የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 16

ዲቁና ትልቅ ሥልጣን ነው !

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ዲያቆን ማለት የዋህ ፣ ትሑት ፣ የልጅ አዋቂ ፣ ክንፉ የቀለለው ፣ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት “ወዴት?” ባይ ፣ የመለኮት ልዑክ ፣ የመላእክት አምሳል ፣ የካህኑ የመቅደስ ልጅ ፣ ማዕረግ ያለው ተላላኪ ፣ እውቀት ያለው እውቀት ፈላጊ ፣ የሕፃን ምሥጢረኛ ፣ የጳጳስ ምርኩዝ ፣ የኤጲስ ቆጶስ ሰነድ ጠባቂ ፣ በንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን አምላኪ ፣ ድንግል ፣ ቤተ ክርስቲያን እናቱ የሆነች ፣ እናትን በእናት የለወጠ ፣ የምሥጢራት አገልጋይ ፣ የቤቴል በር ከፋች ፣ ቢያዜም የሚያምርበት ፣ ቢስቅ የሚያስደንቅ ፣ ቢናገር የሚኮላተፍ አፈ ማር ፣ የገባሬ ሠናዩ ቄስ አዋጅ ነጋሪ ፣ ሰግዶ የሚያሰግድ ፣ የሊቁ አዳሪ ተማሪ ፣ የነገው ቄስ ፣ የነገው መነኰስ ፣ የነገው ጳጳስ ፣ ሁሉ የሚወደው ፣ ለመማር ማልዶ የወጣ ፣ አእይንተ እግዚአብሔር ካህናት የሚጠነቀቁለት ፣ ብዙ መካሪ ያለው ፣ የሚገሥጹት ልጅ ፣ የሚገርፉት ሹም ፣ በዓይን በጆሮ የሚማር ፣ የልብ አውቃ ፣ የወንጌል አክባሪ ፣ ዘመኑን ያተረፈ ፣ የአዲስ ኪዳን ነቢይ ሳሙኤል ፣ የዓመተ ምሕረት ነቢይ ኤርምያስ ፣ ታናሽነቱ የማይናቅ ፣ መሥዋዕት ቀማሚ ፣ በዕርፈ መስቀል ደመ ኢየሱስን አቀባይ ፣ የሥልጣን መሠረት ፣ ዕደግ ተብሎ የሚመረቅ ፣ ቢረግጡት ምንጣፍ ፣ ቢደገፉት መከዳ የሆነ ፣ እያፈረ የሚቀድስ ፣ እየፈራ የሚያስተምር ፣ የትምህርት ሱሰኛ ፣ በልጅነት የዘመተ ፣ የአባቱን ቤት ለጽድቅ የመነነ ፤ የእናቱን ጓዳ በልመና እንጀራ የለወጠ ፣ ተንቀሳቃሽ ተማሪ ፣ የብሉይ ጓደኛ ፣ የሐዲስ መሽራ ነው።

ዲያቆንን የማይወድ ማን አለ ? እግዚአብሔርን የሚወድድ ሁሉ ይወደዋል ። ዲቁና ትልቅ ሥልጣን ነው ። የልጅነት ጨዋታን ለጌታው የሠዋ ፣ ከአብሮ አደጎቹ ይልቅ በዕድሜ የገፉትን አባቶች የመረጠ ፣ በየዕለቱ በአበው የሚመረቅ ፣ የየዋሃን የጸሎተኞች ቱፍታ ያረፈበት ነው ። ዲያቆን ቢያዜም ያምርበታል ፣ አንድ ልብ ነውና የኑሮ ሸክም አልመጣበትምና እውቀት ይጠልቅበታል ። የቄስ ፣ የጳጳስ ፣ የፓትርያርክ መሠረት ነው ። ሁሉም ዲያቆን ጳጳስ አይሆንም ፣ ሁሉም ጳጳስ ግን ዲያቆን ነበረ ። ዲቁናን ሁሉ ሊያከብረው ይገባል ። ዲያቆናት ሠልጣኝ ወታደር ፣ ተማሪ ደቀ መዛሙርት ፣ ወራሽ ልጆች ናቸው ። የነገዋ ቤተ ክርስቲያን በዛሬዎቹ ዲያቆናት ትታያለች ። ዲያቆናት አበባ ናቸውና እንክብካቤ ይፈልጋሉ ፤ የከተማ መናኝ ናቸውና ጥበቃ ይሻሉ፣ ቆብ አልባ መነኮስ ናቸውና ከሴት ርቀው ንጽሕ ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል ። ዲቁና መሠረት ነውና መሠረቱ የጸና መሆን አለበት ። ዲቁና ከተበላሸ ሁሉም ነገር እየተበላሸ ይመጣል።

ዲያቆናት ጭምት መሆን አለባቸው ። እኮ ጭምት ማለት ምን ማለት ነው ? ጭምት ማለት ጣፋጭ ዝምታ ፣ ጣፋጭ ዝግታ ፣ ጣፋጭ ዕይታ ያለው ማለት ነው ። ጭምት ዱዳ አይደለም፣ ጭምት ለፍላፊ አይደለም ፤ ጭምት በቦታው ተገቢ ነገርን የሚናገር ነው ። የበደለ ሲያይ “የእኔን መጨረሻ አሳምርልኝ” ብሎ እያለቀስ የሚመክር ነው ። ድምፁ እንደ አዋጅ ድምፅ አይደለም ። ያልሰማህ ስማ ፣ የሰማህን ላልሰማ አሰማ አይልም ። ዲያቆን የበላዩም የበታቹም ሲሳሳት በጭምትነት ይጸልያል ፣ በወዳጅነት ይመክራል። የቤተ ልሔም ምሥጢር ጠባቂ ነው ። የቤተ ልሔም ድንግል ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር ። ዲያቆንም ብዙ የማይደነቅ ፣ ብዙ የማይደነግጥ ነው ። ጭምት ለነገው የሚያስብ ፣ መጨረሻው እንዲያምር የሚጸልይ ነው ። ጭምት የሁል ጊዜ ተማሪ ነው ። ጆሮው እንደ ዝኆን ጆሮ ሁሉን የሚያደምጥ ፣ መልካሙን የሚቀበል ነው ። ጭምት ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ማንንም ድጦ የማያልፍ ነው ። ጭምት ባይርበውም ለራበው ያዝናል። ራሱን ብቻ ሳይሆን ዙሪያውን ያያል።

ዲያቆን የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም ። እንደ ውኃ እናት ከውኃ አይለይም ፣ ከውኃ ውጭ አይደፍርም ። አለልክ መብላትም የመስከር ያህል ነው ። ዲያቆን መጥኖ የሚበላ ፣ በምግብ ብዛት ዕድሜውን የማይጐዳ ነው ። ዲያቆን ከብዙ ሴቶች ጋር ወዳጅ የሚሆን ፣ የቆነጃጅት አጃቢና አጫዋች አይደለም ። መፍራት ገደሉን ሳይሆን የሚያዳልጠውን ስፍራ ነው ። አርቆ ማጠር የዲያቆን መገለጫ ነው ። አንድ ዲያቆን እውቀት ፣ ምሥጢር ጠባቂነት ፣ ጠንቃቃነት ያስፈልገዋል ። እንደ ወታደር የሚዘምት ፣ እንደ ሰላይ ለቤተ ክርስቲያት ጆሮ የሆነ ነው ። መጠጥና ሴት የሚወድድ ወታደርም ደኅንነትም መሆን አይችሉም ። ሁለቱም ጎበዙን ሁሉ ወንፊት ያደርጉታልና ። ዲቁና ትልቅ ሥልጣን ነው ። ብሉይ ሐዲስን ነገር መለኮትን ላላወቀ አይሰጥም ። ዲቁና ትልቅ ሥልጣን ነው ። ምእመናን ሊያከብሩት ይገባል ። ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ ዲያቆን ነበረ ። የቤተ ክርስቲያን አባት ለመባል ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡-

1- ክህነት ያለው ፣
2- ኢአማንያንን አሳምኖ የመለሰ ፣
3- መንፈሳዊ መጻሕፍትን የጻፈ መሆን አለበት ። ዲያቆን ሆነው የቤተ ክርስቲያን አባት የሆኑ አሉ ። ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ዲያቆን ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አባት ነው ። ዲያቆናት አባት ሊሆኑ ይችላሉ ።

አዎ መስፈርት ያስፈልጋል ። የቃል ትምህርትና ዜማ ብቻ መስፈርት አይሆንም ። ዲያቆን የሚያነበውን መተርጎም ፣ የተረጎመውን መኖር ያስፈልገዋል ። እኔ ጢሞቴዎስ ወደፊት መስፈርት የሌለው ዘመን እንደሚመጣ ፣ ከአላውያን ነገሥታት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችዋ አገልጋዮች ይሆናሉ ። የቄስ ክብር ፣ አጥሩ ዲያቆን ነው ። የካህኑ ልጅ ነውና ሊያለብሰው ፣ ሊያበላው ፣ ሊያስከትለው ፣ ሊያሰለጥነው ይገባል ።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 16
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ