መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ደብረ ታቦር

የትምህርቱ ርዕስ | ደብረ ታቦር

እንኳን ለ 2017 ዓ.ም. የደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

የታቦር ተራራ ማለት ነው:: በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ተራራ ነው:: አራቱ  ተራራዎች በጌታችን አገልግሎት ከፍ ብለው ይታያሉ:— የመጀመሪያው የደስታ ሕይወት የሚገኝበትን ምሥጢር ያስተማረበት የብፁዓን ተራራ ነው፣ ሁለተኛው ክብሩን የገለጠበት የታቦር ተራራ ነው። ሦስተኛው የመጨረሻውን ቀን ምልክት የተናገረበት የደብረ ዘይት ተራራ ነው። አራተኛው ዓለምን በደሙ ፈሳሽነት ያዳነበት የቀራንዮ ተራራ ነው። ጌታችን የገለጠው መለኮታዊ ክብሩ የእሳት ፍንጣሪ፣ የምጣድ ብልጭታ የምታህል የደቀ መዛሙርቱን አቅም ያገናዘበ ነው። ሙሴ በደብረ ሲና ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ በተመለሰ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፣ እስራኤል ሊያዩት ስላልቻሉ ፊቱን በጨርቅ ሸፈነ፤ እንዲሁም ጌታችን ራሱን በሥጋ ሰውሮ ባይመጣ ኖሮ ማንም ሊያየውና ሊቀርበው አይቻለውም ነበር። ከአሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ሦስቱን የዚህ ክብር እድምተኞች አደረጋቸው። ጴጥሮስ መስቀልን ይሸሽ ነበርና ከመስቀል በኋላ ያለውን ክብር አሳየው። ያዕቆብና ዮሐንስ ምድራዊ ሥልጣንን ይፈልጉ ነበርና በትሕትና የሚኖረው ኃይልና ክብር አጥቶ አለመሆኑን አሳያቸው።

በዚህ ዓለም ላይ ሰዎች የደስታ ጥያቄ አለባቸው ፣ የዚህን መልስ በብፁዓን ተራራ ላይ ገለጠ። አምላካቸው በክብሩ እንዲገለጥ የተጠቁ ሁሉ ይናፍቃሉ፣ ስለዚህ በደብረ ታቦር ክብሩን ገለጠ። ይህ ዓለም መጨረሻ እንዳለው ሁሉም ያምናል፣ የምጽአቱን ምልክት በደብረ ዘይት ገለጠ። ዓለም ያለ መሥዋዕት አይድንም፣ ለእኔ የሚኖር ሰው አጣሁ የሚል ብዙ ብሶተኛ አለ። ጌታችን በደብረ ቀራንዮ ተሠዋ፣ ለእኛ የሚኖር ብቻ ሳይሆን የሞተም ልዩ ፍቅር ተገለጠ።

መስቀልና ክብር ትይዩ ናቸው። መስቀል ይቀድማል፣ ክብር ይከተላል። ከመስቀል በኋላ ክብር ይመጣል ብሎ መጠበቅ ለሰው ደካማ እምነት ከባድ ነው። ጌታችን በደብረ ታቦር የገለጠው ከመስቀል በኋላ ያለውን የአማኞች ክብር ነው ። ሞቱ ሲቀርብ ክብሩ መገለጥ ጀመረ። ይህ ክብርም ከውጭ የመጣ ሳይሆን ከውስጥ ያበራ ነው።

ብሉይና ሐዲስ በደብረ ታቦር ተገናኙ። ዐቃቤ ሕጉ ሙሴ ፣ ነቢዩ ኤልያስ መጡ ። ኦሪትና ነቢያት የመላው ብሉይ ኪዳን ስም ነው ። በደብረ ታቦር የአዲሱ ኪዳን ፍጹም መካከለኛ ክርስቶስ አለ (1ጢሞ. 2:5)። ጌታችን ከሙሴና ከኤልያስ ጋር የመከረው ስለ መስቀል ነው። መስቀል አስቀድሞ የተተከለው በገነት ነው። ያንን መስቀል ሙሴ በመሠዊያው፣ ኤልያስ በቅድስና ጩኸት ገለጡት። ድኅነት የብሉይና የሐዲስ ዋና ርእስ ነው።

ዮርዳኖስና ደብረ ታቦር ትይዩ ናቸው። በሁለቱም ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጧል። ከዮሐንስ መጥምቅ ክብሩ ከፍ ያለውን ልጁን እግዚአብሔር አብ ለዓለም ገልጧል። አሁንም ከሙሴና ከኤልያስ የከበረ መሆኑን በደብረ ታቦር እግዚአብሔር አብ መሰከረ (ማቴ. 17:1-8)። መንፈስ ቅዱስ በዮርዳኖስ በአምሳለ ርግብ ወረደ ፣ በደብረ ታቦር በብሩህ ደመና ተገለጠ። አምሳለ ርግብ የኖኅ ዘመንን ሲያስታውስ፣ ብሩህ ደመና እስራኤልን ዐርባ ዓመት በምድረ በዳ የከለለውን ጥላ ያስታውሳል። ምንም በአጭር ቁመት ፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ በመካከላቸው ቢገኝም ሊሰሙት የሚገባው አንድ ልጁን ክርስቶስን እንደሆነ አባቱ መሰከረ።

ከዚህ ታላቅ ክስተት በኋላ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው አለ። ከተራራው ወርዶ ኢየሱስ እንዳይሰቀልበት ብሎ ነው። ያለ መስቀል ድል የለም። መስቀል ካልቀደመ ክብር አይከተልም። ጌታችን ኢየሱስ የሚሞተው መላ አጥቶ ሳይሆን በፈቃዱ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ይህ የገባው ከብዙ ዘመን በኋላ መሆኑን ራሱ ገለጠ:— “ከገናናው ክብር :- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና ፤ እኛም በቅዱሱ  ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።” (2ጴጥ 1: 17)።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠሩት ደብረ ታቦር አንዱ ነው። ዘጠኙም ዐበይት በዓላት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ናቸው። ከበዓላትም ዐበይት (ታላላቅ) የተባሉት ከጌታችን ክብር የተነሣ ነው። ታዲያ ይህች ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን አታውቅም ለማለት  እንዴት ተደፈረ ?

በዓሉ “ቡሄ” የሚል መጠሪያ አለው። ቡሄ ማለት መላጣ፣ ገላጣ ማለት ነው። ጌታ ክብሩን ስለ ገለጠ የተሰጠ ስያሜ ነው። ገናና ድምፅ ከሰማይ መምጣቱን ለማመልከት ጅራፍ ይተኮሳል፣ ይጮኻል። ችቦ የሚበራውም ብርሃነ መለኮቱ መገለጡን ለማመልከት ነው። ሕፃናትን በምሳሌ የሚያስተምር ነው። ይህ በዓል ልጆችና ወጣቶች በኅብረት እንዲያድጉ ያደርጋል፣ ያፋቅራል። የክርስትና ዓላማ የሕዝቦች አንድነት ነውና በዓሉ ያስተሳስራል።  በዚህ ቀን ለዘመድ ፣ ለአማች፣  ለምራት…  ዳቦ ይላካል። የቆሎ ተማሪም ለምኖ የደገሰውን በዚህ ቀን ለሕዝቡ ይጋብዛል። ደብረ ታቦር በነሐሴ 13 ቀን ይከበራል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ዛሬም መስቀልን ሽሽተን ለምንቀጥፍ ለምንዋሽ ልጆችህ  ክብርህን  ግለጥልን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ