የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደብረ ዘይት

                              የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ……  ቅዳሜ፣ መጋቢት ፭/ ፳፻፯ ዓ.ም.
የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል፡፡ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ (ማቴ.24÷ 3)፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
 
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወሰ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአን ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት”
ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በተእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።”
 
ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24ን ነው፡፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታ እንደማይሰማቸው ይገልጣል፡፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን መቆም አይችሉምና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም እመጣለሁ ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል፡፡ ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡ የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው፡፡ በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል፡፡ ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ አይመጣም፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ይመጣል፡፡ ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣ ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል፡፡ ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም፡፡ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡

የጌታችን ዳግም ምጽአት፡-
1.     የጸሎታችን መልስ ነው።
2.    የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።
3.    የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
4.    የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
5.    የእምነታችን ክብር ነው።
6.    የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
7.    የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡ 
 
                                የጸሎታችን መልስ ነው
ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ፡፡ ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። ልበ ሙሉ ሆነው ኃጢአት እንዳይሠሩ የመምጣቱ ዜና ስለሚረብሻቸው ነው፡፡ የጌታችን ዳግም ምጽአት በሚታሰብበት ቀን እንኳ ብዙ የኃጢአት መታሰቢያ ሲደረግ ይውላል፡፡ ለብዙ ሰዎች እኩለ ጾም ከሥጋና ከስካር ከተላቀቁ አንድ ወር መሆኑን ለመገናኘትም ወር እንደሚቀራቸው የሚያስቡበት ቀን ነው፡፡ በጊዜያዊ ጨዋነት የሰነበቱትም ሲሰክሩ የሚውሉበት የተውኔት ቀናቸው ነው፡፡ ሃይማኖት የማይሞት ኃይል ነው፡፡ ከሰው ልብ ግን ሊሞት የሚችለው ሰዎች እንደ ባሕል ቆጥረውት ሲኖሩ ነው፡፡
 
የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው፡፡ የምንፈራውና ያርቅልኝ የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥት ትምጣ” እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው፡፡ የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው፡፡ በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ. 14÷17)፡፡ የክርስቶስ መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው፡፡ ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው፡፡
 
የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆች የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና”ይላል (ሮሜ. 8÷19)፡፡ ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል (ቁ.22)፡፡ በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው፡፡ እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግድ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል፡፡ የራሱም ዕረፍት ነው፡፡ ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን፡፡ ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን፡፡ የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው፡፡
 
የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው
ማራናታ ማለት ጌታ ይመጣል ወይም ጌታ መጣ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 609)፡፡ ይህ ቃል ዮሐንስ ራእዩን ሲዘጋ ተጠቅሞታል፡- “ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ. 22÷20)። ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት ጣር ካየ በኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ማራናታ አለ፡፡ የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ ሞት ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ መከራ ገደብ ያገኛል፡፡
 
የተስፋችን ፍጻሜ ነው
የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡፡ የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም፡፡ ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እስከማያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የተባረከው ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ. 2÷12-13) ይላል፡ ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ፡፡ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡ የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው፡፡  
የእምነታችን ክብር ነው
ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን በጉን እረኛችን አድርገን ወደ ፍስሐ ዓለም እንገባለን፡፡
 
የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው
በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፤ ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ. 21÷1)፡፡ አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው፡፡ አሁን ፍጥረት አርጅቷል፡፡ በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨመረ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው፡፡ ይህን አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት ነው፡፡ ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል፡፡
የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው
ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ፡፡ ገነት ጊዜያዊ የነፍሶች ማረፊያ ናት፡፡ ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ፡፡ መንግሥተ ሰማያትና ገሀነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41)፡፡
 
የዘላለም ዘመንም ይከፈታል፡፡ ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን፡፡
 
የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል፡፡ 
“አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ& ቶሎ ና” /ራእ.22÷20/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ