ፀሐይ ባትጠልቅ ጨረቃ አትታይም። ፈተና ካልመጣም የማናውቃቸው ሰዎች አሉ። ፈተናው የሚሰጠን የመጨረሻ ውጤት የቅርብ ያልነው ሩቅ፣ የሩቅ ያልነው የቅርብ መሆኑን ነው። ፀሐይ እንደምትወጣ እርግጠኞች ነን። ጨረቃና ከዋክብት ለመውጣታቸው ግን እርግጠኛ አይደለንም። ጨረቃ የማትወለድበት፣ ከዋክብት የሚሰወሩበት ጊዜ አለ። የምታስተማምነዋ ፀሐይ ስትጠልቅ ያልጠበቅናቸው ጨረቃና ከዋክብት ይወጣሉ። የማታ ብርሃኖች ዙሪያውን በደንብ ባያሳዩንም ለእግራችን መርገጫ ያሳዩናል። ሰማዩን በውበት ይገልጡልናል። የብርሃንን ዋጋ እንድናስብና እንድንሰስት ያደርጉናል። እንደ ፀሐይ እርግጠኛ የሆንባቸው ሊጠልቁ ይችላሉ። ያልጠበቅናቸው ደግሞ ብቅ ይላሉ። ጨርሶ አይጨልምምና። “ፀሐይ ስለ መጥለቋ ከተመረርህ ከዋክብትም ይሰወሩብሃል” ይባላል። ቢወጡም አታያቸውም ማለት ነው።  ምሬት ዓይንን ያጨልማልና።
 
አዎ ያለ ሰዓቱ አይነጋም። አሁን ለመተኛት ገብተን ወዲያው ቢነጋ መልካም አይደለም። ያለ ሰዓቱ ከነጋ፡-
 
1-     አእምሮአችን አይታደስም፡- አእምሮ የሚታደሰው የዋልንበትን አሳብ ፍጹም ትተን ስናርፍ ነው። በቂ ዕረፍት ስናገኝ ለቀጣዩ ቀን መማርና መሥራት እንችላለን። በሕይወት ውስጥ የሚገጥመን የፈተና ሰዓትም ራሳችንንና ዙሪያችንን እንድናይ ስለሚረዱን ያበስሉናል። እኔ ማን ነኝ? የምኖረው ከእነማን ጋር ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የምንችለው በመከራ ሰዓት ነው። የፈተና ቀኖች የጠለለ አሳብን፣ የተጣራ ወዳጅን ያስቀሩልናል። ለቀጣዩ ዘመንም በቀላሉ የማይበገር አእምሮን ያጎናጽፉናል። ያለ ሰዓቱ ካልነጋ አንበስልም። እኛ የሚያስጨንቀን መከራው ነው፣ ጌታ ግን ትምህርቱ እንዳያልፈን ያስባል። ሕጻን ልጅ ስለ መድኃኒቱ ምሬት ያለቅሳል፣ ወላጆች ግን ስለመዳኑ ይጨክናሉ። ሩኅሩኁ ጌታ እስክንማር ይጨክናል።
2-   ከድካም አንላቀቅም፡-ያለ ሰዓቱ ከነጋ አሁን የተለየነው ግርግር መልሶ ይመጣል። አሁን የተውነውን ሥራ እንቀጥላለን። ከድካም ስለማንበረታ በቀጣዩ ቀን እንደክማለን፣ እንወድቃለን፣ በሥራችንም ውጤታማ አንሆንም። የቀጣዩን ቀን ትግል ለመቋቋም በሰዓቱ መንጋት አለበት። እግዚአብሔር ከግርግሩ ለይቶ፣ ሱስ ከሆኑብን የጊዜ ገዳዮች አውጥቶ የሚያሳርፈን በጨለማ ቀኖች ነው። በሰዓቱ ሲነጋ በርትተን ለቀጣዩ ዘመን ኃይል ይዘን እንቆማለን።
በሰዓቱ ይንጋ፣ በትግሎቻችን ሁሉ ጌታ ትዕግሥት ይስጠን። የማይነጋ ሌሊት የለም። ማታ ጠዋት ይሆናል። ማታ የተለየን ጠዋት ይመጣል። ጠዋት ሲመጣ ግን በሰዓቱ ነግቷልና አእምሮአችን ታድሶ፣ አቅማችን በርትቶ እንቀበለዋለን። ጸጋ ይብዛላችሁ።
 
እኔ የክርስቶስ ባሪያ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ