መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ያላለቁ ሥራዎቻችን

የትምህርቱ ርዕስ | ያላለቁ ሥራዎቻችን

የብዙዎቻችን ሕይወት ባላለቁ ሥራዎች የተሞላ ነው። ያለብን ፍርሃት ምንጬ ያላለቁ ተግባሮቻችን ናቸው:: ጊዜአችን የሚባክነው በማያስፈልግና በማያስቸኩል ጉዳይ ላይ ነው። የቀኑ ጀምበር ሲጨልም ያልሠራነው ነገር ትዝ ይለንና መኝታውን ያበላሻል። መሐል ባሕር ላይ ያለ በማዕበል ይታወካል፣  ወደብ ላይ የደረሰ መርከብ ግን ማዕበል አያሰጋውም። ፍርሃት እንዲያስፈራን የምንፈቅድለት ሥራችንን ለመፈጸም ባለን ቸልተኝነት ነው። ሕይወት ትግል ቢኖረውም የአብዛኛው ትግል መነሻ የእኛው ችግር ነው። በትዳራችን፣ በልጆቻችን፣ በሥራችን ፣ በወዳጅነታችን የገጠሙን ችግሮች የእኛ እንዝላልነት ውጤት ናቸው። እናቶቻችን፦ “ሴት ልጅ ኮስተር ካለች አንበሳም አይደፍራትም” ይላሉ። እንኳን ወንድ አንበሳም የማይዳፈራት ከሆነ ችግሩ ምን ላይ ነው ? ማለት አለብን።

ሰንበት በአማኝነት ብቻ ሳይሆን በምህራዊ ጥናትም ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነው። በሰንበት ግን ተገቢውን ተግባር፣ የነፍስ ሕክምና አናደርግም። ልጆቻችን እንኳ በሰንበት ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ እየተደረገ ነው። አንዱ ዓላማው ከቤተ እግዚአብሔር የራቁ ብኩን ትውልድ እንዲሆኑ የታቀደ ነው ። የምድር ገዥዎች  ሬሳ ለመምራት ካቀዱ ዓመታት አልፈዋል። በሰንበት ዕረፍት የማይሰማን ያልፈጸምነው ተግባር ስላለ ነው። ዕቃ እንደ ጣለ ቅር ይለናል። መሐል መንገድ ላይ እንደ ቆመ መጋለጥ ይሰማናል። ከኑሮአችን አልፎ ሞታችን ያስፈራናል።  ቤተሰቦቻችን ለእግራችን ስጋጃ ፣ ለጎናችን ትራስ፣ ለጉልበታችን ጋቢ ፣ ለሆዳችን ጣፋጭ ምግብ፣ ለአፍንጫችን ዕጣን ቢያደርጉልንም ልባችንን ሰቅዞ የሚይዘን አንድ ነገር አለ። እርሱም ያልፈጸምነው ተግባር ነው። ወሩ ሲያልቅ እንደ ተተኵሰ ጥይት ያስደነግጠናል። ከመቸው ኅዳር መጣ፣ ከመቼው ሰኔ ደረሰ እንላለን። ያልተፈጸሙ ተግባሮቻችን በደስታ ዘመንን እንድንለውጥ እያደረጉን አይደለም።

አንዳንድ ተግባሮቻችንን ገና አልጀመርናቸውም። መኖራችንን ዋጋ የሚሰጡት ፣ ለሰማዩ  ጥያቄ መልስ የሚሆኑን ናቸው:: በትልቁ አባት ፊት አንገታችን ሰባራ፣ ፊታችን አፋር እንዳይሆን እነዚህን ተግባራት መፈጸም አለብን። ከዛሬ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ በማሰብ ሥራችንን አልጀመርንም። ከዛሬ የተሻለ የእኛ ቀን የለም። ትልልቅ ተግባራትን ለመፈጸም እንፈልጋለን። ሁለት ነገሮችን አልተረዳንም፦ የመጀመሪያው ትልልቅ ተግባራት በሕይወት ዘመናችን የሚመጡት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ነው። እያንዳንዱ ቀን በትንንሽ ተግባራት የተሞላ ነው። ሁለተኛው  ትንንሹን ተግባር ስንፈጽም ትልቅ እንደሚሆን እንዘነጋለን። አንዳንድ ተግባሮቻችን እኛ ከሌለን ላይፈጸሙ ይችላሉ። የእኛ መኖርና የሰዎቹ መኖር ወሳኝ ነው። ጀምበሬ ሳይጠልቅ መልካም መሥራት፣ ጀምበራቸው ሳይጠልቅ መልካም ማድረግ ይገባናል። ሕይወት በጉዞ ላይ ናት፣ ቆሞ  የሚጠብቅ ዕድል በዓለም ላይ የለም። ለሰው ልጅ ትልቅ ሀብቱ ጊዜ ነው። ጊዜ ያለውን ድሀ  ያለው ማነው? መቼ እንደምንጠራ አናውቅምና አራት  ነገሮችን ማከናወን አለብን፦

1- ሥራችንን መሥራት፣
2- ንስሐ መግባት ፣
3. ይቅር መባባል፣
4. ልጆቻችንና ቤተሰቦቻችን እንዳይባሉ ኑዛዜ ማስቀመጥ አለብን።

ጀምረን ያልፈጸምናቸው ተግባራት አሉ። ችኩል ሰው የመጀመር ጀግና ነው። ለመፈጸም አንደኛ ስልቹነት፣ ሁለተኛ በጅምር መርካት፣ ሦስተኛ ፍርሃት፣ አራተኛ የሰዎች ትችት ይታገለዋል። ጀምሮ አለመፈጸም ያለ መጀመር ያህል ነው። የሰው ልጅ እልህና ቅንዓት ወይም ውስጣዊ ሙቀት ያስፈልገዋል።

ጀምረን ለመፈጸም ጥቂት የቀሩን ግን እያታገሉን ያሉ ተግባራት አሉ። “አይጥ ወልዳ ወልዳ ጅራቷ ሲቀራት ታንቃ ሞተች” ይባላል። የቀረው ትንሽ ቢሆኑም ውጊያው እልህ አስጨራሸ ይሆናል። በርቱ ወገኖች ሲያልቅ ደስ ይላችኋል። በዓለም ታሪክ እንዳየነው የጦርነት መጨረሻ ጦርነት ሆኖ አያውቅም።

ጠዋት ወደ ሥራ ለመሰማራት፣ ከትምህርት ገበታ ለመገኘት ደወሉ ይደወላል:: ምንም ሳንሠራ የመጨረሻው ደወል እንዳይደወል መፍራት አለብን። ቀኑ ሳይጨልም በፊት ሥራችንን ለመፈጸም ይህንን ምክር ማክበር ይገባል።

ሥራን ለመሥራት የእኛ መኖር፣ የምንደርስላቸው ሰዎች መኖር ፣ ዕድል ያስፈልጋሉ። ሦስቱ በአንድነት ካልተገናኙ ሥራ አይሠራም።

ያልሠራነው ምንድነው?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ