ድሀና የድሀ ልጅ ነኝ
“በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን ፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቍጣ ልጆች ነበርን ።” ኤፌ. 2፡3
ከኃጢአተኞች የምንለየው ምሕረት ያገኘን ኃጢአተኞች በመሆናችን እንጂ ፍጹማን በመሆናችን አይደለም ። የዳንን በሽተኞች እንጂ ከቶም ያልታመምን ጤነኞች አይደለንም ። እንደ ዓለማውያን ዓለማዊ ነበርን ። እምነትን በትሕትና እንይዘው ዘንድ ፣ በታመሙት ከመፍረድ የምናዝን እንድንሆን ፣ የቀድሞ ሙታን ተብለን ተጠርተናል ። አንዳንድ ሰዎች የቀድሞ አምባሳደር ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ይባላሉ ። እኛ ግን የቀድሞ ሙታን ነን ። የቀደመውን ኑሮ ማንሣት የፈለገው ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ያሻል ። የቀደመ ኑሮአችንን የሚያነሡ የተለያዩ ወገኖች አሉ ። ዛሬ እየበላን ከሆነ የረሀብ ዘመናችንን ሊያስታውሱን የሚፈልጉ አሉ ። ዓላማው አውቅሃለሁ የመኩራት መብት የለህም ብሎ ለማሸማቀቅ ይሆናል ። አንዳንዶች ደግሞ ለመጫወትና ያ ጊዜ አለፈ ብሎ አብሮ ለመደሰት ሊያነሡት ይችላሉ ። ሲያነሡት ግን ቍስሉ የሻረ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ። አሊያ የሰው ቀንን ማበላሸት ያመጣል ። ሐዋርያው የቀደመውን ኑሮ ማንሣት የፈለገው ታብየዋል ብሎም አይደለም ። እግዚአብሔርም የመጣንበት ሲጠፋን ያስታውሰናል ። ዳዊት ንጉሥ ሁኖ ወዳጁን በገደለ ጊዜ ፣ እርሱም አንድ ዘመን ወዳጁ የነበረው ሳኦል ወይም አማቹ የነበረው ንጉሥ ለሞት ይፈልገው የነበረ ፣ ከእረኝነት ሜዳ ቤተ መንግሥት የገባ መሆኑን ዘንግቶ ነበር ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ አስታወሰው፡- “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር ። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል ፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል ።” 2ሳሙ. 12፡7-9።
የትላንት ተበዳዮች የዛሬ በዳዮች ፣ የትላንት አልቃሾች የዛሬ አስለቃሾችን እግዚአብሔር ያስታውሳቸዋል ። ሰው ትላንቱን ማሰቡ ዛሬ ሌሎችን እንዳይበድል ሊያደርገው ይችላል ። ደግሞም “የመጣህበትን አትርሳ ፣ የምትሄድበት እንዳይጠፋህ” ይባላል ። ደግሞም “ያለህበትን ለማወቅ የመጣህበትን አትርሳ” ይላሉ ። በሌላ አገላለጽም፡- “ዓይንህ የፊቱን ቢያይ ልብህ የኋላውን ያስብ” ይባላል ። ትላንት ክፉ መምህራን ገጥመዋቸው ያለቀሱ ተማሪዎች ፣ ዛሬ መምህራን ሁነው ተማሪ ያስለቅሳሉ ። ትላንት በቤት ኪራይ ተመርረው “ምነው ኖሮኝ በነጻ ባኖርኩ” ያሉ ዛሬ የሚከፍሉአቸውን ያስጨንቃሉ ። የትላንቱ ከተረሳ የድፍረት ኃጢአት ይበዛል ። የተሰበሰበው የሚበተነው ፣ የተደራጀው የሚዝረከረከው ፣ በምናድንበት ቀን ገዳይ የምንሆነው ትላንትን ስንረሳ ነው ። የትላንትን መርሳት ባሕርይ አይደለም ፣ ቀን የሚጭንብን ግብዝነት ነው ። ራሳችንን እዚህ ምን ታደርጋለህ ብለን መገሠጽ አለብን እንጂ በግፍ መወዳደር አይገባንም ። ብዙ ያየነው ለመራራት እንጂ “እኔም ደርሶብኛል” ብለን ለመጨከን ፣ ቍስለኞችን ለመርገጥ ፣ ድሆች ላይ ጀግና ለመሆን አይደለም ። ምናልባት የትላንቱን አስበን ደጎች ስንሆን ሰዎች ይጨማለቁብን ይሆናል ። ምናልባት እግዚአብሔር እየፈተነን ይሆናልና መታገሥ ያስፈልገናል ። ከእግዚአብሔር መንገድ ከመውጣት የሰዎችን አመል ተሸክሞ መጕበጥ ይሻላል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ የትላንት ኑሮአቸውን ሲያስታውስ ራሱን ከእነርሱ እንደ አንዱ አድርጎ እንጂ ነጻ አውጥቶ አልነበረም ። ይህ የምክር ኃይል ነው ። ሰዎች ብቻህን ተሳስተሃል ስንላቸው ከመቀበል ይልቅ መቃወምን ይመርጣሉ ። ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆነን ስንናገር ግን ይቀበላሉ ። ስብከት የሚባለውም ይህ ነው ። ራስን አጽቆ ሌላውን መኰነን ሳይሆን ስብከት ራስን ከኃጢአተኞች ጋር ደምሮ “እኔ ከዳንሁ እናንተም ተስፋ አላችሁ” የሚል ድምፀት ነው ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን ሐዋርያው ጳውሎስ ነው ። “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ ፤” እንዲል ። 1ጢሞ. 1፡15። ስብከት ሌላውን ማቃለል ፣ ሕዝብ ላይ የመጮኽ ሥልጣን ፣ የማጋለጥ መርሐ ግብር ፣ የአውጫጭኝ ዕድር ፣ ሰው ሁሉ ረክሶ እኔ እንዴት ተቀደስሁ የሚል መመጻደቅ አይደለም ። አንድን ሰው በአሽሙር ለመንካት ሚሊየን ሰው የሚሰብኩ ሰዎች እንዳሉ እሙን ነው ። መድረኩና አትሮኖንሱ ግን የሥላሴ ነውና ልንዳፈረው አልተፈቀደልንም ። ራሳችንን ከበዳዮች እንደ አንዱ አድርገን ስንሰብክ ኃጢአተኛነት የሚያሰቃያቸው ወገኖች ለንስሐ ድፍረት ያገኛሉ ። የወዮልሽና የእሳት ሊዘንብ ነው አስተማሪዎች የጠፉትን ከመመለስ ይልቅ እያስደነበሩ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች አልባ ያደርጓታል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን ፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቍጣ ልጆች ነበርን” በማለት ለማስታወስ የፈለገው በክርስቶስ ያገኙትን የዛሬውን ድኅነት እንደ ቀላል እንዳይቆጥሩት ነው ። ለአዳኝነቱ ግብር ምስጋና ማቅረብ ፣ ዝማሬና ስብከትም ቀራንዮን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን መትጋት ይገባናል ። ሁሉም ሃይማኖቶች አምላካቸው ድል ነሺ እንደ ሆነ ይሰብካሉ ፣ የክርስቲያን አምላክ ግን ነፍሱን ለብዙዎች የሰጠ ፣ ሞተ ተብሎ በእርግጥ የተነገረለት ፣ ሞት ግን አልችለውም ብሎ የለቀቀው ወይም ሞትን በቃህ ብሎ ጉልበቱን የሰበረው ነው ። ስለቱን አስተካክለው ዘንዶ እንዲውጣቸው የሚያደርጉ ዘንዶ አዳኞች አሉ ። ገና እግራቸውን መዋጥ ሲጀምር እነርሱም በሰይፋቸው እየተረተሩት ይገባሉ ። ዘንዶው ጨርሼ ዋጥኋቸው ሲል ጨርሶ እንደ ሞተ አያውቅም ። ጠቢባንን ያሞኘ ሞት ፣ ገዥዎችን የገዛ ዘንዶ ጌታችን በቃሉ ስለት ፣ በሞቱ ድል አድራጊነት ሆድ ዕቃውን ወይም መቃብርንና ሲኦልን ተረተረው ። ታዲያ ለዚህ ጌታ ምን ይሰጠው ይሆን ! እኔ ድሀና የድሀ ልጅ በመሆኔ ተመስገን እለዋለሁ ። ቢኖረኝም ለውለታው ልክ መክፈል አልችልም ። እርሱ ከምስጋናዬ በላይ ነው ። አሜን ።
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /30
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም.