የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደህና ነው /4

ባልና ሚስት ለአንድ አካል የሚሠሩ ሁለት እግሮች ናቸው  ። አንደኛው ሲራመድ አንደኛው የሚጠልፍበት ፣ አንደኛው ሲጽናና ሌላው የሚረበሽበት ፣ አንዱ ሲያድግ ሁለተኛው የሚቀናበት ኅብረት አይደለም ። ባልና ሚስት ለእግዚአብሔር ሥራ አንድ ሲሆኑ ኑሮአቸው መባረክ ይጀምራል ። የሱነም ሴት ባሏ እንዳልሽ የሚላት ፣ ተማምኖባት ቤቱን የለቀቀላት ብትሆንም እርስዋ ግን ባሏን ታማክረው ነበር ። ወስና ሳይሆን አስቀድማ አሳብ ትጠይቀው ነበር ። ትዳርን ረጅም ጉዞ የሚያስኬደው የጋራ ምክክር ሲኖር ነው ። እንዳልሽ ቢልም ማማከር መልካም ነው ። ሕዝባቸውን የማያማክሩ መሪዎች መልካም ሠርተውም ይነቀፋሉ ። መሪ ማለት የአገር ባል ነው ። ልዩነቱ ትዳሩን ሲፈታ “መፋታትን እጠላለሁ” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል የማይመለከተው ባል መሆኑ ነው ። ባልና ሚስት በትዳራቸው ወደ ብቃት ሲደርሱ አንዱ ያሰበውን ሌላኛው ያስበዋል ። እንደ መንቶች ስሜታቸው እየተቀራረበ ይመጣል ። የመንቶች በተፈጥሮ ሲሆን የባልና የሚስት ግን በመሞራረድ ፣ ቢያንስ ከሃያ ዓመት በኋላ ነው ። የሱነም ሴት ለኤልሳዕ ቤት ብቻ ሳይሆን የቤቱንም ዕቃ አሟላችለት ።

“ትንሽ ቤት እንሥራለት” አለች ። ይህ የሚያሳየው ትልቅ ስጦታዋንም ትንሽ አድርጋ የምታይ ትልቅ ሴት መሆኗን ነው ። ትልቅ ሰው የሚቀበለውን ትንሽ ትልቅ አድርጎ የሚመለከት ሲሆን እርሱ ለሌላው የሚሰጠውን ትልቅ ደግሞ ትንሽ አድርጎ ይመለከታል ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንድ አበባ የሰጣቸውን ሰው ብድግ ብለው እጅ ነሥተው ይቀበሉ ነበር ። የሱነም ሴት ትንሽ ቤት እንሥራለት አለች ። የቤት ትንሽ እንደሌለው የሠራ ሰው ያውቀዋል ። ቤት ማለት ጣራና ግድግዳ ብቻ አይደለም ። በሚታየው ነገር ውስጥ ብዙ የማይታይ ፣ በሚታወቅ ነገር ውስጥ ብዙ ምሥጢር ያለበት ነው ። የሱነም ሴት ለኤልሳዕ የሚያስፈልጉትን የቤት ዕቃዎች እንዲታዘዝ ባልዋን አሳመነች ። አልጋ ለማረፊያ ያስፈልገዋል አለች ። በዚህ ዓለም ላይ ሰው በትክክል የሚጠቀመው ንብረቱ አልጋው ነው ። ወንበሩን ሳይቀመጥበት ሊከርም ይችላል ። አልጋውን ግን ሳይተኛበት አይቀርም ። ጠረጴዛና ወንበር ይገዛለት አለች ። ለመመገቢያ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ሲያነብ ፣ ሲጽፍ እንዲመቸው ነው ። ይህች ሴት ለሥጋው ብቻ ሳይሆን ለአእምሮውም ታስብ ነበር ። ስጦታ ሥጋን ፣ አእምሮንና መንፈስን ታሳቢ ማድረግ አለበት ። ለሥጋ እንጀራ ፣ ለአእምሮ እውቀት ፣ ለመንፈስ ቃለ እግዚአብሔር ሲኖረው ስጦታ ያማረ ነው ። ለሥጋው ስንሰጠው በርታ ብለን አእምሮውን ማጎልመስ አለብን ። ወይም በስጦታው ልክ ሥራ ፈጥረንለት መስጠት ፣ ለምኜ ሳይሆን ሠርቼ አገኘሁ እንዲል እናደርገዋለን ። የሰጠህ እግዚአብሔር ነው ማለትም መንፈሱን ያረካል ። የሱነም ሴት መቅረዝም እናኑርለት አለች ። እንዳይጨልመው ፣ ሌሊት ለጸሎትና ለንባብ ሲነሣ እንዳይቸገር ነው ። ለቀን እንጀራውን ፣ ለሌሊት መብራቱን አሰበችለት ። እውቀት ያለው እናትነት ነበራት ። ስለዚህም ትልቅ ሴት ተባለች ።

የኤልሳዕ የቤቱ ምርቃት ደረሰ ። ኤልያስን የተከተለው ቤት ጥሎ ነበር ፣ ዛሬ የኤልያስ አምላክ ቤት ሠራለት ። እርሱ የአምላኩን ቤት ሲሠራ አምላኩ የእርሱን ቤት ሠራለት ። የቤቱ ምርቃት ቀን ታላቅ ደስታ የነበረበት ፣ ኤልሳዕም አምላኩን ስለዚህች ሴት ያመሰገነበት ዕለት ነው ። አገልጋዮች የሚያመሰግኑብን ወይ የሚያለቅሱብን እንሆን ይሆን  ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። አገልጋዮች ያዘኑበት ምእመን መንገዱ እሾህና ጋሬጣ ያለበት ነው ። ሙሴ የሚመራው ሕዝብ አሰናክሎት ከበረሃ የቀረ አገልጋይ ነው ። ኢያሱ ግን ሸክሙን ተቀበለው ። የሱነም ሰዎችም ችላ ያሉትን ነቢይ ፣ ለገዛ ጉዳዩ እንደሚጮህ ሰው የተቆጠረውን ኤልሳዕን ይህች ሴት አሰበችለት ። የእግዚአብሔርን ሥራና የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ብዙ ጊዜ የሚያስቡት ሴቶች ናቸው ። የእግዚአብሔር ደጃፍ ክፍት መሆን ለእነርሱ ልዩ ትርጉም አለው ። ማልቀሻቸውም መጽናኛቸውም የእግዚአብሔር ቤት ነው ። ወንዶች እስከ ዘጠና ዓመት መሞሸር የሚፈልጉ ፣ ምድራዊ ደስታን የማይጠግቡ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይታያል ። የቤቱ ምርቃት ቀን የሱነም ሰዎች ተገኝተው ከሆነ የሚሉት ነገር ይገርመናል፡-

ድሮም አንቺ ጸጋሽ ይህ ነው ።
ችግረኛ ዘመዷን ብታደርግለት አይሻም ነበር ?
ምነው ብትነግሪን እኛም እንተባበር ነበር ።
ለመንፈሳዊ ሰው እንዲህ ያለ ቅንጦት ማድረግ ያሰናክለዋል ።
ኤልሳዕ ብዙ ሹማምንትን ያውቃል መች ይቸግረዋል ።

አንዱ ለሰጠ ብዙ ዓይነት ስሜቶች ይንጸባረቃሉ ። መልካም ሥራ ፍሬ መሆኑን ረስተው ጸጋ የሚያደርጉት አሉ ። መልካም መሥራት የእነ እገሌ እንጂ የእኛ አይደለም ብለው የድንጋይ ብርድ ልብስ ለብሰው የተኙ አያሌ ናቸው ። ለራስ ቤተሰብ እንጂ ለሌላው መልካም ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የማያስቡ ሞልተዋል ። አራዊትም ለልጆቻቸው ደግ መሆናቸውን እነዚህ ሰዎች አያውቁም ይሆናል ። ደግነት የእኔ ለማይሉት ሰው ሲደረግ ደግነት ይባላል ። ሥራው ሲሠራ የጠፉ ሰዎች ካለቀ በኋላ “ምነው ሳትነግሩን” ይላሉ ። መንፈሰ ጕንድሽ ወይም ስስታም ኪሱ ውስጥ አሥር ጊዜ እየገባ ይግደረደራል ፣ አንድ ጊዜ ግን አይሰጥም ። መንፈሳዊ ሰው ሲራብና ሲጎሳቆል ማየት የሚያስደስታቸው የድህነት ዘበኞች አሉ ። ላለመስጠት ብለው እንኳን የአገልጋይ የለማኝ ገቢ የሚያጠኑና የሚያስጠኑ አሉ ። አንድ ሰው ዬኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከፍሎ የለማኝ ገቢ ያስጠና ነበር ፣ ጥናቱ ካላቀ በኋላ አትስጡ ይል ነበር ። ይህ ሰው እንዳይሰጥ ስስቱ ፣ እንዳይተው ስብከቱ አስጨንቆት ነው ። የሰጪዎች መስጠት ንፉጎችን ምክንያተ ብዙ ያደርጋቸዋል ። ይህ የሚያሳየው ደጎች ንፉጎችን በተግባር  እንደሚገሥጹ ነው ።

ኤልሳዕ በቤቱ ምርቃት ቀን ደስታው ትልቅ ሆነ ። ለካ አገልግሎታችን ሁሉም የገፋው አይደለም ፤ እንዲህ ያሉ ደጎችንም አፍርቷል ብሎ ተስፋው ከፍ አለ ። የዚህች ሴት ውለታ ከበደው ። አገልጋዩን ግያዝን ጠራውና “ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው ።” የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሲደረግላቸው የሚያውቁና የሚያመሰግኑ መሆን አለባቸው ። ውጦ ዝም መሆን ፣ ከዚህኛው የእገሌ ወጥ ይሻላል ብለው እንደ ቀላዋጭ ምስጋና ቢስ መሆን አይገባቸውም ። ዘርፈን እንጥፋ ብለው ሕዝቡን በጭካኔ የሚበዘብዙም መሆን አይገባቸውም ። ምስጋናን ማወቅ አለባቸው ። ይልቁንም ዛሬ እየቀለዱበት እንኳ የሚከተላቸውን ሕዝብ ሊራሩለት ይገባ ነበር ። ዛሬ የሌለበትን በሽታ ሲፈውሱት ከርመው የሚፈወስ እርግጠኛ በሽታ ሲመጣ ጥለውት ጠፉ ። እነ አባ ቁጭ ይበሉ ክፉ ቀንን አይወዱም ፣ ደጉን ቀን እያከፉ ይዘርፋሉ እንጂ ። በሽታን ሁሉ “መንፈስ ነው” የሚሉ ይኸው ዛሬ መንፈሱን ከዓለም ላይ ያስወጡልን ። ለአጉል ፈዋሽ ለንስሐ የሚያበቃ በሽታ ይሻላል ። በሽተኛ ለመፈወስ/ለመዳን ማመን ላያስፈልገው ይችላል ። በወንጌል ላይ በቤተሰብና በአገልጋዩ እምነት የተፈወሱ ብዙ በሽተኞች አሉና ። እምነት የሚያስፈልገው ለነፍስ ፈውስ ነው ። አላመንክም እያሉ በበሽታው ላይ ከሀዲ ነህ የሚሉት ፈዋሽ ነን ባዮች ጸጋችን አይደለም ብለው መድረኩን ቢለቁ ያማረ ነበር ። እነዚህም ዜጎች ናቸውና ቤተ ክርስቲያን አደራጅታ ፋብሪካ ብትከፍትላቸው ከብዙ ጥፋት ትድናለች ። መጋዝ ሲሄድም ሲመለስም እየቆረጠ ነው ። ሲክዱም ሲያምኑም ፣ ሲዋሹም ጌታ ጌታ ሲሉም የሚቆርጡ ሰዎችን ቤተ ክርስቲያን መከላከል አለባት ።

“በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች ። እርሱም፦ እነሆ ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ አሁንስ ምን ላድርግልሽ ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን ? በላት አለው እርስዋም፦ እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች ።”

ኤልሳዕ አሳቧን አደነቀ ። የተግባር መነሻ አሳብ ነውና ። ማድረግ ቢያቅታቸውም ያሰቡልን የተባረኩ ናቸው ። ኤልሳዕ ተቀባይ ብቻ አይደለም የሚሰጠው አለው ። የማይሰጥ ድሀ ፣ የማይቀበል ባለጠጋ የለም ። እንዲሁ የሚሰጥ እንዲሁም የሚቀበል የለም ። ለድሀ ሣንቲም ስንሰጠው እርሱ ደግሞ ደስታ ይሰጠናል ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ግን ከዚህ በላይ ነው ። ኤልሳዕ እንኳን የአገሩን የሶሪያን የመከላከያ ሚኒስትር ንዕማንን ማዘዝ የሚችል ነው ። ቤት አልባ ሁኖ አህጉርን ማዘዝ ይቻላል ለካ ! ለሠራዊት አለቃ የሚነግርላት ማንም እንዳይነካት ነው ፣ ለንጉሥ የሚነግርላት ርስት እንዲሰጣት ነው ። ይህች ሴት ግን ከምድር ተቀብላ የሰማዩ እንዳይቀርባት የምታስብ ሴት ናት ። አይሆንም አለች ። በኑሮዋ የረካች ሴት ናትና ። የሠራዊት አለቃ አያስፈልገኝም በዙሪያዬ ያለው ወገኔ ነው ይጠብቀኛል አለች ። በርግጥም ትልቅ ሴት ነበረች ። ሕዝቡን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ጠባቂ ታየው ነበር ። በርግጥም እንዳመነው ይሆናል ። ርስትም አልሻም አለች ። ያለኝንም በቅጡ ከበላሁት ዕድለኛ ነኝ ማለቷ ነው ። የተረጋጋ ኑሮ የምትኖረው ፣ በረጋ አሳብም የጠራ ምክር የምትፈጽመው በመጠን በመኖሯ ነው ።

ኤልሳዕ ደስታውን መቆጣጠር ስላልቻለ ፣ የሚያደርገው ስለጨነቀው ምን ላድርግልሽ ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን ? አላት ። እንደዚህ የሚያስደስት ተግባር የፈጸመች ሴት ስሟ ማን እንደሆነ አልተጻፈልንም ። ስም የላትም ፤ ስም ካላቸው በላይ ግን ትሠራለች ። ዛሬም ስሙን ያንጠለጠሉት የማይሠሩትን ስም የለሾች ይሠሩታል ። ስም ብቻ ሆኖ ከመቅረት እግዚአብሔር ይጠብቀን ።

ሁሉም ሰው ይወደኛል ማለት ሞኝነት ፣ ሁሉም ይቀበለኛል ማለት ዓለምን አለማወቅ ነው ። ድካማችን አንድ ሰውም ካተረፈ ትልቅ ነገር ነው ። እንዳሰብነው አገር ባያምን ፣ ሕዝቦች በአንድ ዜማ ለኅብረት ባያዜሙ ደህና ነው ። የቆሮንቶስ ሰዎች በሀብታቸው ሳይባረኩበት የፊልጵስዩስ ሰዎች ከድህነታቸው ቀንሰው እስረኛውን ጳውሎስን በማሰባቸው ተባረኩ ። የጳውሎስ አምላክ እንደ ባለጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ ሞላባቸው ። ልጅ እንደ ራሱ እንጂ እንደ ወላጁ አይደለም ። እንደ እኛ የሚያስቡ ልጆችን ባንወልድ ፣ እንደ እኛ የሚሮጡ ደቀ መዛሙርትን ባናፈራም ደህና ነው ። ደህና ነው ማለት የሰውን ትቶ የእግዚአብሔርን ማሰብ ነው ። አዎ ደህና ነው ።

ደህና /4
ሰኔ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ