ባል የሞተ እንደሆነ ጣጣው ፣ እንግዳ ክስተቱ ፣ የቤተሰብ መራኮቱ ብዙ ነው ። “አባዬ ፣ አባዬ” የሚል ልጅ ከገባ ልቅሶው አንድ ጊዜ ገታ ይደረግና “ማን ይሆን ?” ይባላል ። በየልቅሶው ቤት በነጠላው ሥር ያለውን ሐሜት እግዚአብሔር ይቍጠረው ። ባል የሞተ እንደሁ ቅርበቱ ለእኔ ነው የሚል አልቃሽ በየአቅጣጫው ይሰማል ። እናትም ለብቻ ፣ እኅቶችም ለብቻ ፣ ሚስትም ለብቻ ቅኔ ያወርዳሉ ። በልቅሶው ፉክክር የሞተው በእግዜር በሽታ አይደለም የሚል ድምፀት እየተሰማ ሚስቱን ይኰንናሉ ። ባለፈው ዘመን የሚከሷት ቢያጡ ለቀጣዩ ይጠረጥሩአታል ። ታዲያ አንድ ሰው ሞተ ። ሚስቱ ወጣት ናት ። ቤተሰቦቹም ከመሞቱ በላይ ወደፊት ያቺ ሴት እንደምታገባ ሲያስቡ ልቅሶአቸው የንዴት ሆነ ። በዚህ ጊዜ ከሟች እኅት አንዲቱ እንዲህ ብላ የኀዘን ሙሾ አወረደች፡-
ይብላኝ ለእናት ለአባት ፣ ይብላኝ ለወንድሞቹ ፣
ይብላኝ ለቤተሰብ ይብላኝ ለእኅቶቹ ፣
ሚስትስ ታገባለች ከባልደረቦቹ ።
በዚህ ጊዜ ያቺ ባልዋ የሞተባት ኀዘንዋ ያልተሰማላት ሚስት እንዲህ ብላ መለሰች፡-
እቴ ምን ያለሽ ነሽ ተናግሮ አናጋሪ ፣
ባልሽ ይሙትና እንደ እኔ ተዳሪ ፤
የአገራችን ሰው በአብዛኛው የሚሞተው በማያገባው እየገባ ነው ። ማንም ሰው እርዳታ ካልጠየቀን በቀር ላማክርህ ፣ ልወቅህ ፣ ልወቅልህ ማለት አይገባንም ። ሁሉም ሰው የራሱ ገመና አለው ። ወዶ ፈቅዶ አንተ ልታውቀኝ ይገባሃል ብሎ ካልመረጠንና ካልነገረን በቀር የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን አይገባም ። የቅርባችን ሰው የወደደውን መውደድ ፣ ይሆነኛል ያለውን ትዳር ለእርሱ መተው ይገባል ። ሟችን በሞቱ ሰዓት ፍቅርን ቢገልጡለት ፣ ዋይ ቢሉለት ፣ ቢጣሉለት አንዳች ጥቅም የለውም ። የቁም ዘመድ መሆን ሲገባ የመቃብር ባንድ ሆኖ ሲዘሉ መዋል ግብዝነታችንን ከመግለጥ ውጭ አንዳች ትርፍ የለውም ። በሰው ላይ ያለን ድርሻ እስከምን ድረስ ነው ( ማለት ያስፈልጋል ። ልጃችን የወደደውን መውደድ እንጂ እርሱ ከሞተ በኋላ የፈረሰውን ቤት የበለጠ ማፍረስ ከሞት በላይ ጨካኝ መሆን ነው ።
ወገንነት ጠብ ፈጥሮ መጣላት ፣ ለምንወደው ሰው መሰዳደብ አይደለም ። አንድ ሰው ብዙ ነው ። ለወላጅ ልጅ ፣ ለእኅት ወንድም ፣ ለሚስት ባል ፣ ለልጆቹ አባት ፣ ለቤተ ክርስቲያን ምእመን ፣ ለአገር ወታደር … ነው ። አንድ ሰው የግላችን ሊሆን አይችልም ። ሰው ከዓለም ይሰፋል ፣ ዓለም የብዙዎች ናት ። በእኛ በኩል መጣ እንጂ ያ ሰው የብዙኃን ነው ። ልጅን ወልደው ለአገር ይሰጡታል ፣ ለዓለም ያበረክቱታል እንጂ የግል ብቻ አያደርጉትም ። የምንወደው ሰው የሞተ ቀን ሚስቱን አለንልሽ ማለት ፣ ልጆቹን ምንም ሳይጎድልባቸው ማሳደግ የአፍቃሪ ወጉ ነው ። ሞት ኀዘን ብቻ ሳይሆን ትምህርትም ነው ። የቀረነው ለመታዘብና ለመሳደብ ሳይሆን ያ ሰው የጀመረውን ራእይ ለመፈጸም ነው ። የሌላውን ስንፈጽም ያዩ ልጆቻችን የእኛንም ይፈጽሙልናል ። ልጆች ያደረግንላቸውን ሳይሆን ለወላጆቻችን ያደረግነውን እርሱኑ ይመልሱልናል ።
ሰዎች እንደ ገመትናቸው አይደሉም ። እንኳን የሰዎችን የእኛንም ነገ አናውቀውም ። የነቢያት ትልቅ አገልግሎት ነገን ማየት ሲሆን እርሱም ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ይመጣል የሚል ነው ። የነገ ትንበያችን መልካም መሆን አለበት ። እኛ ልናደርገው የሚሰቀንን ሰዎች ያደርጉታል ብለን ማሰብ አይገባንም ። በሌሎች ላይ የፈረድነውን እኛ አብዝተን ልናደርገው እንችላለን ። በሰው ልጅ የፈረድነው በልጃችን ፣ በሰው ትዳር የፈረድነው በትዳራችን ፣ በሰው ሞት የፈረድነው በሞታችን ብቅ ይላል ። የፈረድነውን ብንረሳውም ፍርዱ ግን አይረሳንም ።
የብዙ ሰው ልቅሶ ውስጡ እሾህ ያለበት ነው ። ለማጽናናት ማልቀስ እንጂ ለማስለቀስ ማልቀስ ተገቢ አይደለም ። አንድ ሰው ሞቶ የምናለቅሰው ለእኛም ጎድሎብናል ፣ የተጎዳችሁት እናንተ ብቻ አይደላችሁም ፣ እርሱ ቢሞትም እኛ አለንላችሁ የሚል ኪዳንም ነው ። ያዘኑ እየመሰሉ ፣ ከንፈር እየመጠጡ በቍስል ላይ ጥዝጣዜ የሚጨምሩ ያልታደሉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በኀዘን ድምፀት ሰባራ ሊያደርጉን የተላኩ የሰይጣን መልእክተኞች ናቸው ። ሰይጣንን እግዚአብሔር ይገሥጽህ ይሉታል እንጂ ጨርሰው አይሰሙትም ። ጠላት ይቀባል ጥላት/ጥላሸት እንዲሉ ከጠላት መልካም ነገር አይጠበቅም ። ወደ ሰው ኑሮ ዘው ብለን መግባታችን ፣ ሲጮኽ መድረሳችን መልካም ነበር ። ያየነውን ግን ማሳየት አናሳነታችን ነው ። ደግሞም ሁላችንም በየቤታችን የደበቅነው የራሳችን ጉድ አለን ። በጉድ የደረጀ የሰው ልጅ “ጉድ ፣ ጉድ” ቢል እግዚአብሔር ይታዘበዋል ። የአንዱ አውልቆ ማበዱ ካልሆነ ሁሉም ሰው እንደ ለበሰ አብዷል ። አንዱ መናገሩ ካልሆነ ሁሉም ሰው በቤቱ ቍስል አለው ። የሰው ነገር ሰውን ከገረመው ሰው አይደለም ማለት ነው ።
እስቲ እንረዳዳ ፣ ከመወጋጋት እስቲ እንደጋገፍ ። ምናልባት ይህች ቀን የመጨረሻ ቀናችን ልትሆን ትችላለች ። ጌታ ወዳጆቹን እራት አብልቶ ፣ ሥጋና ደሙን ሰጥቶ ተሰናበተ ። እኛም ራሳችንን በመስጠት ፍቅርን እንግለጥ ። ጌታ ሆይ አግዘን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም.