የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ይስሐቅም

“ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ” ማቴ. 1፡2 ።
አይሁዳውያን አያት የሌለውን ልጅ እንደ ልጅ አይቆጥሩትም ። ሰባት ቤቱን ዘርዝሮ የማያወራ አይሁዳዊ አይደለም ብለው ያስባሉ ። በዘር ቆጠራ ለሚያምኑት አይሁዳውያን የክርስቶስን ምድራዊ የዘር ሐረግ ይቆጥራል ። በራሱ መንገድ ሳይሆን በእነርሱ መንገድ ሂዶ ወደ ክርስቶስ ሊያደርሳቸው ይፈልጋል ። ከማይጠፋ ዘር ተወልደናል በማለት ይህንን መሻር አልፈለገም። የዘር ሐረግን መቊጠሩ ትልቅ የስብከት ዘዴ ነው ። ስብከት ማለት እንደገባን መናገር ሳይሆን ሰዎቹ እንደሚገባቸው መናገር ነውና ። ለአይሁዳውያንም ያለውን አድናቆት የሚገልጥ ይመስላል ። ምክንያቱም የዘር ሐረግን መቊጠር መቻል በራሱ እውቀት ነውና ። በቤት ውስጥ ያደገ ልጅ ይህን ሲያጠና ያድጋል ። አንድ አይሁዳዊ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ሥሩ ያለው ከአብርሃም ጋር መሆኑን ያስባል ። ሥሩ ስላልተበጠሰ አልወድቅም ብሎ ያስባል ። ለመዳን ባይጠቅም እንኳ ልናደንቅ የሚገባን ብዙ ነገር አለ ። መንፈሳዊ ሰው በሁሉ ይማራል እንጂ እንደ ሞኝ ሁሉንም አይንቅም ። “ሞኝ ከሁሉ ይጣላል” እንዲሉ ። ጌታችን እንስሳትን እየጠቀሰ ሲያስተምር ከእነርሱም ለመማር ዝቅ በሉ እያለን ነው ። ስለ እምነት ኑሮ ወፎችን ፣ እንዲሁም አበቦችን ተመልከቱ ይለናል ። ከጠላት መማር እንደሚገባን ሲገልጥ “እንደ እባብ ብልህ ሁኑ” አለ ። ለሚማር ሰው እያንዳንዱ ቀንና አጋጣሚ በትምህርት የተሞላ ነው ። “የተማረ ቄስ ሁሉን ይቀደስ ፣ ያልተማረ ቄስ ሁሉን ያረክስ” እንዲሉ ። ሐዋርያውም “ለንጹሖች ሁሉ ንጹሕ ነው” እንዳለ ። ሰዎች “የለበስከው ጥሩ ነው” ሲሉ መልሱ “በጥሩ ዓይንህ ስላየኸው ነው” ይባላል ።
የዘር ሐረግን መቊጠር የትመጥን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ መካከል ጋብቻ እንዳይፈጸም ይረዳል ። በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም ጋብቻ ዝምድናን ያፈርሳል ። በዝምድና ላይ ዝምድና አይፈቀድም ። ሁለተኛው የቅርብ ቤተሰብ ጋብቻ ሲፈጽም የሚወለዱት ልጆች ጤነኛ አይሆኑም ። እግዚአብሔር የትውልድ ጤና ጠባቂ ነው ።
የዘር ሐረግ ቆጠራው ሉቃስ እስከ አዳም ሲቆጥር ማቴዎስ ግን ከአብርሃም ይጀምራል ። ማቴዎስ ለአይሁዳውያን በመጻፉ የአይሁዳውያን አባት ከሆነው ከአብርሃም ይጀምራል ፤ ሉቃስ ግን ለዓለም በመጻፉ ዓለሙን ከሚያገናኘው ከአዳም ጋር በማገናኘት ይቆጥራል ። ወንጌላውያን ለማን እንደሚጽፉ ያወቁ ነበሩ ። ለማን እንደሚናገር የሚያውቅ የሚናገረውን ያውቃል ።
“ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ” ይላል ። ይስሐቅ ያዕቆብን የወለደው ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው ። ዘፍ. 25፡ 26 ። በ60 ዓመቱ ነው የወለደው ። ለሃያ ዓመታት ያህል ልጅ አልነበራቸውም ። በዚህም የቤቱ ፍቅር አልተናጋም ። መሠረቱ እግዚአብሔር የሆነለት ትዳር ምንም አያናጋውም ። ይስሐቅ ባለመውለዷ ምክንያት ከርብቃ ጋር አልተሟገተም ። ሴት ልጅ አምራች አይደለችም ። እግዚአብሔር ሲሰጣት ብቻ የምትቀበል ናት ። ይስሐቅ ስለ ሚስቱ በመጸለይ እግዚአብሔር ልጅ ሰጠው ። ቆይቶ የወለደው መንታ ልጆችን ነው ። እግዚአብሔር ለሚታገሡት እጥፍ በረከት ይሰጣል ። እግዚአብሔርን መጠበቅ አያጸጽትም ። በሌሎች ላይ የምናየው ጉድለት የጸሎት ርእስ ነው ።
“ይስሐቅም” የሚለው ቃል ይደንቃል ። የመጨረሻዋ ፊደል “ም” ትደንቃለች ። ይስሐቅ ከመቶ ዓመት በኋላ የተወለደ ልጅ ነው ። ያ የማታ ጀንበር የሆነው ይስሐቅ ራሱ ዘግይቶ የተወለደ እርሱም ወለደ ። ምናልባት ይህን ጽሑፍ የምታነቡ ገና በጽንስ ሳላችሁ ይወገዱ የተባላችሁ ትሆናላችሁ ። በልጅነታችሁ በታላቅ መከራ ውስጥ ያለፋችሁና ሞትን ብዙ ጊዜ አይታችሁ ሊሆን ይችላል ። ብዙ ራብና ጥማትን ያፈራረቃችሁ ትሆኑ ይሆናል ። እናንተም ወጉ ደርሷችሁ ይኸው ወለዳችሁ ፣ እናንተም ወጉ ደርሷችሁ ይኸው ታላቅ ቦታ ደረሳችሁ ፣ እናንተም ወጉ ደርሷችሁ ሰውን ለመርዳት በቃችሁ ።ወግ ላሳያችሁ ጌታ ምስጋና አቅርቡለት ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ