የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደኅና ነው /7

ይህ ዓለም ደስታና ኀዘን ጎን ለጎን የሚሄዱበት ዓለም ነው ። ደስታን ኀዘን ይከተለዋል ፣ ኀዘንንም ደስታ ይተካዋል ። ከቶ የማይጨልም በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው ። ቀን እንዳለ ሌሊት አለ ፣ ብርሃን እንዳለም ጨለማ አለ ። ከደስታው ለኀዘን መዘጋጀት ፣ ከኀዘኑም ለደስታው ትምህርት መውሰድ ተገቢ ነው ። ከደስታው ለኀዘን ዘመን ያልተዘጋጀ ይጎዳል ፣ ከጥጋብ ዘመን ለረሀብ ዘመን ማስቀመጥ ዮሴፋዊ ጥበብ ነው ። ከረሀብ ዘመንም ለቀጣዩ ደስታ ትምህርት መቅሰም ተገቢ ነው ። ከፍ ዝቅ ባይል ይህ ዓለም አሰልቺ ይሆን ነበር ። የወጣው ሲወርድ ፣ የወረደው ሲወጣ ሕይወትን ውብ ፣ ርእሱንም ልዩ ልዩ ያደርገዋል ። መካኒቱ ስትወልድ ፣ ብዙ የወለደችው ሲደክማት ይህን ከፍታና ዝቅታ የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው ። በደስታው በጣም አለመደሰት ኀዘኑን ለመቻል ይረዳል ፤ በኀዘኑም በጣም አለማዘን የደስታው ዘመን ላይ ጨለምተኛ ፣ የትላንት እስረኛ ከመሆን ያድናል ። ይህ ዓለም የልክ ዓለም ነው ። ጠጣር በኪሎ ፣ ፈሳሽ በሊትር ፣ ርቀት በሜትር የሚለካበት ዓለም ነው ። ነገሮችን በልካቸው መያዝ የኑሮ ጤንነት ነው ።

እግዚአብሔር ሰጥቶ የማይነሣ ነው ። ነሥቶም የሚሰጠው የበለጠ ሊያስደንቀን ነው ። አንዱ ነገር ቀድሞ አልነበረንም ፣ አሁን አለን ፣ ቀጥሎ ይጠፋል ። መልሶም ይገኛል ። መጀመሪያ ስናገኝ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ብለን አመሰገንን ። ሲወሰድብን ደግሞ የእኛ አለመሆኑን ተረድተን ለበጎ ነው አልን ፣ ሲመለስልን ደግሞ በማስተዋል መያዝ እንዳለብን ተረዳን ። እግዚአብሔር በአንዱ ነገር ሦስት ጊዜ እንደሚያስደስተን እንረዳለን ። መጀመሪያ ቢሆንልኝ እያልን በተስፋ እንደሰታለን ፣ ሁለተኛ ስንቀበል ፣ ሦስተኛ ሲመለስልን ደስ ይለናል ።

ያቺ የሱነም ሴት ልጇ አደገ ። አንድ ቀንም አጫጆች ወዳሉበት እርሻ ሄደ ። ይህ ልጅ አቅም አግኝቶ ወደ እርሻ ከሄደ ዕድሜው ከፍ እንዳለ እንረዳለን ። የእርሻ ቦታ ራቅ ስለሚል ለመጓዝ አቅም ነበረው ፣ አባቱንና እርሻውን ለማየት ከፈለገ ለማፍቀርና የወደፊት ቦታውን ለማየት ውስጣዊ ብርታት አግኝቷል ። ያለ ጠባቂ ብቻውን የመሄድ መብት ካገኘ ለአካለ መጠን ደርሷል ማለት ነው ።

ሁሉም ቀን አንድ ዓይነት አይደለም ። ታላቅ ዕድል የሚገኝበት ፣ ታላቅ አደጋም የሚደርስበት ቀን አለ ። እንዲህ ያለውን ቀን በጸሎት እንጂ በጉልበት ማሸነፍ አይቻልም ። ያ ልጅ ፣ የማታ ወርቅ ሁኖ የተሰጠው ያ ጎበዝ በአባቱ እርሻ ላይ ሳለ በድንገት ራሴን ፣ ራሴን አለ ። እንኳን ሰው እባብ እንኳ የሚሞተው ራሱን ሲመታ ነው ። ራስ ለክፉው እባብ እንኳ ገዳዩ ነው ። ራሴን ፣ ራሴን ብሎ በድንገት ባረቀ ። አባቱም ሎሌውን ጠራና ቶሎ ብለህ ወደ እናቱ ይዘኸው ሂድ አለው ። አባቱ ጋ የሌለ እናቱ ጋ ያለው ነገር ምንድነው  ካልን ፍቅር ነው ። ያ ፍቅር የሞት መድኃኒት እንደሆነ አባቱ አወቀ ። ያ አባት ጥንካሬ አለው ። ስለዚህ ከቤቱ ርቆ ይሠራል ። ያች እናት ፍቅር አላት ፣ በቤት ሁና ልጅን ታሳድጋለች ። እግዚአብሔር አንዱ ሰው ጥንካሬና ፍቅርን እንዲያገኝ ብሎ ልጅን በአባትና በእናት ፍቅር እንዲያድግ አዘዘ ። አንድ ልጅ በእኩልነት አባትና እናቱን አግኝቶ ማደግ አለበት ። አንዱ ሲጎድል ልጅ ባለ አንድ ክንፍ ይሆንና በሕይወት ሸለቆ ላይ መብረር ያቅተዋል ። አባቱን ሲያጣ ፈሪ ፣ እናቱን ሲያጣ ፍቅር የጎደለው ይሆናል ። ፍቅር አግኝቶ ጥንካሬ ካጣ ፈሪ ፣ ስሜቱ ቶሎ የሚጎዳ ስስ ይሆናል ። በትንሽ ፈተናም ይበረግጋል ። ጥንካሬ አግኝቶ ፍቅር ካጣም ለሰው ዋጋ የማይሰጥ ፣ ቁሳዊ ነገርን ብቻ የሚወድ ይሆናል ። ያ አባት ልኩን በትክክል ያውቀው ነበር ። እርሱ ጋ የሌለውንና ሌላው ጋ የሚገኘውን ያወቀ ሰው ብልህ ነው ። የልጇን ጠባይ በደንብ የምታውቀው ፣ የምታክመው እናቱ ነበረች ። ቆይቶ እንደምናየው እናቱ የሞት መድኃኒትም ፍለጋ የገሰገሰች ሴት ናት ። በርግጥምትልቅ ሴት ናት ።

በእግሩ የሄደው ልጅ በሸክም ወደ እናቱ መጣ ። ሰው ሲሄድና ሲመለስ የተለያየ ነው ። ሲሄድ ጤነኛ ሲመለስ ሬሳ ሊሆን ይችላል ። ራሱን ችሎ የሚቆመው ልጅ በወደቀ ጊዜ አህያና ሎሌ አልቻለውም ። አባቱን ሊያይ እርሻውን ሊመለከት ፣ አጨዳውን ሊያደንቅ የመጣው ልጅ እንዳሰበው አልሆነለትም ። የአጨዳው ስፍራ ጦር ሜዳ ሆነበት ። ቆሞ ሳይሆን ወድቆ ተመለሰ ። በቃሬዛ ወደ እናቱ የመጣውን እናቲቱ ግን ሳይከብዳት እስከ ቀትር ድረስ ተሸከመችው ። ሙቀትን መስጠት የሚሞት ልጅን ይመልሳል ። ሕይወትን እየተጋራን የምንኖርበት ዓለም ነው ። እናቲቱ ያ ጎረምሳ አልከበዳትም ። መቻል የአቅም ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነው ። ከፈቀድን የሚበልጠንን መሸከም እንችላለን ። ፍቅር ጉልበታም ያደርጋል ።

ሞት ግን የእናትን እቅፍም ፈልቅቆ ይወስዳል ። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና የሰው ዘበኛ አይመልሰውም ። የእናት ፍቅርም ከሞት አያድንም ። ከሞት የሚያድን የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው ። ይህች ሴት የልጇን ሕይወት ተቀምታ በድኑን እንደ ታቀፈች አወቀች ። ከዚህ በፊት የልጅ ሬሳን ማየትን አታውቅም ። የልጅ መጀመሪያዋ የሞትም መጀመሪያዋ ሆነ ። የማታውቀውን ነገር ዛሬ ልታውቀው ስለሆነ ተረጋጋች ። እውቀት መረጋጋትን ይጠይቃል ። አልጮኸችም ፣ አላፈረችም ፣ ወይኔ ልጄ አላለችም ። ሲታመም የላከውን አባቱን ሙቷል ብላ ለመጥራት ፣ ልጄን ምን አደረጋችሁት ብላ ለመክሰስ አሳብ አልነበራትም ። ዕድር ለመጥራት ፣ ዘመድ ለማሰባሰብ ፣ ንፍሮ ለመልቀም ፣ ድንኳን ለማዘርጋት ፣ አልቃሽ ለመጥራት ፣ ከፈን ግዙልኝ ለማለት አልቸኮለችም ። ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ብቻ ፈለገች ።

ሬሳውንም በእግዚአብሔር ሰው ሰገነት ላይ ፣ በአልጋው ላይ አጋደመችው። በሩንም ቆለፈችና ወደ ባልዋ የምጓዝበት አህያ ላክልኝ ወደ እግዚአብሔር ሰው እሄዳለሁ አለችው ። ባልዋም ልጁ እንደተሻለው አስቧልና አልጠየቃትም ። እናቲቱ ጋ መፍትሔ እንዳለ እርግጠኛ ነበር ። ሥራ ፣ ሥራውን የሚል በሚስቱ እምነት የነበረው ባል ነበረ ። ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ቀርሜሎስ ለምን ትሄጃለሽ  ለምንስ ታስቸግሪዋለሽ  በዓል ወይም የወር መባቻ ቢሆን ምግብም ይዘሽ ትሄጂ ነበር አላት ። ባሏ የተሸፈነለትን ትልቅ መርዶ አላወቀም ። ተጋርዶ የሚኖር ሰው ነበረ ። ሁለት ሰው ከሚጨነቅ እኔ ብጨነቅ ይሻላል የምትል ፣ እንደ እኔ ሌላው ላያምን ይችላል ብላ የምታስብ ሴት ነበረች ። ለባልዋ የልጇን ሞት ብትነግረው ብዙ ነገሮች ይዘባረቃሉ ። ሬሳ አስቀምጣ እንድትሄድም ማንም አይለቃትም ነበር ። እንደ ታመመች ተቆጥራ ትያዝ ነበረ ። ሰዎች የማይሸከሙት ከሆነ መንገር ጥቅም የለውም ። የት ቦታ መናገር እንዳለባት ታውቃለች ። ለባልዋ ጥያቄ ግን መልስዋ አጭር ነው ። “ደኅና ነው” የሚል ነው ። ሬሳ አስቀምጦ ፣ የልጅ ሞትን አይቶ ደኅና ነው ካለች እኛማ ደኅና ነው ለማለት እንዴት አንደፍርም  አላቃሽ ጋ ሳይሆን የሚጸልይልን የእግዚአብሔር ሰው ጋ መገስገስ እንዴት ያለ መታደል ነው !

ኤልሳዕም በሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ሂድ ይህች ሴት ምን ሁናለች  ተቀበላት አለው ። አጠገቡ እስክትደርስ አላስቻለውም ። የእግዚአብሔር ሰዎች ሩኅሩኅ ናቸው ። እርስዋ ግን ግያዝን “ደኅና ነው” አለችው ። የት ቦታ ማልቀስ እንዳለባት ታውቃለችና ዝም አለች ። የእግዚአብሔር ሰውን እግር ይዛ ማለቀስ ጀመረች ። ግያዝ ግን ሊያርቃት ፈለገ ። ኤልሳዕም ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት አለው ። ሴቲቱም እንዳትዋሸች ብዬህ አልነበረም ወይ  አለችው ። ኤልሳዕም ልጇ እንደ ሞተ አወቀ ። ግያዝንም በትሬን ያዝ ፣ ወገብህን ታጠቅ ፣ በመንገድ ለእግዜር ሰላምታም ቢሆን እንዳትቆም አለው ። ሴቲቱ ግን ፡- ሕያው እግዚአብሔርን አብረኸኝ ካልሄድህ አልተውህም አለችው ። ግያዝም ቀድሞ ሄደ ልጁ እንደ ሞተ አረጋገጠ ፣ በትሩን ቢያሳርፍበትም ምንም ድምፅ አልነበረም ። የእግዚአብሔር ሰው በትሩ እንኳ ሥራ ይሠራል ። ኤልሳዕም ወደ ቤት ገብቶ ከግያዝ ጋር ሆኖ በሩን ዘጋ ። ጸለየ ። በሕፃኑ ላይ ተጋደመበት ፣ ትንፋሽ ሰጠው ። ሕፃኑ ነቃ ። ከሞትም ተነሣ ። ለእናቲቱም ሰጣት ። እርስዋም ሰግዳ እግዚአብሔርን አከበረች ። ሲሞትም ሲነሣም ባሏ እንኳ አያውቅም ነበር ። “ደህና ነው” አለች ፣ ሁሉም ነገር ደኅና ሆነ ። ደኅና ነው ካልን ደኅንነት ይሆናል ።

ተፈጸመ

ደኅና ነው /7
ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ