የሰው ልጅ በኑሮው ውስጥ ሦስት ተመልካቾች አሉት ። የመጀመሪያ እግዚአብሔር ፣ ሁለተኛ የገዛ ሕሊናው ፣ ሦስተኛ ሰዎች ናቸው ። ይሉኝታ ሰዎች ምን ይሉኝ ( የሚል ፍርሃት ፣ ራስ ጠይቆ ራስ የግምት መልስ መስጠት ፣ ሰዎችን ከልክ በላይ ማክበር ፣ የሚመሩበት መርሕ አለመኖር ፣ ኗሪ ሳይሆን አኗኗሪ መሆን ነው ። ለእግዚአብሔርና ለሕሊናቸው የማይጨነቁ ወገኖች ፣ ለሰዎች ያውም ለሐሜታቸው ይጨነቃሉ ። በደለ ይለኛል ብለው ሲፈሩ እነዚያ ሰዎች በሐሜታቸው እየበደሉ መሆናቸውን ይረሳሉ ። አንዳንዴ ኀጥእና ኀጥእ ሲገፋፉ ይሉኝታ ይፈጠራል ። “ቀጥ ቀጥ ያለ ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ” እንዲሉ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ሲታጣ ይሉኝታ ያለውም ሰው ያምረናል ። ይሉኝታ ውስጣዊ ስሜት ሲሆን ሰውን በማይታይ ገመድ ይዞ የሚኖር ነው ። ለይሉኝታ ብለው ክፋትን የማያደርጉ ሰዎች ልባቸውም ንጹሕ ነው ማለት አይደለም ። አገር ለቀው ፣ በማያውቁአቸው ሕዝብ መካከል ኃጢአት ሠርተው የሚመጡ ሰዎች እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰዎችን የሚፈሩ ናቸው ። ይሉኝታ እንድንሰደድ ፣ ብዙ ገንዘብ እንድናወጣ የሚያደርግ ይልቁንም የእኛን ሰው ያደከመ ትልቅ ሸክም ነው ። እውነተኛ ቅድስና በሕሊና ስምምነት ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔር የሚፈጸም ነው ። በኦሪት ሁለት መርሖችን እናገኛለን ። የመጀመሪያው የሊቀ ካህኑ አዋጅ ነው ። በሊቀ ካህኑ ግንባር ላይ ሁሉም ሰው የሚያነበው ጽሑፍ ይታያል ። “ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ፡- ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ” ይላል (ዘጸ. 28 ፡ 36)። ቅድስና ለእግዚአብሔር ነው ። ቅድስና የሰዎችን ከበሬታና ማስተዛዘኛ ማግኛ ወይም መነገጃ አይደለም ። ቅድስና ለእግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔርን እያዩ መራመድ ፣ የእግዚአብሔርን ዋጋ ከፋይነት ብቻ ማሰብ ፣ ለሕሊና የሚስማማ ግብር ነው ብሎ መቀበል እርሱ ቅድስና ይባላል ። እገሌ ተሐራሚ ነው ፣ ጸሎተኛ ነው ፣ በጥሬ ነው የሚጾመው ለመባል ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ የሚያየውን ሕይወት መኖር እርሱ እውነተኛ ቅድስና ነው ። ይሉኝታ ቅዱስ እንዲሉን ተውኔታዊ ጨዋነት ማሳየት ነው ። ክፉ መሆንን ሳይጠሉ ፣ ክፉ መባልን መጥላት እርሱ ይሉኝታ ይባላል ።
ሁለተኛው የኦሪት ምክር፡- “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” የሚል ነው ። (ምሳ. 29 ፡ 25) ። የድብብቆሽ ሕይወት የሚኖር ሰው የይሉኝታ እስረኛ ነው ። እንደውም ድብብቆሹ የበለጠ እንዲበድል ፣ ኃጢአት እንዲጥመው ፣ አላገኘውም ብሎ እንዲጨማለቅበት ፣ የዕለት ሥራው እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል ። ወጥመድ አያራምድም ፣ ሰውን መፍራትም ነጻነት ያሳጣል ፣ ከኃጢአት ግን አይጠብቅም ። በእግዚአብሔር መታመን ግን ነፍስን ከግድፈት ፣ ሰውነት ከዝገት ይጋርዳል ። ቅድስና ለእግዚአብሔር ነው የሚለው አዋጅ ፣ ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው የሚለው ምክር ከይሉኝታ ሰንሰለት የሚፈታ ነው ። ሰዎች በሁለት ነገር ከክፉ ሊርቁ ይችላሉ ። እግዚአብሔርን በመፍራትና ሰዎችን በማፈር ። ወይም የሰማይን ዋጋ በማሰብና ታሪኬ እንዳይበላሽ በማለት ክፉውን ለመራቅ ይሞክራሉ ። ይሉኝታ በይሻላል መስፈርት ያለ ፣ ዓይን ካፈጠጠ ስህተት የሚጋርድ ፣ ትንሽ ሰውነት ያለበት ፣ ልክ አይደለሁም የሚል ወቀሳም ያልተለየው ሊሆን ይችላል ። እግዚአብሔር ግን የልብ አምላክ ነውና በልብ መቀደስን ይፈልጋል ።
በዚህ ዓለም ላይ ሁሉም ሰው የራሱ ችግር እንዳለው ሁሉ የራሱ ግድፈትም አለው ። ንጹሕ ነኝ ብሎ የመጀመሪያውን ድንጋይ ማንሣት የሚችል ብቁ ማንም የለም ። የመውገር ፍላጎት አብዛኛው ሰው አለው ፣ ኃጢአት የሌለበት እርሱ ይውገር ቢባል ግን ሁሉም ውልቅ ብሎ የሚወጣ ፣ ጸንቶ መቆም የማይችል ነው ። ይሉኝታ ሰዎች ስለ እኔ ይህን ሊያስቡ ፣ ይህን ሊናገሩ ይችላሉ የሚል ያልተጨበጠ ፍርሃት ነው ። ከይሉኝታ የሚፈታን አንዳንድ ጊዜ ሰዎቹ ከማሰብ ወጥተው መሳደብ ሲጀምሩ ነጻነት እናገኛለን ። ሰዎች ስህተታቸው እስኪነገር ድረስ እያበረዱ የሚጓዙ ናቸው ፣ ስህተታቸው አደባባይ ከወጣ በኋላ ግን ፍሬን እንደ ተበጠሰበት መኪና ሕግን አያከብሩም ። የሰዎች ምሥጢር ጠባቂ የምንሆነው ጨርሰው የኃጢአት ሎሌ እንዳይሆኑ ነው ።
ይሉኝታ እውነተኛነት የሌለው ኑሮ ነው ። ማድረግ እየፈለግን የማናደርገው ማኅበረሰቡን በመንገዳችን እንደ ቆመ ትራፊክ ስለምንፈራ ነው ። ትክክለኛውን ነገር ከማኅበረሰቡ ባሕል ጋር አስታርቆ ማድረግ የምንኖርበት ዓላማ ነው ። ይሉኝታ ማድረግ የማንፈልገውንም ማድረግ ነው ። መጠጣት የማይፈልገው ሰው ይጠጣል ፣ በውስጡ ኀዘን ሳይሰማው ልቅሶ ቤት ሄዶ ያለቅሳል ፣ ደስ ሳይለው በሰው ሰርግ ላይ ይዘላል ። የአንድ ሰው ኑሮና ሕይወት በማኅበረሰብ ደረጃ በሚወሰንበት አገር ላይ ሰው የሚፈልገውን ትቶ የማይፈልገውን ለማድረግ ይዳረጋል ። ፍጹም ይሉኝታ ቢስ የሆነው የሰለጠነው አገርና የይሉኝታ ወጥመድ ያለበት ሌላኛው ምድር መታረቅ አለባቸው ። ይሉኝታ ራስን መክሰር ሊያመጣ ይችላል ። በሰዎች ምርጫ መኖርን ፣ ሁልጊዜ የሌሎችን ውሳኔ መቀበልን ፣ እየተረገጡ አላመመኝም ማለትን ፣ መብትን አሳልፎ መስጠትን ፣ ያላመኑበትን ነገር አዎ አዎ ማለትን ፣ ሳይረዱ ገብቶኛል ማለትን ያመጣል ። ይሉኝታ ከሕሊና ነጻነት ፣ ከእውቀት ፣ ከፍልስፍና ፣ ከሃይማኖት ፣ ከመንፈሳዊነት ያግዳል ።
የሕፃን ልጅን ቆሻሻ ስንጠርግ “የእገሌ ልጅ ንፍጣም ነው” ይሉሃል ብለን እንጂ ንፍጥ አስቀያሚ ነው ብለን አይደለም ። ስለዚህ ያ ልጅ ሲያድግ የሚጸዳው ለራሱ ሳይሆን ለሰው ብሎ ነው ። ምንም ነገር ለማድረግ ስንነሣ “ሰው ምን ይልሃል (” የሚል ድምፅ ከጎናችን ካሉ ሰዎች ይሰማል ። ሰው እኮ የሚኖረው ለማለት ነው ። ሰው የፈለገውን ማለት ይችላል ፣ ሕይወቱ ግን የእኔው ነው ብሎ ጥሶ የሚወጣው እንደ እብድ ይታያል ። ይሉኝታ ያረገዘችው ተደብቃ እንድትሰነብት ፣ የበላው ሰውዬ እንዳልበላ እንዲያስመስል ፣ የማያውቀውን አውቃለሁ እንዲል ያደርጋል ። በማያሳፍረው ማፈር ከይሉኝታ ይወለዳል ። መንገድ ጠፍቶን የእኛን ሰው ብንጠይቅ አላውቅም የሚል የለም ፣ ሁሉም ሰው በዚህ በኩል ነው እያለ ስድስት አቅጣጫ ይነግረናል ። አታውቅም ይሉኛል የሚል ፍርሃት አለበት ። ለዚህ ነው ያልተማረው ሰው የተማረውን የሚያርመው ። አንድ አሳብ ሲሰጥ ሁሉም ሰው አስተያየት መስጠት ግዴታው ይመስለዋል ። ለሁሉም ነገር አስተያየት አይሰጥም ። ብዙ አስተያየቶቻችን እንከን ፈላጊነት አለባቸው ። ይህ ሁሉ ይሉኝታ ድሩን ስላደራብን ያተረፍነው ጠባይ ነው ። ሊቃውንት ዝምታን ፣ ያልተማሩ መለፍለፍን የመረጡት በይሉኝታ ሥርወ መንግሥት ውስጥ ስላለን ነው ። ስንቱ ሊቅ ፣ ስንት ስህተት እያየ የቡና መጠጫ ፣ የጠላ ዋንጫ ከሚያደርጉኝ ብሎ ዝም ብሏል ። ይሉኝታ ሊቅ ገዳይ ነው ።
ስሜታችንንም ሆዳችንንም እየሸሸግን የምንኖር ነን ። ሆድ አይሸሸግም ፣ እኛ ግን እየራበን በልቼ ነው እንላለን ። ስሜትም ከተሸሸገ ውስጣዊ እሳተ ጎሞራ የሚፈጥር ፣ ራስን ጠርጎ የሚወስድ ነው ። የይሉኝታ ባሕላችን ግን ሆዳችንም ሕሊናችንም በረሀብ ጠኔ እንዲኖር ያደርገዋል ። መጠየቅ መማር ባለመፈለጋችንም አላዋቂነት እንዲሰፍን አድርጎናል ። ትልቁ እስረኛ በይሉኝታ አጭር ዘመኑን ያመረረ ሰው ነው ። አዎ “እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ።
ይቀጥላል