“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።
በበጎ ፈቃዱ ብሎ እግዚአብሔር አብን ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ብሎ እግዚአብሔር ወልድን ፣ ልጆቹ ልንሆን ብሎ ዳግም የሚወልደንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አነሣ ። መዳናችን ሥላሴያዊ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም ። “ኢየሱስ ብቻ” የሚል ትምህርት የሰባልዮሳውያን ኑፋቄ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ። በበጎ ፈቃዱ የሚለውን ለማየት እንሞክር ። እግዚአብሔር ፈቃድ ያለው አምላክ ነው ። ይህም አካላዊነቱን ያስረዳናል ። እርሱ ሰውን በመልኩ በመፍጠሩ የሰው ልጅም ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው ። በዚህ ክፍል ላይ የተጠቀሰው ፈቃድ ነጻነት ተብሎ የሚተረጎመው ፈቃድ አይደለም ። የተግባር ዋዜማ የሆነው ፈቃድ ነው ። በሌላ አገላለጽ ቁርጥ አሳብ ማለት ነው ። በአሳቡና በተግባሩ መካከል የጊዜ ርዝመት እንጂ መለያየት የሌለበት ፣ የሆነ ያህል የሚቆጠር ነው ። እግዚአብሔር አሰበ ስንል አደረገ ማለታችን ነው ። በእግዚአብሔር ፈቃድና ተግባር መካከል የሚያሰጋ አዲስ አሳብ ሊመጣ አይችልም ። ፈቃደ ሥላሴን በሚመለከት ሦስት ነገሮች ጉልህ ሁነው ይታያሉ ። በፈቃዱ እኛን ለመፍጠር ፣ ለማዳንና ልጆቹ ለማድረግ ወሰነ ። እግዚአብሔር የወሰነው እኛን ለማራቅ ሳይሆን ልጆቹ ለማድረግ ነው ። እርሱ ደግሞ የወደደው ሰውን እንጂ እነ እገሌን አይደለም ።
ብዙ ወላጆች ልጃቸውን በሚመለከት ሲናገሩ በስህተት በወጣትነት ዝላይ የወለድሁት ነው ይላሉ ። እግዚአብሔር ግን በፈቃዱና በውሳኔው እንጂ በስህተት አልወለደንም ። እርሱ ልጆቹ ካደረገን እርሱ አባታችንም እናታችንም ነው ። እርሱ ልጆቹ ካደረገን እኛን ለመውለድ በመስቀል ምጥ አልፏል ማለት ነው ።
በሰው ነፍስ ውስጥ አሳብ ፣ እውቀት ፣ ስሜት / መነቃቃት ፣ ፈቃድ ወይም ውሳኔ የሚባሉ ነገሮች አሉ ። ነፍስ ብዙ ክፍልፋይ ያላትና እስካሁን ድረስ ተጠንታ ያልተደረሰባት ናት ። ሰውን ሙሉ አካሉን ብንጨብጠው አወቅነው ማለት አይደለም ። ሰው ከዓለም ይልቅ የሚሰፋ ፍጡር ነው ። ይህ ስፋት ያለው በነፍሱ ውስጥ ነው ። በሥጋው እዚህ ይታያል ፣ በአሳቡ ግን ዳርቻዎችን ያስሳል ። ሰው ሰፊ ፍጡር ነው ። አሳብ የነገሮች ሁሉ ፅንሰት ነው ። ይህ ዓለም እንኳ የተበጀው አስቀድሞ አሳብ መጥቶ ነው ። አሳብ ከቀደመ መንገደኛ ፍጡር የለም ። ግብ ያለው ፍጡር ግን አለ ። አሳብ የእውቀት መገኛ ነው ። ማሰብ ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ነው ። ሰውን ሰው የሚያሰኘው ቅርጹ ሳይሆን አሳቡ ነው ። በቅርጽ ከሆነ እኛን በጥቂት የሚመስሉ እንስሳትም አሉ ። ማሰብ ነጻነት ይፈልጋል ። ነጻነት ከሌለ ማሰብ ፣ ማሰብ ከሌለ እውቀት ሊኖር አይችልም ። እውነተኛ ነጻነትም የመሳደብ ሳይሆን የማሰብ መብት ነው ። የአሳብ ነጻነት ከሌለ እውቀትና ምርምር ሊኖር አገርም ሊያድግ አይችልም ። የአፍሪካ መሪዎች እንኳን ተናግሮ አስበህ ነበር በማለት ሰውን ያንገላታሉ ። ራሳቸውን እንደ አማልክት ስለቆጠሩ ሰው የሚያስበውንም ያውቃሉ ። በአገራችንም እያንዳንዱ ሰው የአሳብ ጨቋኝ ይመስላል ። አሳብ እንደ ጠላት እንድንተያይ ፣ ጦር እንድንማዘዝ ያደርገናል ። አሳብ በአሳብ እንደሚሸነፍ ማመን ይቀረናል ። ሰው የወደደውን እንዲያምንና እንዲከተል እንፈቅዳለን ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። የአሳብ ጨቋኝ ከሆንን በአገራችን ላይ ከመቶ ሚሊየን በላይ አምባገነን አለቆች አለን ማለት ነው ።
ከአሳብ ቀጥሎ እውቀት ይመጣል ። እውቀት ጫፉ የተጨበጠ እንጂ ያለቀ ማለት አይደለም ። እውቀትን የጀመራት እንጂ የጨረሳት የለም ። ከምናውቀው የማናውቀው ይበዛል ። የምንማረውም አለማወቃችንን አውቀን ትሑት እንድንሆን ነው ። አላዋቂ ደፋር ነውና ከዚያ ለመዳን መማር ያስፈልገናል ። እውቀት ሰው ነፍሱን ከዝገት የሚጠብቅበት ትልቅ እንቅስቃሴና ዘይት ነው ። ዝገትን ለመከላከል መንቀሳቀስና ዘይት አስፈላጊ ነው ። ዝገት አንድ ነገር ለተፈጠረበት ነገር ባለመዋሉ የሚመጣ ድርቀት ነው ። ለተፈጠሩበት ነገር መኖር ዕድሜን ያረዝማል ። መኪና ለመሄድ ስለተሠራ በተጓዘ ቍጥር ዕድሜው ይረዝማል ። እውቀት ጠል የሆነ ማንነት ውስጥ ያለ ሰው ስለሚዝግ ሰውን ይመርዛል ፣ ቀጥሎ ራሱ ይጠፋል ። እውቀት ጠል የሆኑ ሰዎች አጥፍቶ ጠፊዎች ናቸው ። ይሉኝታ ስለሌላቸው አውርተው አያባሩም ። ትምህርት ቤቶች እውቀትን የምናገኝባቸው መስኮች ናቸው እንጂ ብቸኛ መንገዶች አይደሉም ። ለሚማር ሰው ሁሉ ቦታ ፣ ሁልጊዜ ትምህርት አለ ። ከአሳብ ቀጥሎ እውቀት የነፍስ ጓዳ ነው ።
ስሜት ለአሳብና ለእውቀት ያለን መነቃቃት ፣ ጉዞ ለማስጀመር ሞተር ማስነሣት ፣ መቀጣጠል መንደድና መሞቅ ነው ። ስሜት ውስጥ ኃይል አለ ። በአሳብና በእውቀት ያልተደገፈ ስሜት ግን አደጋ አለው ። ያለ ሙቀትና ያለ እልህ ሥራ መሥራት አይቻልም ። መንፈሳዊ ቅንዓት አስፈላጊ ነው ። ቀዝቃዛነት ካልተወገደ ፣ ግለት ካልመጣ ራእይ ሊኖር አይችልም ። ስሜታዊ አንሁን እንጂ በስሜት የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት ይገባናል ። እግዚአብሔር ስሜታቸው ቶሎ በሚነካ ውስጣዊ ሙቀት ባላቸው ፣ ተነሣሽ ሰዎች ይደሰታል ። ቅዱስ ጴጥሮስን የመረጠው በብቃቱ ሳይሆን ቶሎ የሚነካ ውስጣዊ ሙቀት ያለው ስለነበረ ነው ። እግዚአብሔር መንፈሰ ቀዝቃዞችን አይወድም ። ውስጣዊ እሳት ከሌለ ከመሞታችን በፊት ሙተናል ማለት ነው ።
ከስሜት ቀጥሎ የምናገኘው ፈቃድን ነው ። ፈቃድ ቁርጥ አሳብ ፣ ወደ ተግባር ለመግባት አንድ እግርን ማንሣት ነው ። እግዚአብሔር በበጎ ፈቃዱ ሊፈጥረን ፣ ሊያድነንና ልጆቹ ሊያደርገን ፈቀደ ። ሰውን እንደገና የወለደ አባት እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /10
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም.
እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት